1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕአፍሪቃ

በአሸባሪነት የተከሰሱ ተጠርጣሪዎች የችሎት ውሎ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 17 2016

በዛሬው ችሎት ዐቃቤ ሕግ ክስ ማሻሻል ምስክሮችን ለጉዳት የሚዳርግ ነው በሚል ያንን ማድረግ እንደማይችል በጽሑፍ አቤቱታ አቅርቧል። የተከሳሽ ጠበቆችም በበኩላቸው በቃል ክርክር በማድረግ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ የተከሳሾችን ጥያቄ እንዲመልስ ተከራክረዋል።

https://p.dw.com/p/4fBV3
በአሸባሪነት ተጠርጥረዉ ክስ ከተመሰረተባቸዉ 51 ሰዎች መካከል ፍርድ ቤት የቀረቡት 23ቱ ናቸዉ
የኢትዮጵያ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለዉ ችሎቱ በአሸባሪነት የተከሰሱ ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ተመልክቷልምስል Seyoum Hailu/DW

በአሸባሪነት የተከሰሱ ተጠርጣሪዎች የችሎት ውሎ

አራት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ጨምሮ በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ በሽብር ወንጀል ክስ ከቀረበባቸው 51 ተከሳሾች መካከል 23ቱ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።የዛሬው ችሎት "ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ የመሠረተውን ክስ እንዲያሻሻል እና ያልቀረቡ ተከሳሾች ላይ በጋዜጣ የተደረገውን ጥሪ ውጤት ይዞ እንዲቀርብ" የተሰጠውን ትእዛዝ ለማድመጥ የተሰየመ ነበር። 

ተከሰሾች "በክሳችን ውስጥ የተገለፀውን የሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት ጉዳት በስም ዝርዝር" በመግለጽ ዐቃቤ ሕግ ያቅርብ" በሚል ያቀረቡት ጥያቄ "ምስክሮችን ለጉዳት የሚዳርግ ነው" በሚል ዐቃቤ ሕግ አቤቱታ አቅርቧል።ግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት ይህንን እና ችሎት ያልቀረቡ በጋዜጣ ጥሪ የተደረገላቸው ተከሳሾችን ጉዳይ ለማድመጥና ትእዛዝ ለመስጠት ለግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ . ም ቀጠሮ ሰጥቷል።//

 

በፌደራል ዐቃቤ ሕግ በሽብር ወንጀል ክስ የቀረበባቸው 51 ተከሳሾች የወንጀል ሕግ እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ከወጣው አዋጅ ድንጋጌዎችን በመጣስ "የፖለቲካ እና የርዕዮት አላማን ለማራማድ በማሰብ የሽብር ድርጊት ፈጽመዋል" በሚል በዐቃቤ ሕግ ክስ የቀረበባቸው ናቸው።በዶ/ር ወንደወሰን አሰፋ ስም በተያዘው መዝገብ ውስጥ 51 ግለሰቦች የተከሰሱ ቢሆኑም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት የሚከታተሉት 23ት ናቸው።

ከተከሳሽ ጠበቆች አንደኛው ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ የዛሬውን የችሎት ውሎ በስልክ ነግረውናል።"ዐቃቤ ሕግ ክሱን እንዲያሻሽል እና ባልቀረቡ ተከሳሾች ላይ የጋዜጣውን ጥሪ ውጤት ይዞ እንዲቀርብ ነበር"

በዛሬው ችሎትዐቃቤ ሕግ ክስ ማሻሻል ምስክሮችን ለጉዳት የሚዳርግ ነው በሚል ያንን ማድረግ እንደማይችል በጽሑፍ አቤቱታ አቅርቧል። የተከሳሽ ጠበቆችም በበኩላቸው በቃል ክርክር በማድረግ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ የተከሳሾችን ጥያቄ እንዲመልስ ተከራክረዋል።በዛሬው ችሎት ተከሳሾች በቁጥጥር ሥር ውለው በእሥር ላይ ከሆኑ አንድ ዓመት ማለፉ ተጠቅሶ ክርክር መደረጉንም ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ተናግረዋል።በቃሊቲ እና በቂሊንጦ ማረሚያ ቤቶች በእሥር ላይ ከሚገኙት ተከሳሾች መካከል በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ይሠሩ የነበሩት መስከረም አበራ፣ ጎበዜ ሲሳይ፣ ዳዊት በጋሻው እና ገነት አስማማው ይገኙበታል።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ