በአዲስ አበባ ከተማ የሚፈናቀል ነዋሪ የለም ተባለ | ኢትዮጵያ | DW | 25.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በአዲስ አበባ ከተማ የሚፈናቀል ነዋሪ የለም ተባለ

በ 10 ኛዉ የአዲስ አበባ ከተማ መሪ ፕላን የሚፈናቀል ነዋሪ የለም ተባለ። በአዲሱ የከተማዋ መሪ ፕላን ላይ ሰሞኑን ከነዋሪወች ጋር በተካሄደዉ ዉይይት ህብረተሰቡ የመፈናቀልን ጉዳይ እንደ ስጋት ያነሳ ቢሆንም በመሪ ፕላኑ ከአሁን ወዲያ የሚፈናቀል ነዋሪ የለም ሲል የአዲስ አበባ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ገልጿል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:40

የሚፈናቀል ነዋሪ የለም ተባለ

አንዳንድ አስተያየት ሰጭወች ግን መፈናቀሉ  አሁንም ይቀጥላል የሚል ስጋት  አላቸዉ። ዘጠኝ  መሪ ፕላኖችን  ያስተናገደችዉ አዲስ አበባ አስረኛዉን ለመተግበር በዝግጅት ላይ ትገኛለች።ለሚቀጥሉት 25 አመታት ያገለግላል በተባለዉ በዚህ መሪ ፕላን ምንነትና ፋይዳ ዙሪያ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ 116 ወረዳወች 300 ሺህ ህዝብ የተሳተፈበት ዉይይት መካሄዱን የአዲስ አበባ ፕሮጀክት ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዳዊት ንጉሴ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በ2006 አ/ም የከተማዋ ነዋሪ በዚሁ መሪ ፕላን ላይ ዉይይት አድርጓል ያሉት ሃላፊዉ፤ ከህብረተሰቡ በርካታ ግብአቶች መገኜታቸዉንና  በመሪ ፕላኑ መካተታቸዉን ገልጸዋል።በዚህም ህብረተሰቡ የከተማዋ እቅድ የኔ ነዉ ብሎ እንዲፈጽም የሚያስችል ግንዛቤ ተይዟል ብለዋል።    

እንደ አቶ ዳዊት ገለጻ መሪ ፕላኑ አዲስ አበባ ከተማን ዘመናዊና አለማቀፋዊ  ከተማ  የሚያደርግና የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር  ጥያቄ የሚመልስ ቢሆንም  ህብረተሰቡ ከአሁን በፊት ከነበሩ ችግሮች በመነሳት በተባለዉ ልክ ይፈጸማል ወይ የሚል ጥያቄ አለዉ ብለዋል።በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ በኩል የነበሩ ችግሮችን መሪ ፕላኑ እንዴት ይፈታቸዋል ብለን ላነሳንላቸዉ ጥያቄ  ከአቅም ችግር ጋር የሚያያዝ በመሆኑ በስልጠና እንደሚፈታ ገልጸዋል።

 ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዚያት  በህብረተሰቡ  ዘንድ ቅሬታና ተቃዉሞ ሲያስነሳ የነበረዉ ነዋሪወችን ከይዞታና ከመኖሪያ ቦታ  የማፈናቀል ጉዳይ  ለዉይይት በቀረበዉ በዚህ የከተማዋ  መሪ ፕላንም እንደስጋት እየታየ ነዉ። አንድ ስማቸዉ እንዳይጠቀስ  የፈለጉ አስተያየት ሰጭ ስጋታቸዉን እንዲህ ይገልጹታል።

«ምንም ቁርጥ ያለ  ያስቀመጡት ነገር የለም።መሰረተ ልማት እናሟላላችኋለን ነዉ ያሉት እንጅ አትፈናቀሉም አላሉም ።ማፈናቀላቸዉ የማይቀር ነዉ። የሚገነቡት ነገሮች፤  የምናያቸዉ ነገሮች፤ አልፎ ሄዶ ኮንዶሚኒየም አምስት ስድስት ኪሎ ሜትር ገብቶ ነዉ የሚገነባዉ በዚህ መካከል አርሶ አደሮች አሉ እና ይሄ እንዴት ነዉ የማያፈናቅለዉ ?»

የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ሃለፊ አቶ ዳዊት ንጉሴ ግን  ከዚህ ወዲህ የሚፈናቀል ነዋሪ የለም ይላሉ።

«አን ዱ በዉይይቱ የተነሳዉ የመፈናቀል ጉዳይ ነዉ። ነገር ግን መሪ ፕላኑ  አንዱ ያስቀመጠዉ ጥሩ ነገር ተግባራዊ  ሲደረግ ከአካባቢዉ የሚፈናቀል  ሰዉ አይኖርም ። ይልቁኑ እዛዉ አካባቢ በልማቱ የሚሳተፉበትና የሚጠቀሙበት አሰራር ነዉ ዲዛይን የተደረገዉ። መሪ ፕላኑ ተግባራዊ ሲደረግ የሚፈናቀሉ ሰወች አይኖሩም እሱን ማስተካከል የሚያስችል  ስትራቴጅ ተቀይሷል።»

 በአዲስ አበባና አካባቢዋ የሚገኙ አርሶ አደሮች  ከይዞታና ከመሬታቸዉ ያለ አግባብ ተፈናቅለዋል በሚል በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች ለወራት የዘለቀ ተቃዉሞ መደረጉ ይታወሳል።በመሆኑም በዘንድሮዉ ዓመት ከዚህ በፊት ተፈናቅለዉ በከፋ የኑሮ ሁኔታ ላይ ያሉ 20 ሺህ አርሶአደሮችን መልሶ ለማቋቋም ማቀዱን መንግስት መግለጹ ይታወቃል።

ፀሐይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ

 

Audios and videos on the topic