በአጣዬ እና አካባቢዉ ተባብሶ የቀጠለዉ ጥቃት | ኢትዮጵያ | DW | 19.04.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በአጣዬ እና አካባቢዉ ተባብሶ የቀጠለዉ ጥቃት

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ በአጣዬ ከተማ እና አካባቢው ካለፈው ዓርብ ጀምሮ ታጣቂዎች በሰነዘሩት ጥቃት እስከ 35 የሚደርሱ ሰዎች ሳይገደሉ እናዳልቀረ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ። የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር በበኩሉ በጥቃቱ በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት እየተጣራ ነው ብሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:28

ማብቂያ ያጣው የአጣዬ እና የአካባቢው ጥቃት

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ በአጣዬ ከተማ እና አካባቢው ካለፈው ዓርብ ጀምሮ ታጣቂዎች በሰነዘሩት ጥቃት እስከ 35 የሚደርሱ ሰዎች ሳይገደሉ እናዳልቀረ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ። የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር በበኩሉ በጥቃቱ በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት እየተጣራ ነው ብሏል። ጥቃቱን በመሸሽ እስከ 15,000 የሚደርሱ ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን ዞኑ አስታውቋል።
ባለፈው ሐሙስ ሌሊት ለአርብ አጥቢያ ጀጀባ በተሰኘች አንዲት ቀበሌ በአነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ በተፈጸመ የታጣቂዎች ጥቃት 1 ሰው ተገድሎ በሌሎች ላይ ደግሞ የመቁሰል አደጋ ከደረሰ በኋላ ጥቃቱ በሌሎች አካባቢዎች መስፋፋቱን የአካባቢው ነዋሪ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

«ሐሙስ ለዓርብ አጥቢያ ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ የሚሄዱ ባልቲ ከምትባል አነስተኛ ቀበሌ አራት አይሩፎች ተከታትለው ሲሄዱ በአንደናው ላይ ጥቃት አድርሰው 1 ሰው ሞቶ ሌሎች ቁስለኞች ነበሩ ያናን ተከትሎ ነው ሁለቱም አካል ወደ ተኩስ የገቡት። »

በአካባቢው ግጭት ሊቀሰቀስ እንደሚችል አስቀድሞ መረጃ ደርሶን ነበር የሚሉት ሌላው የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪ ደግሞ መረጃውን ቢያገኙም መሄጃ በማጣታቸው ጥቃቱ ገፍቶ መጥቶብናል ሲሉ ተናግረዋል።

«ግጭቱ የተነሳበት ምክንያት ምንድነው እና መረጃ ሲደርሰን እንዲህ አይነት ረብሻ ያነሳሉ ፤ የተቀናጀ ኃይል አለ ፤ እርዳታ እየመጣላቸው ነው ። የኦነግ ሸኔ የሚባል ቡድን እነርሱ ጋር እየተከማቹ ነው ። ሸዋ ሮቢት ላይ ኃይለኛ ውጊያ አለ። እናቃጥላለን የሚል መረጃ ደረሰን ። እኛ ግን የትም መሄጃ ስለሌለን ዝም ብለን የተመለከትነው ። ኋላ ላይ ነገሩ ሲብስ አርብ ዕለት ተኩሱን ልነግርህ አልችልም።»

በአማራ ልዩ ኃይል እና በታጣቂዎቹ መካከል የሚደረገው ውግያ መባባሱን ተከትሎ በርካቶች ወደ ተራራማ አካባቢዎች እና ወደ መሐል ሜዳ አካባቢ መሸሻቸውን እነዚሁ ነዋሪዎች ተናግረዋል። በአካባቢው ሶስት ቀናትን በወሰደው እና በርካታ አካባቢዎችን እንዳዳረሰ በተነገረለት በዚሁ ግጭት የአማራ ልዩ ኃይል አባላታን ጨምሮ እስከ 35 ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ እነዚሁ የአይን ምስክሮች ተናግረዋል።

«አሁን እዚህ እኛ እዚህ በትናንትናው ዕለት በሙስሊም ቀብር 6 አስክሬን በኦርቶዶክስ ደግሞ 4 አካባቢ በሸዋ ሮቢት ብቻ ማለት ነው የተቀበረው። ራሳ አካባቢ ደግሞ ይክንኑ ያህላል ። በአጠቃላይ እስከ ልዩ ኃይሉ ከ29/35 ሰው እንደሞተ መረጃ አለኝ።»

ሌላው የአይን እማኝም ይህንኑ ባረጋገጡበት አስተያየታቸው በጥቃቱ በርካቶች መገደላቸውን ይናገራሉ።

«ሰዎች ሞተዋል። ለምሳሌ ወደ ራሳ ልጆች ወጣቶች ነበሩ ለእርዳታ እየመጡ እያለ ከ10 ወጣቶች በላይ ነው የተገደሉት ። እና ሌሎችም ግለሰቦች እንዲሁ ተገድለዋል። ቢያንስ እዚህ ሸዋ ሮቢት ከተማ ላይ ብቻ ከ20 ያላነሱ ተገድለዋል።»

ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ አስተዳደር ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች ተከስቶ የነበረው ግጭት በቅጡ  በቁጥጥር ስር ሳይውል ሁኔታውን የሚያባብስ ክስተት ተፈጥሯል ያሉት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረጻዲቅ ናቸው። እንደ እርሳቸው ለግጭቱ መባባስ አስተዋፅዖ ያደረገው በአካባቢው ለተፈጠረው ችግር የሚመጥን የጸጥታ ኃይል አለመሰማራቱ ነው።

«ያው እንግዲህ በአካባቢው ባለው የጸጥታ መዋቅር መቆጣጠር አልተቻለም። አንደገና የኃይል ማነስ ነበር ። ግችቶቹ በርከት ያሉ አካባቢዎች ነበሩ። ይሄን ለመቆጣጠር እና ለማስቆም የኃይል ማነስ ነበር ሁለተኛ የገባውም ተቆራርጦ እርምጃ ለመውሰድ ጉድለቶች ነበሩ። በእነዚሁ ምክንያቶች ግጭቱ ተባብሷል።»

በአካባቢው ለግጭቶች በተደጋጋሚ መከሰት እና መባባስ በአካባቢው ይንቀሳቀሳል ያሉትን «ኦነግ ሸኔ» የተባለ የታጠቀ ኃይል ተጠያቂ እንደሚሆን አቶ ታደሰ ገልጸዋል።

«በዚህ ዓመት ብቻ አይደለም ይህ ችግር የተከሰተው ። ከ2011 ጀምሮ በተከታታይ በየዓመቱ ግጭቶች ነበሩ። አካባቢው ላይ ደግሞ አልፎ ኣልፎ በብሔረሰብ ዞኑ መዋቅር ውስጥ ከራሳቸው መደበኛ የጸጥታ አካል ጋር ግጭት የሚያደርጉ የኦነግ ሸኔ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ በጋራ ግምገማ አረጋግጠናል።»

በጥቃቱ ከሞቱት እና ከቆሰሉት በተጨማሪ ከአራት እስከ አስራ አምስት ሺ የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ተፈናቅለው መሃል ሜዳ መስፈራቸውን የዞኑ አስተዳዳሪ ነግረውናል።በጉዳዩ ላይ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪውን ጨምሮ  የዞኑ የደህንነት እና የጸጥታ ኃላፊ አስተያየት ለማካተት በ,ተደጋጋሚ ስልክ በመደወል ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

የመከላከያ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣዉ መግለጫ ግጭት ተጠናክሮ በቀጠለባቸው በሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር አካባቢዎች በጸጥታ ዕዝ ወይም ኮማንድ ፖስት እንዲመራ መወሰኑን አስታውቋል።

ታምራት ዲንሳ 

እሸቴ በቀለ

 

 

Audios and videos on the topic