በአፍሪካ ህገመንግስት ለይስሙላ | የጋዜጦች አምድ | DW | 17.02.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

በአፍሪካ ህገመንግስት ለይስሙላ

በቶጎ ጦር ኃይል አቀነባባሪነት የፕሬዝዳንትነት ስልጣን የጨበጡት ፋኡሬ ጌናሲግቤ በትናንትናዉ ዕለት ለህዝቡ በመገናኛ ብዙሃን ንግግር ያደርጋሉ የተባለዉ አልተሳካም። በምዕራብ አፍሪካ ለረጅም ዘመናት በስልጣን የሰነበቱ አባታቸዉን ሞት ተከትለዉ ፕሬዝዳንት ከሆኑ 11 ቀናት ብቻ ያስቆጠሩት ትንሹ ጌናሲግቤ ከምዕራብ አፍሪካ የምጣኔ ሃብት ማህበረሰብ በምህፃረ ቃል /ኤኮዋስ/ ጋር ያደረጉትን ስብሰባ ተከትሎ ነበር ንግግራቸዉ የተጠበቀዉ።

የመገናኛ ሚኒስትሩ ፒታንግ ቲቻላ ትናንትና ቀደም ብለዉ አዲሱ ፕሬዝዳንት በአገሪቱ ብሄራዊ መገናኛ ብዙሃን ለህዝባቸዉ ንግግር እንደሚያደርጉ ተናገሩ።
ህዝቡም ምሽቱን በጉጉት በየቡና ቤቱ ሳይቀር ጥቅጥቅ ብሎ ሞልቶ በቴሌቪዥን ሊከታተላቸዉ ሲጠባበቅ አመሸ።
በብሄራዊ ቴሌቪዥኑ የምሽቱ ተረኛ ሁለት የዜና አንባቢዎች ስለ ፕሬዝዳንቱ ንግግር ያነሱት የለም። በተጨማሪ ከባለስልጣናቱም በኩል የተሰጠ ማብራሪያ አልነበረም።
ከኤኮዋስ ጋር የተደረገዉ ዉይይት ትኩረቱ የጌናሲግቤን ፕሬዝዳንትነት ካፀደቀዉ ወታደራዊ ኃይል ወጥታ ቶጎ ህገ መንግስታዊ ሥርዓት እንድትከተል ማድረግ ላይ ነበር።
ዉይይቱም ዉጤታማና የሚያበረታታ እንደሆነ የኒጀር የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር አይቻቱ ሚንዳዉዶ ለአንድ ሰዓት ያህል ከአዲሱ የቶጎ ፕሬዝዳንት ጋር ከተወያዩ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ገልፀዋል።
4.7 ሚሊዮን ህዝብ ያላትና በጊኒና በቤኒን መካከል ተሰንቅራ የምትገኘዉ ትንሽየዋ የቶጎ ሪፐብሊክ ከምዕራብ አፍሪካ የምጣኔ ሃብት ማህበረሰብ የተሰነዘረላት የመፍትሄ ሃሳብ ሁለት ነዉ።
ባስቸኳይ የምክር ቤቱ አፈጉባኤ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ይሆናል ወደሚለዉ ህገ መንግስታዊ አሰራር መመለስና በ60 ቀናት ዉስጥ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማካሄድ።
አለያም በትንሹ ጌናስሲግቤ የሚመራና በተቻለ ፍጥነት ወደ ምርጫ የሚሄድ የአጭር ጊዜ የሽግግር መንግትስት ማቋቋም።
15 አባላት ያሉት ኤኮዋስ አማራጩን መተግበር ካቃታት በቶጎ ላይ እርምጃ እንደሚወስድባት ሲዝት የአፍሪካ ህብረትም በህገ መንግስታቸዉ ካልተመሩ የአገሪቱን ባለስልጣናት ከቦታ ወደቦታ መዘዋወርን በመከልከል ሃብታቸዉን እንዳያንቀሳቅሱ እንደሚያግድ አስጠንቅቋል።
በቶጎ ለረጅም ጊዜ በነፃነት ለመንቀሳቀስ ያልቻለዉ ተቃዋሚ ቡድን አምባ ገነኑ ኢያዴማ ከሞቱበት ዕለት አንስቶ ስርዓት ባለዉ መንገድ ተቃዉሞዉን እያሰማ ቢሆንም እንደታሰበዉ የህዝቡን ድጋፍ አላገኘም።
ህዝቡ ቡድኑን ተከትሎ ለተቃዉሞ እንዳይወጣ እስከ አፍንጫዉ ከታተቀዉና ለመሪዎቹ በሚገባ በመታዘዝ ከሚታወቀዉ የአገሪቱ የጦር ኃይል የሚሰነዘርበትን የበቀል ምላሽ ፈርቷል።
ያም ቢሆን ግን አዲሱን የቶጎ ፕሬዝዳንት እንደአባታቸዉ ለረዥም ዘመናት ሳይቆዩ በፊት ከስልጣን ለማዉረድ የሚደረገዉ ፓለቲካዊ ጫና ቀጥሏል።
ለአገሪቱ መንግስት ቅረበት አላቸዉ የሚባሉት ስምንቱ የቶጎ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጣቢያዎችም የተቃዋሚዎቹን ሃሳብ ሳይቀር እያስተላለፉ ነዉ።
ተቃዋሚዎቹ በሰጡት መግለጫም ህገመንግስቱን በመፃረር የተፈፀመዉን ተግባር በተመለከተ ለህዝቡ መናገራቸዉን እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
የቶጎ ባለስልጣናትም ጫናዉ በመብዛቱ ሳይወዱ በግድ ወደ ነበረዉ ህገመንግስታዊ አሰራር ለመምጣት መስማማታቸዉን ሆኖም ዉሳኔያቸዉ እንዴት ይፋ ሊሆን እንደሚችል እንዳላወቁ ይናገራሉ።
ኤኮዋስ ዉስጥ ከፍተኛ ሚና ያላት ናይጀሪያም በወታደራዊ ኃይል የሚፈፀም መፈንቅለ መንግስትን በተመለከተ ባላት የተቃዉሞ አቋም ጦሯን ወደ ቶጎ ልትልክ እንደምትችል ገልፃ ነበር።
ሆኖም ማክሰኞ ዕለት በተካሄደዉ ዉይይት ቶጎ ባለፉት ሳምንታት በአገሪቱ የተፈፀመዉን የስልጣን ጨዋታ ባስቸኳይ ወደ ነበረበት ጤናማ ሁኔታ እንደምትመልስ ተስፋ ሰጪ ዉጤት ላይ በመደረሱ ሃሳቧን ለዉጣለች።
በዛም አሉ በዚህ የሁሉም ቃል አንድ ነዉ ከእንግዲህ በአፍሪካ በስልጣንና በወታደራዊ ሃይል በመመካት ህገመንግስትን መጨፍለቅ ይብቃ።