በአምቦ፣ ወልዲያ አድማ ቀጥሏል | ኢትዮጵያ | DW | 08.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በአምቦ፣ ወልዲያ አድማ ቀጥሏል

በኦሮሚያ ክልል አምቦ ትላንት የተጀመረው የአገልግሎት መስጠት  አድማ ዛሬም ቀጥሎ መዋሉን የከተማው ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ በአማራ ክልል ወልዲያ ከተማ ተዘግተው የነበሩ ሱቆች ዛሬም አለመከፈታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:53

መንስኤው የግብር ጭማሪና የእስረኞች አያያዝ ነው ተብሏል

በመንግስት ላይ የሚሰነዘሩ ተቃውሞዎችን በማስተናገድ በምትታወቀው አምቦ ሱቆች እና የንግድ ተቋማት መዘጋታቸውን፣ የባጃጅ ታክሲዎችም በመንገዶች ላይ እንደማይታዩ የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ ዛሬ በከተማይቱ ስላለው ሁኔታ ቤተሰባቸውን ለመጠየቅ ወደ አምቦ ያቀኑ ግለሰብን ጠይቀናቸው ነበር፡፡

ፈራ ተባ እያሉ ተከታዩን አጭር ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ “ያለው ነገር ልክ እንደ ትላንቱ ነው፡፡ ሱቅም እንደተዘጋ ነው፡፡ ምንም ትራንስፖርት የለም፡፡ ሰው በእግር ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ቤት ነው ያለሁት፡፡ ምንም እንቅስቃሴ ስለሌለ የምወጣበት ምክንያት የለም” ብለዋል፡፡ 

የእኚህን ግለሰብ አስተያየት ሌላ አንድ የአምቦ ነዋሪም ያጠናክራሉ፡፡ ለአድማው መንስኤ ነው ሲባል የሰሙትንም ያስረዳሉ፡፡ “ዛሬም ትላንት በነበረው በተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደቆመ ነው፡፡ ሱቆችም ማንኛውም አገልግሎት ሰጪ ተቋም ዝግ ነው ዛሬ፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና በእስር ላይ እየደረሳባቸው ያለው በደል ይቁም ወይም ከእስር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈቱ የሚል መረጃ አለ፡፡ በሰሚ ሰሚ ማለት ነው፡፡ ሌላው ግን ግብር ክልክ በላይ የተጫነባቸው የነጋዴው ማህብረሰብ መፍትሄ እስከምናገኝ በሚል ሁኔታ ነው” ሲሉ ነዋሪው ያብራራሉ፡፡

በአምቦ ከተማ የፌደራል ፖሊስ እና የክልሉ ልዩ ኃይል አባላትን መመልከት የተለመደ እንደሆነ የሚናገሩት የአምቦው ነዋሪ ትላንት እና ዛሬ ግን አካባቢውን የሚቃኙ የጸጥታ ኃይሎች ከላይ ታች ሲመላለሱ መዋላቸውን ያስረዳሉ፡፡ ትላንት የተጀመረው የአምቦው አድማ በማን እንደተጠራ በግልጽ ባይታወቅም እስከ 15 ቀን ሊቀጥል እንደሚችል ወሬ መስማታቸውን አንድ ከአዲስ አበባ ወደ አምቦ ለስራ የተጓዙ ግለሰብ ትላንት ለዶይቼ ቬለ ተናግረው ነበር፡፡ የሚያድሩበት ቢያገኙም ምግብ ለማግኘት ግን ተቸግሬ ነበር ብለዋል፡፡ 

ለአምቦው አድማ የግብር ጭማሪ እንደ አንድ መንስኤ እንደቀረበ ሁሉ በአማራ ክልሏ ወልዲያም በተመሳሳይ ምክንያት ሱቆች ለሁለተኛ ቀን ተዘግተው ውለዋል፡፡ ከአምቦው በተለየ በወልዲያ የህዝብ መጓጓዣዎች ስራ ላይ ነበሩ፡፡ ሌሎች አገልግሎት መስጪያዎች ክፍት እንደነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ 

Symbolbild Schloss Tür Versperrt Vorhängeschloss Holztor

ሞሃመድ ፈንታ የተባሉ የወልዲያ ነዋሪ ስለ ዛሬ የከተማይቱ ውሎ ተከታዩን ተናግረዋል፡፡ “ከተማይቱ ሙሉውን ተዘግታለች፡፡ ሱቆች በሙሉ ተዘግተዋል፡፡ ወደ ውጭ ያሉት ቦታዎች ናቸው እንጂ ሁሉም ተዘግተዋል፡፡  መናኸሪያ፣ ፒያሳ ያሉት ሱቆች በሙሉ ዝግ ናቸው፡፡ አዲያቦ አከባቢ ማከፋፈያው ተዘግቷል፡፡ ምክንያቱ ግብር ያለአቅም ጥለውብን ነው፡፡ ያንን መክፈል ያለመቻል ችግር ነው” ብለዋል፡፡  

ስማቸው እንዳይጠቀስ የሚፈልጉ ሌላ የወልዲያ ነዋሪ ዛሬ በከተማይቱ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ታስቦ ሁሉ ነበር ይላሉ፡፡ ሱቆች የተዘጉት እና ሰልፍም የተጠራው በጓደኛ በኩል መልዕክት በመለዋወጥ እና በመደዋወል እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

“በሳምንት አንድ ቀን ማክሰኞ ገበያ አለ እና ዛሬ ገበያ አይኖርም ተብሎ ነበር፡፡ ያው እንደ ድሮ አይደለም የተቀዛቀዘ ነው፡፡ በመርሳ ደግሞ ቅዳሜ ዕለት ገበያ አልተዋለም፡፡ ዛሬ የሳምንት ገበያ አለ ወልዲያ፡፡ እርሱም ተቀዛቅዟል፡፡ እንደውም ሰልፍ ሁሉ ይወጣል እየተባለ ነበር እርሱ እርሱ ቀርቷል፡፡ አላግባብ ግብር ተጨምሮብናል፡፡ ማመልከቻም ስናስገባ የሚሰጠን ምላሽ ጥሩ አይደለም [የሚል ነው]፡፡ ቢያንስ ከተጣለባችሁ ግብር 50 በመቶውን ክፈሉ እና ከዚያ ቀስ እያለ ይታይላችኋል የሚሉ ነጋዴ እንሰማለን፡፡ እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴ ነው ያለውና ጥሩ ድባብ አይደለም የሚታየው ነገር” ሲሉ በከተማይቱ የታዘቡትን ያስረዳሉ፡፡   

ለዶይቼ ቬለ የደረሰ አንድ ደብዳቤ እንደሚያሳየው የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ሱቃቸውን ለዘጉ ነጋዴዎች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሰጥቷል፡፡ አስተዳደሩ በክትትል ደረስኩባቸው ላላቸው ነጋዴዎች በሰጠው በዚሁ ደብዳቤ በተሰጣቸው ፍቃድ ለሸማቹ አገልግሎት የማይሰጡ ከሆነ የንግድ ፍቃዳቸውን እንደሚሰረዝ እና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ ያስጠነቅቃል፡፡   

በአምቦ ስላለው አድማ ከኦሮሚያ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡ በወልዲያ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ የአካባቢውን አስተዳደር ምላሽ ለማካተት ወደ ሰሜን ወሎ ዞን የጸጥታ እና አስተዳደር መምሪያ ብንደውልም ኃላፊው አቶ አደራው ጸዳሉ ስልጠና ላይ ናቸው ተብለናል፡፡ ተወካያቸው እኛን ለማነጋገር ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic