በአዉሮፓ ፓርላማ የቀረበዉ እማኝነትና ከፓርላማዉ የሚጠበቅ እርምጃ | የጋዜጦች አምድ | DW | 18.05.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

በአዉሮፓ ፓርላማ የቀረበዉ እማኝነትና ከፓርላማዉ የሚጠበቅ እርምጃ

በኢትዮጵያ ባለፈዉ ዓመት ግንቦት ሰባት በተካሄደዉ ምርጫና እሱን ተከትሎ እስካሁን እልባት ያላገኘዉን የምርጫ ዉዝግብ አስመልክቶ የተለያዩ የተቃዉሞ ሰልፎች ሲካሄዱ ለየመንግስታቱ ቅሬታና አቤቱታ ሲቀርብ ሰንብቷል።

በቅርቡ በአሜሪካ ኮንገረስ ከመንግስት ወገን ተወካይ በተገኙበት የተካሄደ የእማኝነት መድረክ ነበር። ያንኑ የመሰለ ምንም እንኳን የመንግስት ወኪል ባይገኙም በአዉሮፓ ፓርላማ ተካሂዷል። በመድረኩ ለእማኝነት ከቀረቡት መካከል የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፤ የአገር ዉስጥና የዉጪ አገር ዓለም ዓቀፍና የአዉሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች፤ የአዉሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑክ መሪ፤ ፈረንሳዊቷ የኢንተርኔት ድረገፅ አንቀሳቃሽ የዉጪ ዜጋ የያዙት መረጃና ያዩትን የተከታተሉትን ለመድረኩ አቅርበዋል።

እማኝነታቸዉን ከሰጡት መካከል በኢትዮጵያ የተካሄደዉን የአምናዉን ምርጫ ለመታዘብ የአዉሮፓ ህብረት የላከዉን ቡድን የመሩትና ኋላም ዘገባዎቻቸዉን በተከታታይ ያቀረቡት የፓርላማዉ አባል የተከበሩ አና ጎሜዝ ግንባር ቀደሟ ነበሩ።

አና ጎሜዝ በወቅቱ በምርጫ ታዛቢነት ተሰማርተዉ ያስተዋሉትን በተለይ ከድምፅ ቆጠራዉ ጀምሮ ነዉ ችግር ያየሁት ሲሉ ነዉ ለፓርላማዉ በድጋሚ የተናገሩት። በዚያም ስለምርጫዉ ባቀረቡት ዘገባ የተካሄደዉ ምርጫ ህዝቡ ከተገመተዉ በላይ ከመሳተፉ ሌላ የድምፅ ማጣራቱ ሂደት እሱን ተከትሎ የተፈጠሩ ተቃዉሞና ከመንግስት ወገን የተወሰደዉ እርምጃ ተዳምሮ ዓለም ዓቀፍ መስፈርትን አያማላም ዲሞክራሲያዉ፣ ነፃና ግልፅ ለመባል የሚለዉን አብራርተዋል።


በእማኝነት መድረኩ እንዳስረዱት የፖለቲካ ተቃዋሚዎቹና በምርጫዉ የተወዳደሩት በነፃነት ለመንቀሳቀስ ስጋት እንዳላቸዉ በተደጋጋሚ ሲገልፁም የለም መንግስታችሁ ይህን እንዲያከብር ቃል ገብቷል ብለዉ በማሳመን እንደገፋፉ ኋላም ሰዎቹ የተናገሩት እንደደረሰ ጠቀሱ።

ከዘገባዎና ከሰጡት የእማኝነት ቃልዎ የእርስዎ ምክር ቤት ምን ያደርጋል ብለዉ ይገምታሉ? ለሚለዉ ጥያቄ የእሳቸዉ ምላሽ፤ የመንግስት ቃል በማመን እኛዉ ገፋፍተን በምርጫዉ እንዲሳተፉ አድርገናል ዳር ቆመን ማየት አንችልም ስለዚህ ከምርጫዉ ጋር በተገናኘ በእስር ላይ የሚገኙት ሁሉ ከተከሰሱበት አስገራሚ ክስ ነፃ እንዲለቀቁ እንደፓርላማ አባልነቴ አጠቃላይ ምክር ቤቱ ከጎኔ እንዲቆም ነዉ ካሉ በኋላ

«ዝም ብለን መቀመጥ አንችልም፤ እንደአዉሮፓ ፓርላማ አባልነቴ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር፤ ለዲሞክራሲና ለህግ የበላይነት መቆም ሃላፊነቴ ነዉ፤ እንዲሁም ይህን የሚጥሱትን በተለይ በኢትዮጵያ እንዲያቆሙ መታገል ግዴታዬ ነዉ። የአዉሮፓ ፓርላማና ኮሚሽኑ በአዉሮፓ መስፈት መሰረት እርምጃ እንዲወስዱ በመቀስቀስና በማስረዳት የኢትዮጵያ መንግስት ከሁሉም በፊት ያሰራቸዉን በሙሉ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ በመፍታት የኢትዮጵያ ህዝብ ዲሞክራሲን በተግባር መተርጎሙን እንድናይ ዉይይት ከሁሉም ኃይሎች ጋር እንዲያደርግ እንዲያስገድዱ ለማድረግ ነዉ።»

ኮሚሽነር ሚሼል ሄደዉ ከመንግስትና ከታሰሩት ጋር መነጋገራቸዉ ብቻዉን ዉጤት አይደለም ያሉት ጎሜዝ የአዉሮፓ ፓርላማ ኢትዮጵያ ዉስጥ ከሚገኙት አምባሳደሮች ጋር በመቀናጀት ወሳኝ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅበት ማስገንዘባቸዉንና ያንንም በቅርቡ እንደሚጠብቁ ገልፀዋል።

አቶ አረጋዊ በርኼ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ኃይሎች ህብረት የተባለዉን ፓርቲ በመወከል በዚህ መድረክ ለእማኝነት ሲገኙ ፓርላማዉ ምን እንደሚጠብቁ እንዲህ ነዉ ያሉት

አቶ አንዳርጋቸዉ ፅጌ ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲን በመወከል ዚህ በፊት በአሜሪካን ኮንግረስ በተካሄደዉ ተመሳሳይ የእማኝነት መድረክ ቀርበዉ ቃላቸዉን ሰጥተዋል። አለ ያሉትን ችግር በዝርዝር አስረድተዋል። በዚህ ሳምንት በአዉሮፓ ፓርላማ ለተመሳሳይ ተግባር መገኘታቸዉን በመጥቀስ ከዛኛዉም ምን እንደተገኘ ከዚህስ ምን እንደሚጠበቅ ሲያስረዱ፤

በአሜሪካዉ ኮንገረስ ተገኝተዉ ከነበሩት መካከል የአኝዋክ የፍትህ ምክር ቤት ዳይሬክተር
የሆኑት አቶ ዑባንግ ሜቶ አንዱ ናቸዉ። በቅድሚያ ያስረዱት እሳቸዉ የመጡት በአንድ ብሄር ላይ ስለተፈፀመ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሳይሆን መላዉ ኢትዮጵያን እንደሚመለክ ነዉ። አያይዘዉም ፓርላማዉ ማድረግ አለበት ያሉትን ገልፀዋል።

«በኢትዮጵያ እየተፈፀመ ያለዉ የስዓዊ መብቶች ጠሰት ተጋኖ የቀረበ አይደለም። ይኸዉም እራሱ መንግስት የራሱን ህዝብ እያሸበረ ነዉ የሚኘዉ። የአዉሮፓ ህብረት ሁለት ዓይነት አቋም ሊኖረዉ አይገባም። በየትኛዉም አገር የሚፈፀም የሰብዓዊ መብቶች ረገጣን አስመልክቶ የሚወሰዉ እርምጃ ተመሳሳይ መሆን አለበት። ለእነሱ ያስተላለፍኩት መልዕክት በኢትዮጵያ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ዉጪ ከመሆናቸዉ በፊት ህብረቱ ቁጭ ብሎ ከማየት ይልቅ የተሻለ ሚና ሊጫወት እንደሚገባዉ ነዉ። ያኔ እናስተካክል ቢሉ የሚችሉት አይሆንም። ነገሮችን እንዲህ እንዲያዩ ነዉ የነገርኳቸዉ። በቤላሩስ ያደረጉትን እንዲሁም በዚምባቡዌ ከምርጫ ጋር በተገናኘ የፈፀሙት ሁሉ በኢትዮጵያም መታየት አለበት። ኢትዮጵያዉያን አሁን እያደረጉት ካለዉ በላይ ሊደረግላቸዉ ይገባል። ይህን ማድረግ ከተሳናቸዉ ለስማቸዉ ጥሩ አይሆንም በጥንቃቄ ሊያዩትና ሊሰሩት ይገባል ብዬ አምናለሁ።»