በአዲስ ዓመት፤ አዲስ ግብ አዲስ ተስፋ   | ባህል | DW | 04.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

በአዲስ ዓመት፤ አዲስ ግብ አዲስ ተስፋ  

አዲስ ዓመት፤ አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት፣ በአዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር የዕድሜያችን ቁጥር የሚጨምርበት ብቻ ሳይሆን በኑሮ ላይም አወንታዊ ለዉጥን ለማድረግ እቅድ ይዘን የምንነሳበትም ነዉ። አዝመራዉ እንዲያሸት፣ ዉጥን እንዲሳካ፣ የጠባዉ አዲስ ዓመት ሰላም ጤናን ፍቅርንና መግባባትን ሰንቆ እንዲያልፍ ምኞት የሚገለጽበትም ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:55

በ2018 አዲስ ዓመት፤ ሠላምና ጤና

 

እንኳን ለአዲሱ የአዉሮጳዉያኑ 2018 ዓ.ም አደረሳችሁ። አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት፣ በአዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር የዕድሜያችን ቁጥር የሚጨምርበት ብቻ ሳይሆን በኑሮ ላይም አወንታዊ ለዉጥን ለማድረግ እቅድ ይዘን የምንነሳበትም ነዉ። አዝመራዉ እንዲያሸት፣ ዉጥን እንዲሳካ፣ የጠባዉ አዲስ ዓመት ሰላም ጤናን ፍቅርንና መግባባትን ሰንቆ እንዲያልፍ ምኞት የሚገለጽበትም ነዉ። በምዕራቡ ዓለም ሃገራት የሚገኙ ነዋሪዎች አሮጌዉ ዓመት አልቆ አዲሱ ሊተካ አራትና አምስት ወራት ሲቀሩት በመጭዉ ዓመት የረጅምና የቅርብ ጊዜ እቅዳችን ያሉትን ያስቀምጣሉ። በእለቱ ዝግጅታችን በጀርመን ሀገር ነዋሪ የሆኑና በምዕራቡ ዓለም ለአዲስ ዓመት ዝግጅት የሚደረገዉን እቅድና ዝግጅት ያጫዉቱናል መልካም ቆይታ።

በጣት ቁጥር የማይሞሉ ቀኖች የተቆጠሩለት አዲሱ የጎርጎረሳዊዉን 2018 ዓ.ምን ለመቀበል በዉጭዉ ዓለም የሚኖሩ አብዛኞቹ ኢትዮጵያዉያን አገራችንን ሰላም ያድርግልን ሲሉ ኢትዮጵያን በማዜም በተለያዩ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ ቤቶችና ቡና ቤቶች አልያም ከባልንጀሮቻቸዉ ጋር በየመኖርያ ቤቶቻቸዉ እና አካባቢያቸዉ በመሰባሰብ ዓመቱን በክብር ተቀብለዋል። በዚህ በአዉሮጳ አዲስ ዓመት ሲብት አብዛኛዉ ሰዉ በአዲስ ዓመት በኑሮዉና በሥራዉ አንድ ርምጃ ወደፊት ለመራመድ የሚያቅድበት፤ ሲሰራዉ አልያም ሲያደርገዉ የነበረዉን መጥፎ ወይም የማይሆን ነገር ከአሮጌዉ ዓመት ጋር ወደ ኋላ የሚጥልበትን እቅድ የሚይዝበት ነዉ።

  በጀርመን የአፍሪቃና የመካከለኛዉ ምሥራቅ አማካሪና ታዋቂዉ ደራሲ እንዲሁም በቱቢንገን ዩንቨርስቲ የክብር ሴናተር ዶ/ር ልጅ አስፋዉ ወሰን አስራተ፤ በዉጭ ሃገር ሲኖሩ ከአራት አስርተ ዓመታት በላይ ሆንዋቸዋል። አዉሮጳዉያን አዲስ ዓመትን ሲጀምሩ ወደፊት የሚሰሩትን ሥራ ብቻ ሳይሆን አዲስ ሕይወትንም ለመጀመር እቅድ እደሚይዙ ይናገራሉ። 

« አዉሮጳዉያን ዓመቱ ሲጀመር እቅድ ማዉጣት ብቻ ሳይሆን ። በአዲሱ ዓመት ለራሳቸዉ ምን አይነት ሕይወት መኖርን እንደሚፈልጉ ለራሳቸዉ ቃል ይገባሉ። «New Year's resolution» ይሉታል። ለምሳሌ በአለፈዉ ዓመት ሲጃራ አጨስ ነበር፤ በዚህ በአዲሱ ዓመት ላለማጨስ ቃል ገብቻለሁ። በዓለፈዉ ዓመት በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ባለማድረጌ አምስት ኪሎ ጨምሪአለሁ፤ ይህን ኪሎ ለመቀነስ በቂ የአካል እንቅስቃሴን አደርጋለሁ። አልያም በባልና ሚስት መካከል ያለ ግንኙነትን በተመለከተም ቢሆን ባል አልያም ሚስት ባለፈዉ ዓመት ብዙ ጊዜዬን በዉጭ ሥራ ላይ ስለነበርኩ በአዲሱ ዓመት በርካታ ጊዜዬን ከቤተሰቤ ጋር ለመሆን ቃል እገባለሁ ሲሉ ለራሳቸዉ እቅድ በመያዝ አዲሱን ዓመት ይጀምራሉ። በርግጥ  በሥራም በኩል ቢሆን የሚያዘዉ እቅድ የሚጀመረዉ በአዲስ ዓመት ላይ አይደለም። ይልቁንም ለመጭዉ ዓመት ሥራ እቅድ የሚጀመረዉ አሮጌዉ ዓመት ከማለቁ ስድስት ወር ግድም ሲቀረዉ ጀምሮ ነዉ።»   

ዶ/ር ልጅ አስፋዉ ወሰን እንደሚሉት ከሆነ አዉሮጳዉያን በእቅድ እንዲመሩ ያደረጋቸዉ አንዱ ምክንያት ምናልባትም የአየር ጠባያቸዉ ነዉ።

«እቅድ የሚለዉ ቃል አዉሮጳዉያንን እና አፍሪቃዉያንን ይለያል። ምክንያቱ ደግሞ በሁለቱ አህጉራት መካከል የሚታየዉ የአየር ፀባይ ልዩነት ምክንያት ነዉ። ለምሳሌ በአፍሪቃ ዉስጥ በአንድ ዓመት ዉስጥ ስምንት - ዘጠኝ ወራት ፀሐያማ ሞቃታማ ነዉ። አፍሪቃ ዉስጥ አዉሮጳ  እንደሚታየዉ ዓይነት በበረዶ የተሞላ ቀዝቃዛ የአየር ፀባይ የለም። ስለዚህም አዉሮጳዉያን ከመጀመርያዉ ጊዜ ጀምሮ ለክረምት ወራታቸዉ እቅድ ማዉጣት አለባቸዉ። በክረምት ወራት የሚበሉትን ነገር ቀድመዉ ማዘጋጀት አለባቸዉ። ከ 21 እና ከ20ኛዉ ክፍለዘመን በፊት የማቀዝቀዣ ቤት ባልነበረበት ጊዜ የሚሳፈልጋቸዉን አታክልት ምግቦች በብዙ ዓይነት ሁኔታ አዘጋጅተዉ እና ብርጭቆዎች ዉስጥ በማሸግ የክረም ወራት ማሳለፍያ ምግባቸዉን አስቀድመዉ አዘጋጅተዉ ያስቀምጣሉ። እናም ይህ አይነቱ የእቅድ መረሃ ግብር ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ነበረ ነዉ።  አፍሪቃን ያየን እንደሆነ እቅድ የሚባለዉን ነገር የጀመርነዉ፤ አብዛኞቻችን ከአዉሮጳዉያን ከተማርን በኋላ በ 21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ነዉ።

ከዚያ በፊት ሁሉ ነገር በእጃችን ስለሆነ ይህንን ያህል የእቅድ ሰዎች አልነበርንም። ለዚህ ከአዉሮጳ የአኗኗር ዘይቤ ጋር አብሮ ለመራመድ አስቸጋሪ የሆነበትም ጊዜ አለ። አንዳንድ አፍሪቃዉያን ወደ አዉሮጳ ሲመጡ ለምሳሌ ሰዓት መጠበቅ የሚባለዉን ነገር በጣም ያዳግታቸዋል።     

ወጣት ተስፋልደት ታደሰ በጀርመን ሙንስትር ከተማ በሚገኝ ዩንቨርስቲ በኮምፒዉተር ሞያ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ነዉ። ጎርጎሪዮሳዊውን አዲስ ዓመት ከአገሩ ዉጭ በጀርመን ሃገር ሲቀበል የዘንድሮ 2018  ዓ.ም  የመጀመርያዉ ነዉ።

« የጀርመን ሃገር ነዋሪዎች በጣም በፕሮግራም ይመራሉ። ይህ ሲባል እናሳካለን የተባሉትን እቅዶች መረሃግብር አዉጥተን ይሄን ነገር በዚህ ሰዓት በዚህ ጊዜ እተገብራለሁ ብለን የምናወጣዉ ነዉ። እዚህ ጀርመን አገር በእቅድ አወጣጥ እና በመተግበሩ ረገድ በጣም በጣም ስኬታማ ናቸዉ። በአንፃሩ በእኛ ሃገር በፕሮግራም የመመራት ልማዳችን በጣም ዝቅተኛ ነዉ። ያ ደግሞ በመጨረሻ ያሰብነዉ ያቀድነዉ አላማ ላይ መድረስ አያስችለንም። » 

እቅድን ለፈረንጆች ብቻ የምንሰጠዉ ነገር መሆን የለበትም፤ ቢሆንም በገጠሩ አካባቢ በእቅድ የሚሰሩ ነገሮች እንዳሉም መግለፅ እወዳለሁ ያሉት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የፊሎሎጂ ረዳት ፕሮፊሰርና በአሁኑ ወቅት በጀርመን ሙኒክ ከተማ በሚገኘዉ ሉድቪግ ማክሲሚሊያን ዩንቨርስቲ ዉስጥ በምርምር ላይ የሚገኙት ዶክተር አምሳሉ ተፈራ በበኩላቸዉ፤

«በእኛም ሃገር በኢትዮጵያዉያኑም ባህል ስናይ እንደዉ ሁሉም ሰዉ ትኩረት ሰጥቶ እንዲህ ነዉ ብሎ አጋኖ ባይናገርበት በእቅድ መመራት ፕሮግራም ማዉጣት እንደተባለዉ የአጭር ጊዜ የመካከለኛ ጊዜ የረጅም ጊዜ ብሎ በግል ሕይወቱ በተወሰነ መልኩ በአብዛኛዉ ደግሞ በየሚሰራበት ተቋምና በየመሥርያ ቤቱ ግድ ይሄንን እቅድ ማዉጣትና በእቅድ መመራትን የግድ እንደሆነ እንገነዘባለን። ወደ ሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ ስንመጣ የዓመት ጊዜን መጠቀምን በተመለከተ እንኳ አሁን በዘመናዊ ኑሮ ያለዉ ማኅበረሰብ ይቅርና  በጣም ያልተማረ ነዉ ብለን በምናስበዉ በአርሶ አድር ደረጃ ያለዉ ነዋሪ በእቅድ እንደሚመራ ማየት እንችላለን።

በግብርናዉ ዓለም አርሶ አደሩን ብናይ በክረምት የሚዘራዉን በክረምት የሚጠቀምበትን ቀድሞ ያዘጋጃል። በበጋዉ በፀሐይ ወቅት ማድረግ የሚገባዉን ቀድሞ ያደርጋል፤ የሚዘራዉን ይዘራል፤ የሚያጭደዉን ያጭዳል፤ ከዝያም ከገበያ ወጥቶ ለቤት የሚጠቀምበትን የሚጠቀምበትን ነገር ሁሉ ቀድሞ ማድረጉን ስናይ አገር በቀል የእቅድ ሁኔታን ከመጀመርያ ጀምሮ እናያለን ማለት ይቻላል።»               

በጀርመን ሲኖሩ የኢትዮጵያን ብሔራዊ በዓላትም ሆነ የጀርመናዉያኑን እንደሚያከብሩ የሚናገሩት ዶ/ር ልጅ አስፋዉ ወሰን አስራተ በተለያየ ጊዜያት በጀርመንኛ ስለ ኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር አመጣጥ፤ እንዲሁም ባህል ጽፈዋል። ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።  

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሰ 

 

Audios and videos on the topic