በአፍሪቃ የነዳጅ ዘይት ሐብት ላይ ያተኮረው ትግል | ኤኮኖሚ | DW | 17.01.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

በአፍሪቃ የነዳጅ ዘይት ሐብት ላይ ያተኮረው ትግል

በዓለም ላይ የኤነርጂ ፍጆት መጨመር የነዳጅ ዘይት ምርት እጥረትን ያስከተለና በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ መድረክ ላይ ብርቱ ስጋትን የደቀነ ጉዳይ ነው። የነዳጅ ዘይት ዋጋ በቅርቡ ከዚህ ቀደም በማይታወቅ መጠን ወደ አንድ መቶ ዶላር መናሩ አይዘነጋም። “ጥቁር ወርቅ” የሚል ቅጽል ስያሜ የተሰጠው የተፈጥሮ ሃብት እንግዲህ የዛሬውን ያህል ውድ የሆነበት ጊዜ የለም።

default

ዩ.ኤስ.አሜሪካ የዓለምን የተፈጥሮ ሃብት በመልገል ቀደምቷ ናት። የነዳጅ ዘይት ፍጆትና ፍላጎቷም እየጨመረ ነው። ይሁንና በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት ሁለቱ ግዙፍ የእሢያ መንግሥታት ቻይናና ሕንድም በሚሊያርድ ለሚቆጠረው ሕዝባቸው የጥሬ ሃብት ድርሻቸውን ለማረጋገጥ ይፈልጋሉ። ታዲያ በተለይም በአሜሪካና በቻይና መካከል በዓለምአቀፍ ደረጃ የነዳጅ ሃብትን የመቆጣጠር ጠንካራ እሽቅድድም ነው የተያዘው።

የነዳጅ ዘይት ዋጋ ከመጠን በላይ መናር በዕውነትም ምንጭ ፍለጋውን እጅግ የጠነከረ አድርጎታል። ይህ አደን መሰል ሩጫ ደግሞ ወደ አፍሪቃ ማዘንበሉ አልቀረም። ፕሬዚደንት ቡሽ ትናንት በሳውዲት አረቢያ ጉብኝታችው በነዳጅ ዘይት አምራቾቹ የኦፔክ መንግሥታት አቅጣጫ በተዘዋዋሪም ቢሆን ብርቱ ማስጠንቀቂያ ነው የሰነዘሩት። ከታላላቁ ተጠቃሚዎች የአንዱ ኤኮኖሚ ሲጎዳ ሽያጫቸው አነስተና እንደሚሆን፤ ማለት ውጤቱ ያነሰ ዘይትና ጋዝ መሸጥ እንደሆነ ይረዳሉ ብዬ ተሥፋ አደርጋለሁ ብለዋል።


የቡሽ ማስጠንቀቂያ አሜሪካ ወደ ሌላ አካባቢ በተጨባጭ ወደ አፍሪቃ ታዘነብላለች የማለትን ያህል የሚመስል ነው። እስከ ጥቂት ዓመታት በፊት ድረስ በዋሺንግተን የውጭ ፖሊሲ መስፈርት የአፍሪቃ ሚና እጅግ ዝቅተኛ ወይም የተወሰነ ነበር። አሁን ግን ክፍለ-ዓለሚቱ በተለይም የተፈጥሮ ሃብቷ ብዙዎችን እየሳበ ነው። በአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር የቀድሞይቱ የአፍሪቃ ጉዳይ ተጠሪ የፖለቲካ ሣይንስ ምሁር የሆኑት ናንሢይ ዎከር “አሜሪካ በአፍሪቃ ስልታዊ ፖሊሲ ለማራመዷ አንዱ ምክንያት ነዳጅ ዘይት መሆኑ አያጠራጥርም። ብሄራዊ የጸጥታ ፖሊሲዋን ለተመለከተ ስለ ኤነርጂ ደህንነት ወይም ዋስትና ነው የሚወራው። በአጠቃላይ አሜሪካውያን በመላው ዓለም በየትኛውም ቦታ ነዳጅ ዘይት የማግኘት ፍላጎት አላቸው” ባይ ናቸው።

አሜሪካ የኤነርጂ ፍላጎትን ለማርካት በያዘችው ስልታዊ የጸጥታ መርህ አፍሪቃን ማተኮሪያ ካደረገች ሰንበት ብላለች። አፍሪቃ በአሜሪካ ስሌት የተለየ ስፍራ የተሰጣት ገና በ 2002 ዓ.ም. ነበር። ከዚያ ጥቂት ቀደም ሲልም ምዕራባዊው አፍሪቃ በአሜሪካ ብሄራዊ የኤነርጂ ፖሊሲ በተለየ ፍጥነት የሚያድገው የነዳጅ ዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ አካባቢ ተብሎ መመደቡ አይዘነጋም። ይህም ያልክንያት አልነበረም።
አካባቢው በእርግጥም በአፍሪቃ ታላቋ ነዳጅ ዘይት አምራች አገር ናይጄሪያ የምትገኝበት ነው። ከዚሁ ሌላ በጊኒ ባሕረ-ሰላጤ በሣኦ-ቶሜና ፕሪንሢፔ ደሴቶች፣ በማሊና በሞሪታኒያ ወዘተ ባለፉት ዓመታት የነዳጅ ዘይትና የጋዝ ምንጮች ተገኝተዋል። ከዚህ ባሻገርም በምዕራብ ሣሃራ አካባቢ ግዙፍ የጋዝና የነዳጅ ዘይት ምንጮች መኖራችውን አዋቂዎች ይገምታሉ። እንግዲህ አካባቢው የተለየ ትኩረት መሳቡ ብዙም አያስደንቅም። እርግጥ ሁኔታውን ለመቆጣጠርምጥረት ሲደረግ ነው የቆየው።

አሜሪካ ከስድሥት ዓመታት በፊት በአፍሪቃ ዋና የሆነውን ወታደራዊ ሰፈሯን በጅቡቲ ከፍታለች። ከዚያ በመሆን ከዓለም የነዳጅ ዘይት ምርት ሩቡ የሚያልፍበትን የባሕር መንገድ ትቆጣጠራለች። ከዚህ በተረፈ ጂቡቲ ለሱዳን እጅግ ጠቃሚ ለሆነው የነዳጅ ዘይት ማመላለሻ ቧምቧ ቀረብ ያለች መሆኗ ተጨማሪ ስልታዊነት አለው። የአፍሪቃ የተፈጥሮ ጸጋ በአሜሪካ ዘንድ ያለው ትርጉም እንግዲህ ከፍተኛ ነው። በዚህ በጀርመን በካስል ዩኒቨርሲቱ የዓለምአቀፍ ግንኙነትና የውጭ ፖሊሲ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ቬርነር ሩፍ እንዲህ ይላሉ።

“የዓለምን የነዳጅ ዘይት ተቀማጭ በመጠቀሙ ረገድ ከፍተኛው ደረጃ ላይ ተደርሷል ወይም ወሰን ታልፏል ለማለት ይቻላል። በዚሁ የተነሣም ለዘይት የሚደረገው ትግል እየጠነከረ ነው። አሜሪካ 13 ከመቶ የሚሆን የወቅቱን ፍጆቷን፤ ይህ ራሱ ግዙፍ ነው፤ ከአፍሪቃ ነዳጅ ዘይት በማስገባት እስከ 2013፤ ማለት በስድሥትና በሰባት ዓመታት ውስጥ ወደ 25 በመቶ ከፍ ለማድረግ ታቅዳለች። የታቀደው ከተሣካ አፍሪቃ ከታላላቁ አቅራቢዎች አንዷ ትሆናለች ማለት ነው”

የአፍሪቃ አጠቃላይ የነዳጅ ዘይት ሃብት ከአንድ መቶ ሚሊያርድ በርሚል በላይ እንደሚሆን ነው የሚገመተው። ከኢራቅ የሚነጻጸር ነው። ታዳያ ግዙፉ ሃብት አፍሪቃ ሃያላኑን መንግሥታት እንድትማርክ ማድረጉ አልቀረም። ቻይና ባለፉት ዓመታት ከብዙሃኑ የአፍሪቃ አገሮች ጋር የኤኮኖሚ ግንኙነቷን ማስፋፋቷ ለዚሁ ጥሩ ምላሌ ነው። አሜሪካ በበኩሏ ከሰባኛዎቹ ዓመታት የአረብ መንግሥታት የነዳጅ ማዕቀብ ወዲህ የተለያዩ አቅራቢዎችን ለማግኘት ስትጥር ነው የኖረችው።

ለአሜሪካ በአፍሪቃ ላይ ማተኮር የክፍለ-ዓለሚቱ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥም ጠቃሚ ሚና አለው። ከአሜሪካ የሚያገናኘው ቀጥተኛ የባሕር መንገድ የአቅርቦቱን ዋስትና ከፍ የሚያደርግ ነው። የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ከአንድ ዓመት በፊት የራሱን የአፍሪቃ ኮማንዶ መፍጠሩም ይታወቃል። እርግጥ የዚሁ በአሕጽሮት አፍሪኮም በመባል የሚታወቀው ዋና መምሪያ መቀመጫ አፍሪቃ ውስጥ ገና እየተፈለገ ሲሆን በወቅቱ በዚህ በጀርመን ሽቱትጋርት ውስጥ ሰፍሮ ነው የሚገኘው። በይፋ የአፍሪኮም ዓላማ ወይም ግብ በጸጥታው ዘርፍ የአሜሪካንና የአፍሪቃን መንግሥታትን ትብብር ማራማድ የሚል ነው። ይሁንና ፕሮፌሰር ቬርነር ሩፍ ለየት አድርገው ይመለከቱታል።

“አሜሪካውያን በወታደራዊ ሕልውና የተፈጥሮ ሃብት ፍላጎታችውን ለማረጋገጥ እንደሚችሉ የሚያምኑ ይመስለኛል። ግን ነገሩ በሁለት ጎኑ የሳለ ቢላን መሰል ነው። ለምን ቢባል የአሜሪካ ወታደራዊ ሕልውና በነዚህ ሃገራት ተቃውሞን ወይም ዓመጽን ሊያስከትል ይችላል። እንግዲህ በአፍሪኮም ፕሮግራም ውስጥ ጎልቶ እንደተቀመጠው ሽብርን በመታገል ሽፋን የሚደረገው ጥረት ተቃራኒውን ውጤት ነው የሚያስከትለው። የአሜሪካ ሰፊ ወታደራዊ ክምችት እንዲያውም ሽብርተኞች እንዲያቆጠቁጡ የሚያደርግ ነው”

ለነገሩ እስካሁን ከላይቤሪያ ፕሬዚደንት ከኤለን-ጆንሰን-ሰርሊፍ በስተቀር አሜሪካ ዋና የጦር መምሪያዋን በአገሩ እንድትከፍት የጋበዘ ሌላ የአፍሪቃ መንግሥት መሪ የለም። አልጄሪያ፣ ሞሮኮና ሊቢያ ከግማሽ ዓመት ገደማ በፊት የአፍሪኮምን ጥያቄ ሲቃወሙ 14 ሃገራትን የጠቀለለው የደቡባዊው አፍሪቃ መንግሥታት የልማት ማሕበርም ግልጽና ተመሳሳይ አቋም ነው የወሰደው። የአሜሪካን የጦር መምሪያ በአፍሪቃ መተከል በወቅቱ እንግዲህ የሚፈቅድ የለም ማለት ነው።

ተዛማጅ ዘገባዎች