1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአራት ክልሎች ቀሪና ድጋሚ ምርጫ ከዘጠኝ የፓርላማ መቀመጫዎች ሰባቱን ብልጽግና ፓርቲ አሸነፈ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 29 2016

ገዢው ብልጽግና ፓርቲ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በአፋር እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ለዘጠኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች በተካሔደው ምርጫ ሰባቱን አሸነፈ። የጉምዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ እና የቦሮ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እያንዳንዳቸው አንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ማሸነፋቸውን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/4hxq4
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ
ከ108 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችም 97ቱን ብልጽግና ማሸነፉን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ዛሬ ቅዳሜ ገልፀዋል።ምስል Solomon Muchie/DW

በአራት ክልሎች በተደረገ ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ አብዛኛውን መቀመጫ አሸነፈ

በሦስት ክልሎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ በተደረገው ውድድር ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሁለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁለት መቀመጫ ያሸነፉ ሲሆን ቀሪ ሰባት የፓርላማ መቀጫዎችን ብልጽግና ፓርቲ አሸንፏል።

በፀጥታ መናጋትና በሰላም እጦት ምክንያት 6ኛው ዙር ምርጫ ሳይደረግባቸው በቀሩት እነዚህ አራት ክልሎች ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ. ም ለ 108 የክልል ምክር ቤቶች መቀመጫ በተደረገው ውድድር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሁለት ተፎካካሪ ፓርቲዎች 11 መቀመጫዎችን ሲያሸንፉ 97 መቀመጫዎችን ብልጽግና ፓርቲ አሸንፏል።

በውድድሩ ከተሳተፉት 12 ፓርቲዎች መካከል አብላጫውን ብልጽግና ያሸንፈ ሲሆን ጥቂት መቀመጫዎችን ያሸነፉት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ላይ የሚንቀሳቀሱት ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የጉሙዝ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብቻ ናቸው።
የምርጫው ውጤት 

ምርጫ ለማስፈፀም የፀጥታ ችግር የሌላለባቸው የተባሉት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ ሶማሌ እና ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ የተፈናቃይ የምርጫ ጣቢያዎችን ጨምሮ ምርጫ በተደረገባቸው 29 የምርጫ ክልሎች ለዘጠኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለ 108 የክልል ምክር ቤቶች ውድድር ተደርጓል። 

«6ኛው ዙር ድጋሚ እና ቀሪ ምርጫ በስኬት ተጠናቋል» ኢሰመኮ

ይህም ሆኖ ግን እንደገና የፀጥታ ሥጋት አለባቸው በተባሉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሦስት ማለትም አሶሳ፣ ካማሺ እና መተከል ዞኖች የፀጥታ ሁኔታ ዳሰሳ ከተደረገ በኋላ መተከል ዞን ውስጥ በነበሩ አምስት የምርጫ ክልሎች ተባሩን መፈፀም የሚያስችል ሰላም ባለመኖሩ 40 የምርጫ ጣቢያዎች ከምርጫው ሂደት ውጪ ሆነዋል።

የ6ኛው ዙር ቀሪ እና የድጋሚ ምርጫ ውጤት ማሳወቂያ
ባለፈው ሰኔ 16 ቀን 2016 በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የተካሔደው የ6ኛው ዙር ቀሪ እና የድጋሚ ምርጫ ነውምስል Solomon Muchie/DW

በውድድሩ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እንዲሁም የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አንድ አንድ የፓርላማ መቀመጫዎችን አሸንፈዋል።
በዚሁ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አራት፣ በአፋር ሁለቱንም መቀመጫዎች እንዲሁም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ አንድ መቀመጫን አሸንፏል።

6ኛው ዙር ቀሪና ድጋሚ ምርጫ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል

ከ108 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችም 97ቱን ብልጽግና ማሸነፉን የብሔራዊ ምርጫ ቤርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ዛሬ ቅዳሜ ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንን ውጤት ከሁለት ቀናት አስቀድሞ ማሳወቅ እንደነበረበት ገልፆ፣ ሆኖም ምርጫ ከተካሄደባቸው ጣቢያዎች መካከል በ150 ዎቹ ላይ ገዢው ፓርቲ አቤቱታ በማቅረቡ በሁለት ቀን መዘግየቱን አስታውቋል። ለመምረጥ ከተመዘገቡት 901 ሺህ ዜጎች መካከል 766 ሺህ ያህሉ ድምፃቸውን ይበጀናል ላሉት መስጠታቸውንም ቦርዱ ይፋ አድርጓል።

በዚህ የሥራ ሂደት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሦስት የምርጫ አስፈፃሚዎች በታጣቂዎች ታግተው እንደነበር ቦርዱ የገጠመውን ችግር ሲገልፁ አቶ ውብሸት አየለ ተናግረዋል። በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ፤ ምርጫው ከተደረገባቸው አራት ክልሎች በተጨማሪ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎችም ምርጫ ያልተደረገባቸው ሥፍራዎች አሉ። ቦርዱ እነዚህን ቦታዎች በተመለከተ ሰላም ወይም አስቻይ ሁኔታ ሲኖር ሕግና ሥርዓትን ጠብቆ ምርጫ እንደሚያከናውን አስቀድሞ አስታውቋል።

ሰለሞን ሙጬ 
እሸቴ በቀለ