በአዲስ አበባ ውስጥ የደረሰ የቦምብ ፍንዳታ | ኢትዮጵያ | DW | 14.10.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

በአዲስ አበባ ውስጥ የደረሰ የቦምብ ፍንዳታ

የኢትዮጵያ መንግስት የመገናኛ ዘደዎችን ጠቅሶ ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው በአዲስ አበባ ከተማ ትናንት በፈነዳ ቦምብ ሁለት ሰዎች ሞተዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ባወጣው ዘገባ መሰረት ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ በፈነዳ ቦምብ ሳቢያ ሁለት ሰዎች በመኖሪያ ቤታቸው መሞታቸውን የሀገሪቱን የመንግስት ሬዲዮ ጠቅሶ ዘግቧል። ፍንዳታው በቦሌ ክፍለ ከተማ በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ መድረሱን እና ለድርጊቱ እስካሁን ኃላፊነት የወሰደ እንደሌለ ዜና ምንጩ የመንግስት የሬዲዮ ጣቢያው የብሔራዊ ፀጥታ እና ደህንነት አገልግሎትን ጠቅሶ ዘግቧል።

ትናንት በኢትዮጵያ እና በናይጄሪያ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ግጥሚያ ከተካሄደበት የእግር ኳስ ስታዲዮም አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መፈንዳቱ የተነገረው ቦምብ በዕለቱ ግጥሚያውን ለመመልከት በተሰበሰዉ ሕዝብ ላይ ጥቃት ለመጣል ታልሞ የተደረገ ይሁን አይሁን አልታወቀም። የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴንን የጠቀሰዉ የአዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘገባ በበኩሉ ሟቾቹ ሁለት የሶማሊያ ተወላጆች መሆናቸዉን አስታዉቋል። ምናልባትም ግለሰቦቹ ፈንጂ በመስራት ሂደት ህይወታቸዉ ሳያልፍ እንዳልቀረ ዘገባዉ ያመለከተዉ።

ከሶማሊያ ጋ የምትዋሰነው ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ህብረት ስር ሆና እኢአ በ2011 አሸባብን ለመዋጋት ወታደሮቿን በሶማሊያ ማዝመቷ ይታወሳል። አሸባብ በበኩሉ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተቃናቃኞቹ ላይ አፀፋ ሲከፍል ታይቷል። በተለይ ኬንያ ላይ በቅርብ በናይሮቢ ውስጥ በሚገኝ የገበያ አዳራሽ ላይ በጣለው ጥቃት 67 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል። ናይሮቢ ውስጥ ከደረሰው ጥቃት በኃላም የኢትዮጵያ መንግስት ሶማሊያ ያዘመተው ወታደሩ በሶማሊያ እንዲቆይ መወሰኑን አሳውቆ ነበር። ዛሬ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፤ የቦሌ ፖሊስ ጣቢያ እና ፌደራል ፖሊስ ያደረግናቸው የስልክ ጥሪዎች ምላሽ አጥተው ውለዋል። አደጋው ከደረሰበት ከሁለት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ወደሚገኘው የሪፖርተር ጋዜጣ አዘጋጆች ቢሮ ስንደውል፣ ዕለቱ የዕረፍት ቀን ስለነበር ምንም ነገር እንዳልታዘቡ ጋዜጠኛ የማነ ናግሽ ገልፆልናል።

እንደ የአዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘገባ ከሆነ ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን የሰዎቹን ማንነት በማጣራቱ ረገድ ምርመራዉ ቀጥሏል።

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic