በአዲስ አበባ ከተማ "የኮሪደር ልማት" ሥራ ላይ የፓርቲዎች ቅሬታ
ሰኞ፣ ጥቅምት 4 2017በአዲስ አበባ ከተማ "የወንዝ ዳር ልማትና የጫካ ፕሮጀክት" በሚል ተጀምሮ አሁን የኮሪደር ልማት በሚል መጠኑንና አድማሱን አስፍቷል ያሉት ሥራ "የመቶ ሺህዎችን ሕይወት እያመሳቀለ" ነው ሲሉ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታቸውን አሰሙ።
የጋራ መግለጫ ያወጡት መኢአድ፣ ኢሕአፓ፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄና እናት ፓርቲዎች፤ "ኢ- ሕገ መንግሥታዊ፣ አግላይ እና የበላይና የበታች አካሄድ" የተከተለ ነው ያሉትን ይህንን ሥራ "በጽኑ እናወግዛለን" ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደሚለው ግን "የኮሪደር ልማት ሥራው ዋና oaላማ አዲስ አበባን ለመኖር ምቹ ማድረግ፣ ማደስ፣ ገፆታዋን ማሻሻል እና ከልማት ሥራው ማንም ወደ ኋላ ሳይቀር ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ነው።"የኮሪደር ልማቱ ውጤትና ተግዳሮቱ
የፓርቲዎቹ መግለጫ ዝርዝር ይዘት
አራቱ የፖለቲካ ድርጅቶች አዲስ አበባ ውስጥ እየተከናወነ ያለው የ"ኮሪደር ልማት" የሚል ስያሜ የተሰጠው ሥራ ግብ "ነባሩን ማኅበረሰብ ከማኅበራዊ መሠረቱ መነጠልና ማሳሳት፣ የእምነት ቦታዎችን ያለሰው ማስቀረት፣ ሰውን ከመሐል መግፋት ከዳር ማስጨነቅ፣ መንግሥት የገጠመውን በጀት እጥረት ከሊዝ ሽያጭ መሰብሰብ" ነው ብለዋል።
ፓርቲዎቹ አደረግነው ባሉት ዳሰሳ "በድንገት ቤታቸው የፈረሰባቸውና ይፈርሳል በሚል ሲነገር ለፀና ሕመም የተዳረጉ፣ ሥራቸው ሙሉ ለሙሉ የተቋረጠና ለከፋ ችግር የተዳረጉ መኖራቸውን አረጋግጠናል፣ ይህም የመቶ ሺህዎችን ሕይወት እያመሰቃቀለ እንደሚገኝ" መገንዘባቸውን ጠቅሰዋል።የመንገድ ኮሪደር ልማቱ እና የተነሺዎች ጥድፊያ በአዲስ አበባ
መንግሥት የዜጎችን መብት እንዲያከብርና ማኅበረሰቡን "መሠረታዊ በሆነ መልኩ ከሚያናጋ በልማት ሽፋን የሚተገበር" ካሉት "ደባ" እንዲታቀብ ያሳሰቡት ፓርቲዎቹ የፈረሳው ሰለባ የሆነው ነዋሪ ድርጊቱን በሰላማዊ መንገድ እንዲቃወም እና ከቦታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች የነበሩበትን ቦታ ካርታና መሰል የነዋሪነት ማስረጃዎች መንግሥት በጥንቃቄ እንዲያስቀምጥ" ጠይቀዋል።
የኢሕአፓ የአዲስ አበባ ኮሚቴ በፊናው በሰጠው መግለጫ የልማት ሥራውን እንደማይቃወም ገልጾ፣ ሆኖም ሥራውን "ለሕዝብ ጥቅም ያላመጣ፣ የልማት ተነሺዎችን ያገለለ፣ ሥራ አጥነትን ያስፋፋ፣ ሰዎችን ለከፋ ችግር የዳረገ፣ የሕዝቦችን ማሕበራዊ እሴት የናደ፣ ጦርነትና ግጭት ሽሽት ከየክልሎች የሚመጡ ዜጎችን መልሶ ከከተማው ያፈናቀለ፣ ይልቁንም ከብልጽግና ፓርቲ ፖለቲካዊ ፍላጎት የዘለለ ትርጉም የሌለው" ሲል በብርቱ ተችቷል፤የፓርቲው የአዲስ አበባ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አበበ አካሉ።
"የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሰላምና ፀጥታ፣ የፍትሕ ፍላጎት የመብት መከበር፣ ጥቅመቸው መጠበቁን ጉዳይ በቸልታ ማለፍ መላውን ሕብረተሰብ ከባድ ወደሚባል እና ዋጋ ሊያስከፍል ወደሚችል ወደ ሕዝባዊ ቁጣ መገንፈል እና ተዛማጅ ጉዳዮች ሊፈጥር ይችላል የሚል አሁንም የፀና ሥጋት አለን"። የአዲስ አበባ «ኮሪደር ልማት»ን የጎበኘው ጎርፍ
የሥራው ዓላማ ከተማዋን ምቹ ማድረግ፣ ማደስ እና ገፆታዋን ማሻሻል ነው - መንግሥት
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብዙ የከተማዋ አካባቢዎችን ይሸፍናል የተባለለት ሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት መጀመሩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ "የኮሪደር ልማት ዋና ዓላማዉ ከተማችንን ለመኖር ምቹ ማድረግ፣ ማደስ እና ገፆታዋን ማሻሻል" ነዉ። በዚህም ሲኖሩ ከነበሩበት ለተነሱ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤቶችን፣ በቂ የመሥሪያ ስፍራዎችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ምትክ መሬት እና ካሳም ማዘጋጀቱን አስታውቋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ