በአዲስ አበባ “የነገሱት” የክፍለሀገር ስጋ ቤቶች | ባህል | DW | 23.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

በአዲስ አበባ “የነገሱት” የክፍለሀገር ስጋ ቤቶች

በኢትዮጵያ ያሉ ስጋ ቤቶች ከሚታወቁበት የልኳንዳ ብቻ አገልግሎት ተላቅቀው እንደ ምግብ ቤት ማገልገል ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ ከዘመኑ ጋር ለመራመድ ጥረት የሚያደርጉ ስጋ ቤቶች ደግሞ ስማቸው ከሚጠራ የመዝናኛ ስፍራዎች መካከል ራሳቸውን ማሰለፍ ችለዋል፡፡ ጥቂቶቹ መሰረታቸውን ከጣሉበት ከተማ ተሻግረው በአዲስ አበባ ቅርንጫፎች እስከ መክፈት ተጉዘዋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:59

የወጣቶችን ቀልብ የገዙት ዘመነኛ ስጋ ቤቶች

በመጀመሪያ ስሙ ብቻ መጠራትን መርጧል፡፡ ዳንኤል ይሰኛል፡፡ ስጋ ወዳጅ ነው፡፡ ምርጥ ስጋ ይገኝበታል የተባለበት ቦታ ከሰማ ከመኖሪያ አካባቢው ርቆም ቢሆን ከመጓዝ ወደ ኋላ አይልም፡፡ እንዳሁኑ ነዋሪነቱን በአዲስ አበባ ከማድረጉ በፊት በባህር ዳር እያለ ጭምር በዚህ ልማዱ ይታወቃል፡፡ ዓመታዊውን የቁልቢ ገብርኤል ክብረ በዓል ለማክበር ከባህርዳር አዲስ አበባን አቋርጦ ወደ ድሬዳዋ ሲያመራም ሆነ ሲመለስ ዱከም ላይ ቆም ብሎ የስጋ አምሮቱን ሲወጣ ቆይቷል፡፡

በትንሽይቱ ዱከም በርካታ ስጋ ቤቶች ቢኖሩም የእርሱ ምርጫ ግን ሁሌም አንድ ነው- ምስራቅ በር ስጋ ቤትና ባር፡፡ ዳንኤል ለስጋ ቤት ካለው ፍቅር የተነሳ ሁነኛ ወዳጆቹን እንኳ የሚጋብዘው ከዚያ ነው፡፡ “ሰውን በቃ ጋበዝኩ የምትለው ጥሬ ስጋ ወስደህ አብልተህ፣ ጮማ ቆርጠህ፣ ጠጅ ጋብዘህ ባለውለታ ነው የምትባለው፡፡ አንተ ያንን ያደረግህ ቀን ‘እንዴ!’ ይባላል እኮ፤ ሁሌ ይነገርልሃል፡፡ ‘አቤት እርሱ የጋበዘን ነው’ የሚባለው” ይላል።  

ዳንኤል “ከምስራቅ በር ስጋ ቤት” ጋር የጀመረው ደንበኝነት አንድ፣ ሁለት እያለ ዛሬ 12ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ በሀገር አስጎብኚነት ዘርፍ የተሰማራው ዳንኤል ጓዙን ጠቅልሎ አዲስ አበባ ላይ ሲከትም በአለፍ ገደም የነበረው የስጋ ቤቱ እና የእርሱ ደንበኝነት መደበኛ መርኃ ግብር ወጥቶለት የሚካሄድ ሆነ፡፡ ታዲያ ብቻውን ሳይሆን ስድስት ጓደኞቹን አስከትሎ ነው፡፡

“በሳምንት አንዴ እሁድ ቀን ሁሉም ሰው የእረፍት ልብስ ይለብሳል፡፡ ቅዳሜ እና አሁድ በለው፤ ሁለቱን ቀን እዚያ ነን፡፡ ሰብሰብ ብለን እዚያ እንሄዳለን፤ ከዚያ ይበላል፡፡ ጥሬው፣ ጥብሱ፣ ደግሞ ቆንጆ ጠጅ አላቸው፡፡ በቃ!  አለ አይደል ይበልጥ ባህሉን፣ ኢትየጵያዊነትን የተላበሰ ነገር ነው፡፡ በቃ! እዚያ ሰብሰብ ብለህ ትሄዳለህ” ሲል ሳምንታዊ ልማዳቸውን ይገልጻል። 

በተለያየ የሙያ ዘርፍ ላይ የተሰማሩት እኒህ ሰባት ጓደኛሞች በአዲስ አበባ እና ደብረዘይት መካከል እንደ አገናኛ ድልድልይ ወደ ሆነችው ዱከም በየሳምንቱ ሲሄዱ ለምግብ እና መጠጥ በሚል ብቻ እንዳልሆነ ዳንኤል ይናገራል፡፡ መዝናናቱ ቀዳሚው ቢሆንም በስጋ ቤቱ መሰባሰባቸው ሌሎች ዓላማዎችን አሉት ይላል፡፡ “ወዳጅነት የሚጠነክረው [በዚያ ነው]፡፡ በሳምንት ሁለቴ እንገናኛለን፡፡ ማህበራዊ ነገር ታወራለህ፡፡ እንትና ታመመ ሊባል ይችላል፣ የእንትና ሚስት ወለደች ሊባል ይችላል፡፡ መወያያዎች ይኖራሉ፡፡ በዚያ ዙሪያ ትነጋገራለህ፡፡ የራሳችን ዕቁብ አለን” ይላል ዳንኤል፡፡  

በዚህ የስጋ አፍቃሪዎች ስብስብ ውስጥ ከነበሩ ሰዎች ሁለቱ ወደ አሜሪካ ቢሄዱም ቀሪዎቹ ጓደኛሞቹ ግን አሁንም አዘወትረው መገናኘታቸውን ቀጥለዋል፡፡ እንደ ድሮው ዱከም ድረስ መሄድ ሳያስፈልጋቸው ጥሩ የሚሉትን ስጋም በከተማቸው አግኝተዋል፡፡ ለዓመታት በደንበኝነት አብረው የዘለቁት ምስራቅ በር ዱከም ስጋ ቤት በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ መክፈቱ የሳምንቱን መጨረሻ ከመጠበቅ ገላግሏቸዋል፡፡ 

“ዱከም ድረስ ሄዶ በልቶ መምጣቱ በጣም አድቬንቸር ነው፡፡ ደስ ይላል፡፡ ግን አሁን ሁሉም ሰው ስራ በዛበት እና ደግሞ አሁን እዚህ መከፈቱ ጥሩ ሆነልን፡፡ አንድ እዚያ ድረስ መሄዱ ቀነሰልን፡፡ ሁለተኛ እዚህ አዲስ አበባ ያለው ጋር ከሰኞ እስከ እሁድ ነው የምናገኘው፡፡ እስከ እሁድ ክፍት ነው፡፡ ተቀጣጥረህ፣ አንዳፍታ ምሳ በልተህ፣ ሮጠህ ትሄዳለህ፡፡ ቅዳሜ እና እሁድ ግን ስልክህን አጥፍተህ ትዝናናለህ” ሲል አሁንም ተሰብስቦ ገበታ መቁዋደሱ እንደቀጠለ ይናገራል፡፡  

በ1982 ዓ.ም በዱከም ስራውን የጀመረው ምስራቅ በር ዱከም ስጋ ቤት እና ባር መድረሻውን በማስፋት ቅርንጫፉን በአዲስ አበባ ከከፈተ ሶስት ዓመት ሞልቶታል፡፡ የ35 ዓመቱ ሀብታሙ ይልማ አባቱ “ጨርጨር” በሚል ስያሜ በዱከም የጀመሩትን የስጋ ቤት ንግድ ወደ መዲናይቱ ያሻገረ ነው፡፡ እምብዛም ያልተለመደውን ከክፍለ ሀገር ተነስቶ በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ የመክፈት አካሄድን ለምን እንደተከተለ ያስረዳል፡፡

“የእኛ እዚህ አዲስ አበባ ያሉት እና ዱከም ያሉት አብዛኛው ደንበኞቻችን የሚጡት ከዚህ ከአዲስ አበባ ናቸው፡፡ አንደኛ ወደዚህ ከመቅረብ አንጻር፣ ሁለተኛ የመንገዱም አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱ አደጋም ምንም ሲመጣም፣ ወደእዚህ ያለው ደንበኛ በፊት ይመጣ እንደነበረው መምጣት ሲቀንስ እና እዚህ ያለውን ደንበኛ ከማግኘት እና ከመስፋፋትም አንጻር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አዲስ አበባ መምጣቱ ለሁሉም፣ መካከለኛ መደብ (middle class) ለምትለው ሰው የኑሮ ዘይቤ (life style) መለወጫ ነገር እየሆነ ስለመጣ ወደዚህ ወደ አዲስ አበባ መጥተን ለመስራት እና ቅርንጫፍ ከፍተን ደንበኞቻችን ለማግኘት ነው ዋናው ምክንያቶቻችን” ሲል ሀብታሙ ያብራራል።   

መነሻው በክፍለ ሀገር ከተሞች ሆኖ በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ የከፈተው ምስራቅ በር ዱከም ስጋ ቤት ብቻ አይደለም፡፡ የአዳማዎቹ ይልማ እና መረብ ስጋ ቤትም ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል፡፡ አባቱ በ1970 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የጀመሩትን የስጋ ቤት ስራ ተረክቦ እየሰራ ያለው ተመስገን ይልማ በአባቱ ስም የተሰየመውን እውቁን ስጋ ቤት ወደ አዲስ አበባ ማምጣት ችሏል፡፡ ተመስገን ከአዳማ ዘጠና ስምንት ኪሎ ሜትሮች ርቆ ቅርንጫፍ ለመክፈቱ የሚሰጠው ምክንያትም ከሀብታሙ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

“አዲስ አበባ የመጣንበት ዋና ምክንያት ያው እንደምታውቀው አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ናት፡፡ የሰውም ቁጥር ብዙ ነው፡፡ ደንበኞቻችን ደግሞ የአዳማም ከተማ ህዝበ ደንበኛችን ነው፡፡ በተጨማሪ ደግሞ የአዲስ አበባም ከተማ ብዙ ደንበኞች አሉን፡፡ ደንበኞቻችን ያንን ስጋ ፍለጋ ወደ አዳማ አሁንም መሄድ አላቋረጡም ግን በቅርበት ደግሞ [ለመገኘት ነው]፡፡ ደንበኞቻችን  ስጋ ለመብላት አዳማ ብዙ ጊዜ ይመጡ የነበረው የሳምንቱን መጨረሻ፣ ቅዳሜን፣ እሁድን ጠብቀው ነው፡፡ አሁን ግን በአዘቦት ቀንም በሚፈልጉት ሰዓት በአጠገባቸው ለመጠጋት በሚል መጣን አዲስ አበባ ስራውን ከማስፋት አኳያ ነው” ይላል፡፡

ተመስገን የአዲስ አበባውም ሆነ የአዳማው ስራ “በጣም ጥሩ ነው” ይላል፡፡ ከአዲስ አበባ ርቀው ይገኙ የነበሩት ምስራቅ በር፣ ይልማ እና መረብ ስጋ ቤቶች በርካታ ደንበኞችን ሊያፈሩ የቻሉበትን ምስጢር ሀብታሙ እንዲህ ያብራራዋል፡፡ 

“እንግዲህ ያለው ነገር ምንድነው? መጀመሪያ  ተራ ስጋ ቤት፣ ልኳንዳ ከምትለው ከፍ አድርጎ ወደ ቁርጥ ቤት፣ ወደ መዋያ ቤት፣ መዝናኛ ቤት ያመጡት የክፍለሀገሮቹ ቤቶች ይመስሉኛል፡፡ ምክንያቱም አዲስ አበባ ላይ የነበሩትስጋ ቤት ሆነው ከጀርባ ትንንሽ ክፍሎች ላይ አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጠህ ነው፡፡ የዱከሞቹ፣ የናዝሬቱ እና እዚያ አካባቢ ያሉት ስጋ ቤቶች ግን ስጋ ቤትን ከሆቴል ቤት ጋር አንድ ላይ በማድረግ ስጋ ቤቶችን ደግሞ እንደ መዝናኛ ይሄ ጥላ አድርጎ፣ መናፈሻ ነገር አድርጎ አንድ ላይ ከስጋ ቤቶቹ ጋር መስራት እና ሽንት ቤቶቹ፣ ሁሉም ነገሩ ጽዳቱን ጠብቆ እንዲሆን መጀመሪያ የጀመሩት የዱከም ምስራቅ በር፣ አዳማ ይልማ ስጋ ቤት፣ መረብ ስጋ ቤት እነዚህ ናቸው ጥሩ አድርገው በመዝናኛ መልኩ ስጋ ቤትን የጀመሩት ብዬ ነው የማስበው” ሲል ሀብታሙ ያብራራል፡፡

የስጋ አፍቃሪው ዳንኤል እንደ ምስራቅ በር ያሉ ስጋ ቤቶችን እንደ ሁነኛ የመዝናኛ ስፍራ ይቆጥራቸዋል፡፡ “እንዴ! አዎ በጣም ትዝናናለህ፡፡  መጠጥ ልትጠጣ ስትል አሁን እዚህ ሀገር እኮ ዛሬ ማታ እንወጣለን ከተባለ ምስራቅ በር የግድ ትመጣለህ፡፡ በደንብ ጎዝጉዘህ ነው፤ ይይዝልሃል፤ በደንብ ይችለዋል፡፡ በደንብ በልተህ ነው እንጂ አሁን ሽሮ በልተህ ትጠጣለህ እንዴ? አይቻልም፡፡ እዚህ ግን መጥተህ ወይ ግማሽ ኪሎ ሸክላ ጥብስ ወይ ቁርጥህን በልተህ ብትጠጣ ያምርብሃል” ይላል ዳንኤል።

የምስራቅ በሩ ሀብታሙ በአዲስ አበባ የሚገኙ ዘመናዊ ስጋ ቤቶች እንደ አንድ የመዝናኛ ስፍራ ማገልገላቸው ከአሰራራቸው ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ደንበኞችን እነዚህን ስጋ ቤቶች የሚያዘወትሩባቸው ምክንያቶችንም የራሱን ስጋ ቤት ከሌሎች ጋር በማነጸጸር በምሳሌ አስደግፎ ያብራራል፡፡ 

ቦሌ ኤድና ሞል ጀርባ የሚገኘውን የአዲስ አበባውን ቅርንጫፋቸውን የሚያዘወትሩት ወጣቶች እንደሆኑ ሀብታሙ ይገልጻል፡፡ ስጋ ቤቱን በማህበራዊ ድረ ገጾች ማስተዋወቁ እና በዚያው በማህበራዊ ድረ ገጽ የሚተዋወቁ ሰዎች በአካል ተገናኝተው ለማውጋት ቤቱን መምረጣቸው ብዙ ወጣቶችን ለመሳቡ አስተዋጽኦ እንዳለው ይናገራል፡፡ በወጣቶች ዘንድ በተለይ ቅዳሜ “ወደ ቁርጥ ቤት” መሄድ የዘመኑ ፋሽን እንደሆነ ያስረዳል፡፡ በዚያ ተሰባስበው ሲወያዩ መዋል እየተለመደ መጥቷል ይላል፡፡ የስጋ አፍቃሪው ዳንኤል በበኩሉ ስጋ ቤት በተፈጥሮው “ለብቻ የሚበሉበት ሳይሆን የሚሰባሰቡት ነው” ባይ ነው፡፡

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች