በአንዋር መስጊድ ላይ የተጣለዉ ቦምብ | ኢትዮጵያ | DW | 14.12.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

በአንዋር መስጊድ ላይ የተጣለዉ ቦምብ

አደጋዉ እንደተሰማ በተለይ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሠራጩ መልዕክቶች ፍንዳዉ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመድ ግጭት የፈጠረዉ ነዉ ብለዉ ነበር። ሌሎች ደግሞ -የተለመደዉ ጥይት ወይም ተኩስ---

አዲስ አበባ በሚገኘዉ በታላቁ አንዋር መስጊድ ላይ ባለፈዉ አርብ የቦምብ ጥቃት መጣሉን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ጉባኤ አጥብቆ አወገዘ። የጠቅላይ ጉባኤዉ ፕሬዝደንት ሐጂ መሐመድ አሚን ጀማል እንዳሉት አደጋዉ የእስልምናን አስተምሕሮ የሚፃረር እና ኢሠብአዊ ድርጊት ነዉ። ባለፈዉ አርብ ሳምታዊዉ የጁመዓ ሶላት ከተሰገደ በኋላ በአንዋር መስጊድ ቅጥር ግቢ ተሠባስበዉ መዉሊድን በሚያከብሩ ምዕመናን መሐል የተወረወረዉ ቦምብ 19-ሰዎችን አቁስሏል።

አንዋር መስጊድ ቅጥር ግቢና አካባቢዉ የሙስሊም ምዕመን ደም ሲፈስ-የአርቡ በርግጥ አዲስ አይደለም።ግን ዱላ፤ካራ፤ ምንላባት ጥይት እንደሁ እንጂ ፈንጂ ብዙም አይታወቅም።አርብ በግልፅ ታወቀ።አደጋዉ እንደተሰማ በተለይ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሠራጩ መልዕክቶች ፍንዳዉ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመድ ግጭት የፈጠረዉ ነዉ ብለዉ ነበር።ሌሎች ደግሞ -የተለመደዉ ጥይት ወይም ተኩስ።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ጉባኤ ፕሬዝደንት ሐጂ መሐመድ አሚን ጀመል እንዳረጋገጡልን ሁለቱም አይደለም።ቦምብ-ምናልባት የእጅ ቦምብ እንጂ።

የቦምቡ ብዛት ወይም የፍንዳታዉ መጠን በዉል አልታወቀም።ያደረሰዉ ጉዳት ግን-ሐጂ መሐመድ አሚን ይቀጥላሉ።አደጋዉን የጣለዉ ወገን ማንነት እስካሁን አልተነገረም።ተጠርጣሪዎች ሥለመያዝ አለመያዛቸዉም የታወቀ ነገር የለም።የሚታወቀዉ:- ፖሊስ ጉዳዩን እያጣራ መሆኑ ብቻ ነዉ።አደጋዉን ማንም አደረሰዉ-ማን ሐጂ መሐመድ አሚን ጀማል እንዳሉት የዋሕ ምዕመንን በጅምላ መግደል፤ ማቁሰል፤ ማሸበር ወይም ለመግደል ማቁሰል መሞከር የእስልምና አስምሕሮን የሚፃረር ነዉ። ዉጉዝ።

ፍንዳታዉ ሙስሊሙን ማሕበረሰብ ማስደንገጥ-ማሳሰቡ አልቀረም።ታላቁን አንዋር መስጊድ ለሚያዘወትሩ ምዕመናን ደግሞ ድንጋጤዉ የናረ ነዉ።ይሁንና ሐጂ መሐመድ አሚን ጀማል እንዳሉት የመስጊዱም ሆነ መስጊዱን የሚያዘወትረዉ ምዕመን እንቅስቃሴ ከወትሮዉ ብዙም አልታጎለም።

ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች በእስልምና ሥም የየዋሐያን ሕይወት ለማጥፋት ከሚንቀሳቀሱ ሐይላት እንዲጠነቀቁ፤ የእስልምና እና የነብዩ ሐመመድን አስተምሕሮት ገቢር እንዱያደርጉም የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት መክረዋል።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሠ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic