በኢሕአዴግ እጅ የወደቀው ድርድር | አፍሪቃ | DW | 30.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

በኢሕአዴግ እጅ የወደቀው ድርድር

መቼ እንደሚጀመር ስለማይታወቀው ድርድር ለመወያየት የተገናኙት ኢሕአዴግ እና 21ዱ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያለሥምምነት ተበትነዋል። መድረክ እና ኢዴፓ የድርድሩ እጣ-ፈንታ በገዢው ግንባር ውሳኔ ላይ የተንጠለጠለ ነው ብለዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:56

በሰባት ዙር ውይይት ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች አልተግባቡም

ከ26 አመታት በላይ በሥልጣን የቆየው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ግንባር እና ተቃዋሚዎቹ በአደራዳሪ አስፈላጊነት ላይ መስማማት ተስኗቸዋል። ተቃውሞ እና ኹከት በወለደው የድርድር ሐሳብ ላይ ሰባት ዙር ውይይት ያደረጉት ኢሕአዴግ እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትናንትም መስማማት ተስኗቸው ተበትነዋል። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና ሰማያዊ ፓርቲ አደራዳሪ ያሻናል ከሚሉት መካከል ይገኙበታል። ሰማያዊ ፓርቲ ከውይይቱ ተገፍቼ ወጥቺያለሁ ብሏል። አደራዳሪ አያስፈልገንም ከሚሉት መካከል ኢሕአዴግ፤ አንድነት እና ቅንጅት ይጠቀሳሉ። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ ኢሕአዴግ ገሸሽ እያለ ነው ይላሉ። «አደራዳሪዎቹ ሚናቸው እና ኃላፊነታቸው ተወስኖ ይሰጣቸዋል። በዚያ መሰረት ግራ ቀኙን የሚያሸማግሉበት መድረክ እንዲፈጠር» እንፈልጋለን የሚሉት ዶ/ር ጫኔ ገዢው ግንባር በጉዳዩ ላይ አቋሙን እንዲያስተካክል ጠይቀዋል።

ዶ/ር መረራ ጉዲና እና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በርካታ አባላቱ የታሰሩበት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ በበኩሉ «የ22 ፓርቲዎች ስብሰባ ድርድር ነው ብሎ ስለማያምን» ራሱን ማግለሉን አስታውቋል። «ኢሕአዴግ ተወያየሁ፤አወያየሁ ማለት እንጂ የሚፈልገው መደራደርን አጀንዳው አድርጎ አይደለም ጥሪ ያደረገልን።» የሚሉት የመድረክ ሊቀ-መንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ «የትም የማያደርስ ንግግር ውስጥ ከመቆየት ያለፈ ውጤት እንደሌለው በመገንዘባችን» ከውሳኔ ደርሰናል ብለዋል። «ከሒደቱ ጨርሰን አልወጣንም።» የሚሉት ፕሮፌሰር በየነ ለኢሕአዴግ በተናጠል የመደራደር ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እየጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢሕአዴግ እና ተቃዋሚዎቹ በውይይቱ በአደራዳሪ አስፈላጊነት ላይ ብቻ ሳይሆን በድርድሩ አካሔድ ላይም ከሥምምነት አልደረሱም። «በዙር እንደራደራለን ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች» መኖራቸውን የተናገሩት ዶ/ር ጫኔ ከበደ «በዙር የሚደረግ ድርድር በተለይ በአጀንዳ አቀራረፅና አያያዝ ዙሪያ ሥጋት» አለን ብለዋል።

መድረክ ስኬታማ ድርድር እንዲኖር ከተፈለገ ዛሬ ለአራት ወራት የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲሻር ይሻል። ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እንደሚሉት «የትኛው ወንጀል የትኛው መብት እንደሆነ» መለየት በሚቸግርበት ወቅት ድርድር ማድረግ የሚታሰብ አይደለም። ፕሮፌሰር በየነ በእስር ላይ የሚገኙ የመድረክ የፖለቲካ አመራሮች እና አባላት ሊፈቱ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የመድረክ ሊቀ-መንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስም ሆኑ የኢዴፓው ዶ/ር ጫኔ ከበደ የድርድሩ እጣ ፈንታ በገዢው ፓርቲ እጅ ላይ መውደቁን  ገልጠዋል። «ገዢው ፓርቲ እንደገና ነገሮችን አስቦ ወደ ድርድሩ መምጣት የሚያስችለንን መንገድ ካመቻቸልን ድርድሩ ይቀጥላል» ሲሉ ዶር ጫኔ ተናግረዋል።

የማኅበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያን ግን መቼ እንደሚጀመር በማይታወቀው ድርድር እምነት ያላቸው አይመስልም። «ስሜን አትጥቀሱ » ያሉን አድማጭ «ከኢህአዴግ ጋር መወያየት ሆነ በመደራደር መፍትሔ ሚመጣ አይመስለኝም።» ሲሉ መሰላቸታቸውን ገልጠዋል። «ኢህአዴግ ላለፉት 26 ዓመታት ድርድርን እንደ አንድ ከፖለቲካ ትኩሳት ማምለጫ ሲጠቀምበት ቆይቷል።» የሚሉት ሌላ ግለሰብ ደግሞ «አሁንም የድርድሩ ዓላማ ከዚህ የዘለለ እንዳልነበረ በግልፅ ያሳየበት ነው።» ብለዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic