″በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ″ : በጎ አድራጎትና ህክምና | ወጣቶች | DW | 17.09.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

"በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ" : በጎ አድራጎትና ህክምና

የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዶቻችን ኢትዮጲያ ውስጥ በጎ ፍቃደኝነትን የማጎልበት አላማ ያላቸው ወጣት ሀኪሞች ናቸው። ይህንንም ዓላማቸውን እውን ለማድረግ  GIV Society Ethiopia የሚል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አቋቁመው ከ 1300 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ነፃ ህክምና እንደሰጡ ይናገራሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:05

GIV Society Ethiopia

ዶክተር ምስክር ካሳሁን በቅርቡ የስራውን ዓለም የተቀላቀለች የጠቅላላ ሀኪም ባለሙያ ናት። እንዲሁም GIV Society Ethiopia የተባለውን የርዳታ ድርጅት ከመሰረቱት አንዷ እና የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ናት። «በጎ ፍቃደኝነት እየተበረታታ ጎን ለጎን ህብረተሰቡ ላይ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚሞክር ድርጅት ነው። » ስትል የድርጅቱን ዋና አላማ ታብራራለች። ድርጅቱ ከተመሠረተ ገና 9ኛ ወሩ ነው።  ይህንንም ለመመስረት ለምስክር አርዓያ የሆናት ካናዳ ውስጥ ከአራት ዓመት በፊት የተመሠረተ አንድ ድርጅት ነው። ከዛም የርዳታ ድርጅቱን ለመመስረት ሌሎች ወጣቶችን ማማከር ጀመረች። ከእነዚህ አንዱ  GIV Society Ethiopiaን  አብሮ የመሰረተው እና ፕሮግራም ዳሬክተር  የሆነው ዶክተር ዮናታን ገብሩ ነው።

የ25 ዓመቷ ዶክተር ምስክር በዚህ አጭር ጊዜ ድርጅቱ በርካታ በጎ ፍቃደኞችን ኢትዮጵያ ውስጥ ማሰባሰብ እንደቻለም ትናገራለች።« ወደ 15 እንሆናለን። ርዳታውን የሚሰጡልን መጥተው የሚያክሙልን በጎ ፍቃደኞች 300 ይሆናሉ።» እስካሁን ከ 1300 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ነፃ ህክምና እንደሰጡ የምትናገረው ዶክተር ምስክር በቀን ከ 200 እስከ 300 የሚሆኑ ሰዎች የሚታከሙበት ስድስት መርኃ ግብሮች ማዘጋጀታቸውንም ትናገራለች።

ዶክተር ማርያማዊት ሰለሞን  ይህንን የበጎ አድራጊ ድርጅት ከተቀላቀለች አራት ወር ሆናት። በአሁኑ ሰዓት በሀኪምነት ለማገልገል ፍቃዷን እየተጠባበቀች ስለሆነ በ GIV Society Ethiopia ውስጥ በጎ ፍቃደኞችን በማስተባበር ስራ ላይ ብቻ ትሰራለች። « ማስታወቂያዎችን በማውጣት በተለያዩ ሙያ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎችን እንዲመጡ እና እንዲመዘገቡ ማድረግ ፣ ምን ምን ማድረግ እንዳለባቸው የመግለፅ ስራ ነው የምንሰራው።» የምትለው የ26 ዓመቷ ወጣት ሀኪም በአሁኑ ሰዓት የገቢ ምንጭ ባይኖራትም የስራ ፍቃድ እስክታገኝ ድረስ በበጎ ፍቃደኝነት ሌሎችን በነፃ መርዳት መቻሏ በጣም ያስደስታታል። «በጣም ታላቅ ስሜት ነው። ድካም አይደለም የሚሰማን ፣ ብዙ ስራ ሰርተን መጨረሻ ላይ ተደስተን ነው የምንሄደው። የምናገኘው ርካታ ብቻ ሳይሆን ታክሞ የሚወጣው ሰው ምርቃት፣ በጣም አስደሳች ነገር ነው። ትልቅ ስራ እየሰራን እንደሆነ አዕነት ስሜት ይሰጣል» ዶክተር ማርያማዊት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ነው ህክምና መማርን የተመኘችው። በምርጫዋም ደስተኛ ናት።

ዶክተር ዮናታን በአንፃሩ መደበኛ ስራ አለው። የ28 ዓመቱ ወጣት ሀኪም አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ክፍል ውስጥ ይሰራል። በትርፍ ጊዜው ደግሞ በ GIV Society Ethiopia ስራዎች በአግባቡ እንዲፈፀሙ ያመቻቻል። ወጣት ሀኪሞቹ ወደፊት ነፃ የህክምና አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር በተለያዩ የማህበራዊ ጉዳዮችን በሚዳስሱ ዘርፎች ላይ መስራት እንደሚፈልጉም ይናገራሉ። « በገንዘብ መዋጮ፣ አስቤዛ በመግዛት ሊሆን ይችላል ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበትን ፕላትፎርም መፍጠር ነው አላማችን» ይላል ዶክተር ዮናታን። ሌላው እቅዳቸው ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጪ መስራት ነው። 

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች