በአፋር ክልል የመሬት መንቀጥቀጥ የከርሰ-ምድር ዉሃ አፍልቋል
ሐሙስ፣ መስከረም 30 2017ሰሞነኛው የአፋር ምድር ርዕደ መሬት የቀይ ባህር መምጫ ምልክት ይሆን?
በአፋር ክልል ከሰሞኑ በተደጋጋሚ የተከሰተው የመሬት መንቀትቀት ተከትሎ በአከባቢው ፍልውሃ መፍለቅ መጀመሩን የአከባቢው ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ገለጹ፡፡
እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ በአከባቢው የሚወጣው ፍልውሃ አሁንም እየተስፋፋ ይገኛል፡፡
እሁድ በተከሰተውና እስከ ማዕከላዊ የአገሪቱ አከባቢዎች 380 ኪ.ሜ. ድረስ ርቆ ከተሰማው ርዕደ መሬት በኋላም አነስተኛ ንዝረቶች በአከባቢው ቀጥለው መሰማታቸውን ነዋሪዎቹ አስረድተዋል፡፡
እንደ ባለሙያዎች አስተያየት ይህ ሰሞነኛው ክስተት የኤደን ባህረስላጤና ቀይባህልን ከአፍር ምድር ጋር የመገናኘት ዝግመተለውጥ አካል ነው፡፡
በዱለቻ ወረዳ የፍልውሃ መፍለቅ
በአፋር ክልል ክልሉን ከኦሮሚያ ክልል ጋር በሚያዋስነው ፌንታሌ ተራራ አከባቢ እሁድ ረጅም ርቀት ድረስ ሄዶ ከፍተኛ ንዝረት ባስከተለው 4.9 ሬክተር ስኬል የመሬት መንቀጥቀጥ ፣መፈጠርን ተከትሎ በክልሉ ዞን 03 ዱለቻ ወረዳ እና አዋሽ ፈንታሌ ወረዳዎች ውስጥ ከተፈጠሩ የመሬት መሰነጣጠቅ ፍልውሃ እየፈለቀ መሆኑን ነው የአከባቢው ነዋሪዎች የሚገልጹት፡፡ ከሰኞ ሌሊት ጀምሮ መፍለቅ የጀመረው ፍል ውሃ “መጠኑ እየጨመረ” እንዳለም ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የአከባቢው ነዋሪዎች የታዘቡት።
በኢትዮጵያ የሰሞኑ የመሬት መንቀጥቀጥ እንዴት ተከሰተ?
ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ እያስተናገደ ባለው የአፋር ክልል ዞን ሶስት ዱለቻ ወረዳ ሳንጋቶ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አስተያየት ሰጪ የሚፈልቀው ውሃ ከፍተኛ ሙቀት ብኖረውም ለሰውነት መታጠቢያ ግን የሚሆን ነው። “ሰኞ ምሽት ሶስት ሰዓት ግድም የመሬት መንቀጥቀት ስሜት ተደጋግሞ ሶስቴ ከተሰማ በኋላ ከፍተኛ ድምጽ ንጋት አከባቢ መሰማቱን ተከትሎ ሳጋንቶ ቀበሌ ውስት ፍልውሃ ወጥቷል” ያሉት እኚህ አስተያየት ሰጪው፤ የወጣውን ፍልውሃ ሰዎች እየታጠቡበት ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ወረዳ ዶፋን ከሚባል ተራራ ስር ወጥቷል የተባለው ፍልውሃ በቀጫጭን የመሬት ስንጥቆች ውስጥ እንደሚወጡም የገለጹት አስተያየት ሰጪው ርዕደ መሬቱ በአከባቢው በየጊዜው ተደጋግሞ እየተስተዋለ ነው ብለዋል፡፡
የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ተጨማሪ ክስተት
ሌላውም የአከባቢው ነዋሪ አስተያየት ሰጪ ሃሳባቸውን ስቀጥሉ፤ “መንቀጥቀጡ በተደጋጋሚ የምንሰማው ስለሆነ እየለመድነው መጥተናል” ብለዋል፡፡ አሁን ላይ እየተፍለቀለቀ ያለው ፍልውሃ አነስተኛ ሃይቅ የሚፈጥር ይመስላልም ነው ያሉት፡፡
በርዕደ መሬቱ ፍልውሃ የወጣበት ዱለቻ ወረዳ ሳንጋቶ ቀበሌ ከዋናው አስፓልት ወደ ውስጥ ገብቶ አፋር. አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎችን የሚያዋስን አከባቢ ላይ እንደሚገኝም አስተያየት ሰጪዎቹ አስረድተዋል፡፡
ከአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ሳቡሬ ቀበሌ አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው አስተያየት ሰጪም ሰሞነኛው የመሬት መንቀትቀጥ የፈጠረው የመሬት መሰንጠቅ ውሃ ማፍለቅ ጀምሯል፡፡ “ጉሩሙሊ በሚትባል መንደር የመሬት መሰንጠቁ እና ውሃ ማፍለቁ በደንብ የታየበት ነው” ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ ከአከባቢው አርብቶ አደሮችን የማንሳት ስራ መሰራቱንም ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ሃገራት የሚታየው የተፈጥሮ አደጋ የብዙዎች ስጋት ሆኗል።
የመሬት መንቀጥቀጡን ተከትሎ በአከባቢው የደነበሩ የአርብቶ አደር ከብቶች ጠፍቶ ወዴት እንደደረሱ እስካለመታወቅ የደረሱ አደጋዎች መስተዋላቸውንም አክለው ነግረውናል፡፡
በክስተቱ ቀጣይነት ላይ የባለሙያ አስተያየት
አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ በአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ የስነምድር ባለሙያው ፕሮፌሰር ገዛኸኝ ይርጋ ሰሞነኛው የመሬት መንቀትቀጥን ተከትሎ ከስምጥ ሸሎቆው የሚፈልቅ ውሃ ተጠባቂ የነበረ ነው ባይ ናቸው፡፡ “መሬት ስንቀጠቀጥ መሰንጠቅ ስለሚፈትር ውሃ በዚያው ነው የሚወጣውና ተጠባቂ ነበር” ብለዋልም፡፡
ፕሮፌሰር ገዛኸኝ ክስተቱ ቀጣይነት ያለውና የቀይባህርና ኤዴን ባህረሰላጤን ኢትዮጵያን ከሚያቋርጠው ስምጥ ሸለቆ ጋር በሂደት የሚያገናኝ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ “በዝግመተ ለውጥ አሁን መሬት እየተሰነጠቀ፤ መንቀጥቀጡም እየቀጠለ ውሃ በትንሽ በትንሹ እየሰፋ ቀይባህርን ከአፋር ጋር በማገናኘት በመታሃራ ዝዋና ሃዋሳ አርባምንች ጋር የሚገናኝ ሃይቅ የመፈጠሩ ምልክት ነው” ሲሉም እያደር ሊፈጠር የሚችለውን የተመራማሪዎች ግምት አስቀምጠዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ