በአዉሮፓ የህዝብ ቁጥር መቀነስ የሚያስከትለዉ ቀዉስ | ኤኮኖሚ | DW | 18.03.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

በአዉሮፓ የህዝብ ቁጥር መቀነስ የሚያስከትለዉ ቀዉስ

የአዉሮፓ ህብረት ኮሚሺን የህዝብ ቁጥር እየቀነሰ መሄዱ በአህጉሪቱ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ላይ ጠንካራ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል አስታወቀ። ከዚህ ጋር ተያይዞም መስራት የማይችለዉ ሆኖም ቁጥሩ እየተበራከተ የሚገኘዉ ህዝብ የአህጉሪቱ የምጣኔ ሃብት እድገት ጎታች ሊሆን እንደሚችል ገልጿል።

የብሪታንያ ገንዘብ ሚንስትር ጎርደን ብራውን ከጀርመናዊው አቻቸው ሀንስ አይሽል ጋር በአውሮፓ ኅብረት ስብሰባ ላይ ሀሳብ ሲለዋወጡ

የብሪታንያ ገንዘብ ሚንስትር ጎርደን ብራውን ከጀርመናዊው አቻቸው ሀንስ አይሽል ጋር በአውሮፓ ኅብረት ስብሰባ ላይ ሀሳብ ሲለዋወጡ

የሚወለደዉ እያነሰ፣ ወጣትና የመስራት አቅም ያለዉ የህዝብ ሃይል ቁጥር እየቀነሰ በአንፃሩ የማይሰራዉና በጡረታ የሚገለለዉ ሰዉ ቁጥሩ እየጨመረ ሄዷል በአዉሮፓ።
የተሻለ ጤና፤ ከፍተኛዉ የእድሜ ጣራና አነስተኛዉ የወሊድ ሁኔታ በአዉሮፓ ያልታሰበ የህዝብ ማነስ ያስከትላል በማለት ነበር የአዉሮፓ ህብረት በትናንትናዉ እለት በቀረበዉ ጥናቱ ያሳየዉ።
ይህ የቀረበዉ አዲሱ ጥናት በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ክርክር ተካሂዶ አህጉሪቱን ከህዝብ እጥረት እንዴት መታደግ እንሚቻልም ዕቅድ አካቷል።
ጥናቱ እንዳሳየዉ አሁን የሚታየዉ አነስተኛ የመዋለድ ልማድ ለሚቀጥሉት በርካታ አመታት መቀጠሉ አይቀርም። በዚህ ሳቢያም እስከመጪዉ 2025 እንደ አ.አ. መሆኑ ነዉ 469.5 ሚሊዮን የሆነዉ የአዉሮፓ የህዝብ ቁጥር በ2030 468.7 ሚሊዮን ያሽቆለቁላል።
በተቃራኒዉ የዩናይትድ ስቴትስ የህዝብ ቁጥር እንደ አ.አ. በ2000ና በ2025ዓ.ም. መካከል 25.6 በመቶ እንደሚጨምር ይጠበቃል።
ኮሚሽኑ የስራ እድል እየጠበበ መሄድና አስተማማኝ ስራ አለመኖር፤ እንዲሁም የኑሮ ሁኔታ መናር ብዙዎች ትዳር እንዳይመሰርቱ አድርጓል ይላል።
በተጨማሪም ልጅ ለማሳደግ ከመንግስት የሚሰጡ ድጋፎች፤ የወላጆች እረፍት፤ የህፃናት እንክብካቤና እኩል እፍያ አለመኖር በአዉሮፓ ለሚታየዉ ከመዉለድ መታቀብ ዋነኛ ምክንያት ነዉ በማለት ጠቅሷል።
ጥናቱ በአንዳንድ አገራት እንደታየዉ ይህን የመሰሉት ማበረታቻዎች የስራ እድልን ማብዛት በተለይም ለሴቶች የስራ እድል መስጠት የወላጆችን ቁጥር ያበራክታል የሚል መከራከሪያ ይዞ ነዉ የቀረበዉ።
የኮሚሽኑ መግለጫ እንደሚለዉ የሰለጠነችዉ አዉሮፓ በመዉለድ አዲስ ትዉልድ ሳትተካ የምጣኔ ሃብት እድገት ኖሯት አያዉቅም።
የህብረቱ የማህበራዊ ዘርፍ ኮሚሽነር ቪላድሚር ስፒደል በትናንታዉ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደገለፁት ይህን መሰሉ ማህበራዊ ለዉጥ በሁሉም መስክ በእለት ተዕለት ህይወት ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል።
አሁን ያለዉ አመለካከት መለወጥ አለበት የሚሉት ኮሚሽነር የወሊድ ቁጥር ቀንሶ የሰራተኛዉ ሃይል ሲመናመን ጤናዉ ተጠብቆ ረጅም እድሜ ለመኖር የሚችለዉ በማንናዉም የዕድሜ ክልል የሚገኘዉ አዉሮፓዊ ይጎዳል።
ከአሁን አንስቶ እስከ መጪዉ 25 አመታት ከ65 አመት በላይ የሆናቸዉ ሰዎች ቁጥር 50 በመቶ ስለሚደርስ አዉሮፓ 20.8 ሚሊዮን የሚሆነዉን ሰራተኛ ሃይሏን ታጣለች።
በተቃራኒዉ በዚህ ሳቢያ የሚከተለዉን ቀዉስ ለማረጋጋት አዉሮፓ ባጠቃላይ ከ70 በመቶ በላይ የሰራተኛ ሃይል ያስፈልጋታል።
እንደ እሳቸዉ እምነት ይህን ያንዣበበ አደጋ ፓለቲካ ብቻዉን ሊፈታዉ አይችልም። ፓለቲካዉ በማህበረሰቡ ዉስጥ ካለዉና ከሚመጣዉ ገፅታ ጋር እጅ ለእጅ መሄድ ይኖርበታል።
በጉዳዩ ላይ የተመራመሩ ምሁራን እንደሚሉት አዉሮፓን ያጥለቀለቀዉ የስደተኛ ብዛት ለጊዜዉ የሰራተኛዉን ሃይል ለማበራከት ቢረዳም የረጅም ጊዜ መፍትሄ ግን መሆን አይችልም።
እንደ ምሁራኑ እምነት በአዉሮፓ የሚገኘዉ የስደተኛ ቁጥር ለጊዜዉ በተወሰነ የስራ መስክ አካባቢ ምጣኔ ሃብቱን ከድርቅ ሊጠብቀዉ ይችላል።
ያም ሆኖ ግን እነሱም እድሜያቸዉ ገፍቶ ለጡረታ ሲደርሱ አሁን የሚያስፈልገዉን ወጣት ብዛት ስለማይሟላ ቀዉሱ ይቀጥላል።
አሁን ባለዉ አያያዝ በአዉሮፓ በእድሜ የገፋዉ ህዝብ ብዛት ለጤና አጠባበቁም ሆነ ለጡረታ አሰራሩ ከፍተኛ ችግር ይሆናል ተብሎ ተፈርቷል።
በመሆኑም የአዉሮፓ ህብረት አባል አገራት እስከ ዛሬ ያደርጉት እንደነበረዉ ለማህበራዊ ደህነት ሲባል የሚሰጡትን የገንዘብ ድጋፍ እንኳን ለሌላዉ ለራሳቸዉ ዜጋም ቢሆን ለመስጠት ይቸገራሉ።
ሁኔታዉ ከቁጥጥር ዉጪ ከመሆኑ በፊትም የአዉሮፓ ህብረት ከአባል መንግስታቱ ጋር የጤና እንክብካቤ፤ የጡረታ አሰራሮችንና የስደተኞች ጉዳይን በሚመለከት አዲስና አንድ ወጥ የፓሊሲ ሃሳቦች ላይ ለመነጋገር እቅድ አለዉ።
ምንም እንኳን ይህን መሰሉ ዉይይት በአዉሮፓ የመጀመሪያ ቢሆን እርምጃ የመዉሰጃዉ ጊዜዉ አሁን ነዉ።