1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፍሪቃ ሕገወጡ የአካል ክፍሎች ንግድ

ቅዳሜ፣ መስከረም 11 2017

ሕገወጥ የአካል ክፍሎች ንግድ በመላው አፍሪቃ እያደገ ነው። የተራቀቀው ቀዶ ጥገና በዓመት ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያስወጣ ሲሆን ያነጣጠረው ደግሞ አቅመ ደካሞች ላይ ነው። ንግዱን ያነሳሱት የቁጥጥር አለመኖርና ለአካል ክፍሎች ያለው ከፍተኛ ፍላጎት ናቸው።

https://p.dw.com/p/4kv0F
ስደተኞች
የአካል ክፍላቸው ከሚወሰደው መካከል ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋለጡ ሕገወጥ ስደተኞች ይገኙበታል ፎቶ ከማኅደርምስል DW/S. Derks

በአፍሪቃ ሕገወጡ የአካል ክፍሎች ንግድ

እየተባባሰ የመጣው የአካል ክፍሎች ንግድ

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሰው የአካል ክፍሎች ንግድ አሁን «ወረርሽኝ ደረጃ ላይ ደርሷል» ሆኖም ግን ሕዝቡ ስለዚህ ጉዳይ ከመናገር ዝምታን መርጧል ይላሉ ናይጀሪያዊው የሰብአዊ መብቶች የሕግ ባለሙያ ፍራንክ ቲዬቴ። ቲዬቲ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት ኅብረተሰቡ ድርጊቱን በይፋ ያወግዛል ተብሎ ቢጠበቅም አልሆነም።

«ከወረርሽኝ ደረጃ ደርሷል ሆኖም ግን በብዛት ሕዝቡ ስለጉዳዩ አይናገርም። ሕዝቡ በጣም በከፍተኛ ደረጃ ያወግዘዋል ብለህ ልትጠብቅ ትችላለህ። ነገሩ ግን እንደዛ አይደለም።»

መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው ግሎባል ፋይናንሺያል ኢንተግሪቲ የተሰኘው ተቋም ይፋ ያደረገው በሙስና፣ በሕገወጥ ንግድ እና በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ ያተኮረ ዘገባ ከ840 ሚሊዮን ዶላር እስከ 1.7 ቢሊዮን ዶላር በዓመት የሰዎችን የአካል ክፍልበማስወገዱ ሕገወጥ ንግድ እንደሚገኝ ገምቷል።

የሰውነት አካልን መገሥና ንቅለ ተከላ የአካል ክፍል ብልሽት ያጋጠማቸውን የታማሚዎች በሕይወት ለማቆየት ጠቃሚ የሆኑ በደንብ ላይ የተመሠረቱ የህክምና ልምዶች ናቸው። ሂደቶቹም በግልፅነትና በፈቃደኝነት ሲካሄዱ በጣም ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ስጋቶች አሉ። ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜም የአካል ክፍል ልገሳ በድህነት ምክንያት ሊፈጸም እንደሚችል ነው ፍራክ ቲዬቲ የሚናገሩት።

«ሰዎች ምናልባት የአካል ክፍላቸውን እየሸጡ ነው፤ ወይም ደግሞ አንዳንድ የህክምና ባለሙያዎች በተለይም ዶክተሮች፤ ጨዋነት በጎደለው መንገድ፤ ብዙውን ጊዜ የታካሚዎቻቸውን የአካል ክፍል እነሱ ሳያውቁ ይጎዳሉ።»

ኩላሊቴ ስንት ያወጣል?

በመላው አፍሪቃ የአካል ክፍል ንግድ ሕገወጥ ነው። ሆኖም ግን በጎርጎሪዮሳዊው 2022 ዓ,ም ናይሮቢ ውስጥ የሚገኘው ኬንያታ ሆስፒታል በፌስቡክ ገጹ፤ «ኩላሊቶችን አንገዛም!» የሚል ማስታወቂያ ታውጥቷል። የኬንያው የህክምና ተቋም ይህን ለማለት የተገደደው በውስጥ መስመር «ለኩላሊቴ ስንት ይከፈለኛል?» የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች ስለደረሱት እንደሆነም ተነግሯል።

በጸጥታ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዊልያም ኦኩሙ እንደሚሉት መደበኛ ያልሆኑት ንቅለ ተከላዎች ሁሉ በግዳጅ የተከናወኑ ላይሆኑ ይችላሉ። ምዕራባዊ ኬንያ ውስጥ በምትገኘው ኤልዶርት ስለሚከናወነው የአካል ክፍል ንግድ ምርመራ ባካሄዱበት አጋጣሚ በአፋጣኝ ገንዘብ ለማግኘት ኩላሊታቸውን ለመሸጥ ፈቃደኛ የሆኑ ወጣት ወንዶችን አግኝተዋል።

«እነሱ በትክክል አልተገደዱም ወይም በማንኛውም መንገድ የግድ አልተባሉም። ሆኖም ገንዘብ ለማግኘት ከመፈለጋቸው የተነሳ፤ ባስቸኳይ ገንዘብ ለማግኘት ይፈልጉ ነበር፤ ወይም ደግሞ እስከ ስድስት ሺህ ዶላር ድረስ ማለትም 700 ሺህ የኬንያ ሽልንግ የሚያስገኝ፤ ገበያ በመኖሩ ምክንያትም ሊሆን ይችላል።»

የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሂደት
በጀርመን የኖርድ ራይን ቬስትፋለን በሚገኝ አንድ ሀኪም ቤት የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ሂደት ፎቶ ከማኅደርምስል Ute Grabowsky/photothek/picture alliance

ኦኩሙ የአካል ክፍላቸውን ለግሰው ሆዳቸው ላይ ትልቅ ጠባሳ ያለባቸው በርካታ ወጣት ወንዶችን ተመልክተዋል። እንዲያም ሆኖ እንደገለጹት ከጋሾቹ ያንን ያህል ገንዘብ የተቀበሉት እምብዛም ናቸው።

«የአካል ክፍላቸውን ለማውጣት ቀዶ ህክምና የተደረገላቸውና ሆዳቸው አካባቢ ጠባሳ ያለባቸው በርካታ ወጣት ወንዶች አይቻለሁ። እንደውም አብዛኞቹ ሲመለሱ ፤ እነሱ መዋዕለ ንዋይ ይሉታል፤ ሞተር ባይስክል ይገዛሉ፤ ወይም አዲስ ቤት ይገነባል ወይም ደግሞ የሆነ ነገር ያደርጋሉ።»

እናም እነዚህ የአካል ክፍላቸውን የሰጡ ወጣቶች ሌሎችም ኩላሊታቸውን እንዲሸጡ ያነሳሳሉ። በዚህም ከኬንያ ውጪ የሚካሄደውን እያደገ የመጣ ሕገወጥ የአካል ክፍል ንግድ ይመግባሉ። ለባለሥልጣናት ሕጉን ለማስከበር አስቸጋሪ ስለነበር የመከሰስ ፍርሃት እንደሌለም አስተውለዋል።

የአካል ክፍል ንግድ እድገት

ምንም እንኳን ስለስውሩ የሰው የአካል ክፍል ሕገወጥ የንግድ ዓለም ዝርዝር ግልፅ መረጃ ባይኖርም፤ ግብፅ፣ ሊቢያ፣ ደቡብ አፍሪቃ፣ ኬንያ እና ናይጀሪያ በዚህ ድርጊት ክፉና የተጠቁ የአፍሪቃ ሃገራት እንደሆኑ ይታመናል።

ለዚህም ምክንያቶቹ ደግሞ ውስብስብ ናቸው፤ ሆኖም የንቅለ ተከላዎች እና የአባል ክፍል ልገሳ ደንብ ከቦታ ቦታ ይለያያል። የተመድ የመድኃኒት እና ወንጀል ጽሕፈት ቤት የሰዎችን አካል ክፍል ስለማውጣትና ሕገወጥ ንግድ፤ የንቅለ ተከላ ቱሪዝም በመባል ስለሚታወቀው ድርጊት ስጋቱን አሰምቷል። እንደ መንግሥታቱ ድርጅት ጽሕፈት ቤት በሕገወጥ ንቅለ ተከላ የሚከናወንባቸው የአካል ክፍሎች ለአደጋ ተጋላጭ ከሆኑ ሕዝቦች ወደ ሀብታም ተቀባዮች የተወሰዱ መሆናቸውንም አሳይቷል።

በዓለም ደረጃ የአካል ክፍል ልገሳን እና ንቅለ ተከላ ዘገባ መሠረት፤ በመላው ዓለም ከሚያስፈልጉት ንቅለ ተከላዎች የሚከናወኑት ከ10 በመቶ በታች ሲሆን፤ ይህም አንዳንድ ታካሚዎች በሕገወጥ መንገድ የአካል ክፍሎችን ለማግኘት እንዲሞክሩ አድርጓቸዋል።

አፍሪቃ ውስጥ ሕጋዊ ንቅለ ተከላ የሚያከናውኑ የህክምና ማዕከላት ቁጥራቸው ትንሽ ነው። ለምሳሌ የዓለም የጤና ድርጅት በጎርጎሪዮሳዊው 2020 በመላው አፍሪቃ 35 የኩላሊት ንቅለ ተከላ የሚያከናውኑ ማዕከላትን መኖራቸውን መዝግቧል። 

 

Organhandel International Dossierbild 2
ፓኪስታን ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ከሚባሉ ወገኖች ኩላሊታቸውን ለ1,400 ዩሮ የሸጡ ሰዎች በከፊል ፎቶ ከማኅደር ምስል picture-alliance/dpa

የተራቀቀ ቀዶ ጥገና

ንግዱ ሕገወጥ እና ትርፋማ ነው ማለት የአካል ክፍሎችን የሚያዘዋውሩት መረቦች በጣም የተደራጁ ናቸው ማለት ነው። ውስብስብ ቀዶ ጥገናዎችን ለማካሄድ የሚያስችል ሙያዊ ብቃት ያስፈልጋል፤ ከዓለም አቀፍ የሕግ አስፈጻሚ ተቋማት እይታ ተሰውሮ፤ ለጋሹም ሆነ ተቀባዩ፤ ገዢና ሻጩን ማገናኘት ማለት፣ የአካል ክፍል ሕገወጥ ነጋዴዎች የህክምናውን ዘርፍ፤ የየአካባቢውን የወንጀል ቡድኖች አልፎ ተርፎም ፖለቲከኞችን ሁሉ ያካተተ ነው።

ዊልያም ኦኩሙ ምዕራብ ኬንያ ውስጥ የተመለከቱት የአካል ክፍል ሽያጭ የዓለም አቀፉ ሕገወጥ ንግድ ተዋናዮች ማኅበር አካል ነው ብለው ያምናሉ። ጉዳዩን ለመመርመር በተንቀሳቀሱባቸው አጋጣሚዎች ካገኟቸው ወጣቶች አንዳንዶቹ ያጋጠሟቸው ዶክተሮች ኪስዋሂሊ ተናጋሪዎች እንዳልሆኑ ነግረዋቸዋል።

«ማን እንዳወጣ ወይም ማን በቀዶ ጥገና ኩላሊታቸውን እንዳወጣ ስንጠይቃቸው፤ ኪስዋሂሊ ስለማይናገሩ ዶክተሮች ተናግረዋል፤ የመጡት ከሕንድ ነው። እናም ብዙዎች ስለሆስፒታል ያነሱትንም ታስታውሳለህ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ጊዜ ንብረትነቱ የሕንድ ፖለቲከኛ የሆነ ኬንያ ውስጥ ተንሰራፍቶ እንደሚገኝ ተወርቷል።»

ከዚህ በመነሳትም ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ገጽታ እንዳለው ለመደምደም እንደሚያስችልም ይገልጻሉ። ባለፈው ዓመት አንድ የለንድን ፍርድ ቤት በአንድ የናይጀሪያ የምክር ቤት አባል እና በባለቤታቸው እንዲሁም በአንድ ዶክተር ላይ ሌጎስ ውስጥ አንድ ወጣት ወንድ ልጅን ኩላሊቱን እንዲሰጥ በማግባባት ክስ ጥፋተኛ ብሏቸዋል። ብይኑ በብሪታንያ የዘመናዊ ባርነት ሕግ የአካል ክፍልን የመሰብሰብ ሙከራ ላይ የተወሰነ የመጀመሪያ ውሳኔ ነው።

ናይጀሪያዊው የሰብአዊ መብቶች የሕግ ባለሙያ እንደሚሉት፤ ከአካል ክፍል ሽያጭ ገንዘብ የማጋበሱ እቅድ ናይጀሪያ ውስጥ የልጆች ፋብሪካ በመባል የሚታወቀውን አካባቢ የሕገወጥ የአካል ንግድ ኢላማ ሊያደርገው ይችላል የሚል ፍርሃት አስከትሏል። በዚህ ምክንያትም የአካባቢው የህክምና ማዕከላት ለችግር የተጋለጡ ሰዎች በዚህ የሕገወጥ ንግድ መረብ እንዳይጠመዱ የመከላከል ሀላፊነት እንዳለባቸውም ያሳስባሉ።  

ሸዋዬ ለገሠ