1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአገራዊ ምክክር፤ የወጣቶች ሚና

ረቡዕ፣ ሐምሌ 3 2016

አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በትጥቅ የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች ጋር በማንኛውም ሁኔታ በመነጋገር የሂደቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ኮሚሽኑ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግ አስታወቀ። ኮሚሽነር ፕ/ር መስፍን አርዓያ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ኮሚሽኑ ከታጣቂዎች ሌላ በከተማም ሆነው ወደ ኮሚሽኑ ላልመጡ የፖለቲካ ድርጅቶችም የሚያቀርበው የተሳትፎ ጥሪ እንደ ቀጠለ ነው።

https://p.dw.com/p/4i7IS
አገራዊ የምክክር ኮሚሽን መለያ
አገራዊ የምክክር ኮሚሽን መለያ ምስል Seyoum Getu/DW

በአገራዊ ምክክር፤ የወጣቶች ሚና

ኮሚሽኑ ማክሰኞ ዕለት አዲስ አበባ ውስጥ ከመላው አገሪቱ የተውጣቱ ከተባሉ ወጣቶች ጋር ባደረገው ምክከርም በሂደቱ የወጣቶች ተሳትፎ በተለይም ግጭትን ከመግታት አኳያ ጉልህ ሚና እንዳለው ተነግሯል።  

በምክክር ሂደት የወጣቶች ተሳትፎ ሚና

ፓል ሬክጆክ በጋምቤላ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነው። ማክሰኞ ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባዘጋጀው የወጣቶች የምክክር መድረክ ተሳታፊ ነበር። ፓል ኮሚሽኑ ከመላው አገሪቱ ከተውጣጡ የወጣቶች ተወካዮች ከተባሉት ጋር በመድረኩ ሲታደም የወጣቶች የሰላም ሚና ጉልህ መሆኑን በማመንም ጭምር መሆኑን ያስረዳል። «ወጣቶች የትኛውንም ጉዳይ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ለመጨረስ ከፍተኛ ሚና አለባቸው» የሚለው ፓል በሂደት የሁሉም ጦረኛ ወጣት አመለካከት መቀየር እንደሚቻል ያምናል።

ኢምፓወር ኔክስት ጀነሬሽን ከሚባል ወጣቶች ላይ ከሚሠራ ግብረሰናይ ድርጅት በወጣቶቹ የምክክር መድረክ መሳተፏን የምትገልጸው ሰላም ገብረመድኅን ደግሞ ለግጭት ከፍተኛ ተጋላጭ የሚሆነው ወጣት በአገር ውስጥ የሚደረግ ግጭትን ከመፍታት አንጻር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ታምናለች።  በግጭት ወቅት ትልቁ የግጭት መሳሪያ የሚሆኑት ወጣቶችን በውይይት ሂደት በማሳተፍ ከግጭት ስፍራዎች ማውጣት እንደሚቻልም ትናገራለች።

የወጣቱ አጀንዳ አሰባሰብ

አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በተለያዩ አደረጃጀትም ሆነ በተናጥል ያሉ ከተለያዩ ማኅበረሰብ የተውጣጡ ወጣቶችን ወይም የወጣቱን ወኪል ከመላው አገሪቱ መልምሎ ማወያየት የተፈለገው ሁሉም ወጣቶም ጋ ያሉትን ችግሮች ለይቶ መያዝ እንዲቻል ነው ይላሉ። «ግጭት ሲኖር የመጀመሪያዎቹ ተመልማይና የግጭቱ ገፈት ቀማሾች ወጣቶች ሲሆኑ ትልቁ የግጭቱ ጉዳት ደግሞ የሚያርፈው ሴቶችና ሕጻናት ላይ ነው። ስለዚህ ወጣቶች ወደ ግጭት የሚያስገባቸው አጀንዳ ካላቸው ጥያቄያቸውን በአጀንዳ መልክ ቀርጸው የማምጣት መብት አላቸው። አገራችን በሰላም መምራት ከተፈለገ አጀንዳቸውን ማምጣት አለባቸው። ስለዚህ ዛሬ አንዱ ነገ ሌላው ከሚያሸንፍበት ግጭት ወጥተን ሁሉም አሸናፊ ወደሚሆንበት ውይይት መሸጋገር አለብን» ነው ያሉት።

የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን
አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ወጣቶችን በማንኛውም ሁኔታ በመነጋገር የሂደቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ እንደሚፈልግ አስታውቋል። ፎቶ ከማኅደር ምስል Seyoum Getu/DW

ለታጠቁ ወገኖች የሚቀርብ ተደጋጋሚ ጥሪና ውጤቱ

ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት ወጣቶች በጉልህ ከሚሳተፉበት የትጥቅ ግጭት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቦ ነበር። ዶይቼ ቬለ በጥሪው የተገኘ ውጤት ስለመኖር አለመኖሩም ለዋና ኮሚሽነሩ ጥያቄ አቅርቦላቸው ሲመልሱ፤ «ባገኘነው አጋጣሚ በሙሉ ጥሪ እናቀርባለን። በርግጥ ለዚህ የተለያዩ ትርጓሜዎች ሲሰጥ እናስተውላለን። በእኛም ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ሲነሳ እናያለን። እኛ ግን በዋናነት የምሠራው፤ በዚህ ዕድሜያችን ለመልካም ነገር ለሕሊናችን ነው። መልካም ነገር በአገራችን ታይቶ ማለፍ እንሻለን። ከዚህ በፊት ካለፍንበት ጦርነት ተምረን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ እንምጣ ነው የእኛ ጥያቄያችን» በማለት  አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 ከመንግሥት ጋር በሚያደርጉት ውይይቶች በዚህ ምክንያት የታሰሩም ካሉ እንዲፈቱና ወደ ውይይት እነዲመጡ፣ ትጥቃቸውን ፈተው ጥሪውን ተቀብለው ለተመለሱም ዋስትና እንዲሰጥ እንደሚሠሩም አስረድተዋል። ከጦር ሜዳ ውጪ ከተማም ውስጥ ሆነው የተቀየሙት በጊዜ ሂደት ወደ ምክክር ተሳትፎ እንዲመጡ ጥረቱ ይቀጥላልም ነው ያሉት። ኮሚሽኑ በትጥቅ ከመንግሥት ጋር ከሚዋጉት ወገኖች ጋር በመመካከር ወደ ምክክር መድረኩ ለማምጣት አበክሮ እንደሚሠራም ተናግረዋል።   «በማንኛውም ጊዜ ሄደን ልናነጋግራቸው ዝግጁዎች ነን» ያሉት ኮሚሽነሩ በከተማ ውስጥ ሆነው ወደ ኮሚሽኑ ላልመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሚደረገው ጥሪ መቀጠሉን አስረድተዋል።

ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ