1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የአምስት ሰዎች መገደል

ረቡዕ፣ ሰኔ 5 2016

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ በተቀሰቀሰ ግጭት አምስት ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የሕዝብ ተመራጮች ለዶቼ ቬለ ገለጹ። ግጭቱ የተቀሰቀሰው የልዩ ወረዳው የፀጥታ አባላት የዘይሴ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓልን ለማክበር የተዘጋጁ ወጣቶችን ለመበተን መሞከራቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል።

https://p.dw.com/p/4gxdr
አርባ ምንጭ
አርባ ምንጭ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የአርባምንጩ ግድያ

የነዋሪዎችን ሕይወት የቀጠፈው የዳንብሌ ቀበሌ ግጭት

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ በተቀሰቀሰ ግጭት አምስት ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የሕዝብ ተመራጮች ለዶቼ ቬለ ገለጹ። ግጭቱ የተቀሰቀሰው የልዩ ወረዳው የፀጥታ አባላት የዘይሴ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓልን ለማክበር የተዘጋጁ ወጣቶችን  ለመበተን መሞከራቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል።

የሳንደለ አባት አሟሟት

በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የዛይሴ ዳንብሌ ቀበሌ ነዋሪ ለሆነችው ሳንደለ ሳፊዮ ያሳለፍነው ቅዳሜ ለእሷና ለተቀሩት የቤተሰብ አባላት ጥሩ ቀን የሆነ አይመስልም። ሳንደለ በዚሁ ቀን እንደማንኛውም የመንደሩ ነዋሪ በቀበሌው በተነሳው ግጭት ሰዎች መገደላቸውን ሰምታለች። ከሟቾቹ አንዱ ወላጅ አባቷ አቶ ሳፊዮ ሰላሙ መሆናቸውን ያወቀችው ግን ዘግይታ መሆኑን ነው ሳንደለ ለዶቼ ቬለ የገለጸችው።

በሰዓቱ አባቷ በትምህርት ቤት ውስጥ በጥበቃ ሥራቸው ላይ እንደነበሩ የተናገረችው ሳንደለ «ፖሊሶች ወደ ግቢው በመግባት መተኮስ ጀመሩ። በሥፍራው ከነበሩ ሰዎች እንደሰማሁት አባቴ ከፖሊሶች በተተኮሰ ጥይት ነው የተገደሉት። የቀብር ሥነሥረዓታቸውም እንደነገሩ ነው የተፈጸመው» ብላለች።

ግጭቱ መነሻ

የወረዳው ፖሊስ  አባላት ወደ ዳንብሌ ቀበሌ በሁለት አቅጣጫ በመግባት ተኩስ መክፈታቸውን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት ሁለት የአካባቢው ነዋሪዎች የግጭቱን መነሻ በመጥቀስ በሥም የሚያውቋቸው ሦስት ሰዎች መገደላቸው ገልጸዋል።

በቀበሌው የሚገኙ ወጣቶች ዮዎ ሱሩቄ የተባለውን የዛይሴ ብሔረሰብን አዲስ ዓመት ለማክበር ዝግጅት ላይ እንደነበሩ የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ «በዚህ መነሻነት መረጃው ደረሰን ያሉ የወረዳው ፖሊስ አባላት ወደ ቀበሌው በመግባት በበዓል ዝግጅት ውስጥ ወደ ነበሩት ሰዎች ተኩስ ሲከፍቱ ሁሉም መሮጥ ጀመረ» ነው ያሉት።

የዳንብሌ የሰላም ሁኔታ

አቶ አብርሃም ኦላሼ በአርባምንጭዙሪያ ወረዳ የዛይሴ ምርጫ ክልልን በመወከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ናቸው። ለዳንብሌ ግጭት የወረዳውን የፀጥታ አባላት ተጠያቂ ያደረጉት አቶ አብረሃም «ጥቃቱ የተፈጸመው አካባቢው ሰላም በሆነበት ሁኔታ ነው። የጥቃቱ ዋናው መነሻ በዓሉን አታከብሩም የሚል ነው። ወደ ግጭት የተገባውም ሆነ የሰው ሕይወት የጠፋው በዚሁ ምክንያት ነው። እስከ አሁንም አምስት ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጬያለሁ። ከግጭቱ በኋላ በቀበሌው መለስተኛ መረጋጋት ቢኖርም አሁንም ነዋሪው በሥጋት ውስጥ ይገኛል » ብለዋል።

ዶቼ ቬለ በልዩ ወረዳው ስለደረሰው ግጭትና ስለጠፋው የሰው ሕይወት አስመልክቶ የአርባ ምንጭ ዙሪያ  ወረዳንም ሆነ የጋሞ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያን ለማነጋገር ጥረት አድርጓል። ይሁንአንጂ የሥራ ሃላፊዎቹ ምላሽ ለመስጠት ፍላጎትም ፍቃደኝነትም ባለማሳየታቸው በዚህ ዘገባ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ