1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአምቦ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ፤ ጊንጪ ተቃውሞ ነበር

ቅዳሜ፣ የካቲት 24 2010

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ትናንት ማጽደቁን ተከትሎ በአምቦ እና ጊንጪ ከተሞች ተቃውሞ መቀስቀሱን ነዋሪዎች ተናገሩ። አንድ የአምቦ ከተማ ነዋሪ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጠናል ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

https://p.dw.com/p/2tdnY
Äthiopien Proteste | Ambo Town
ምስል DW/M. Yonas Bula

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ትናንት ማጽደቁን ተከትሎ በአምቦ እና ጊንጪ ከተሞች ተቃውሞ መቀስቀሱን ነዋሪዎች ተናገሩ። የአዋጁ መፅደቅ ከተሰማ በኋላ ወጣቶች እና የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች አደባባይ መውጣታቸውን የተናገሩ የአይን እማኝ መንገድ መዘጋቱን፣ አንድ ተሽከርካሪ መቃጠሉንም ተናግረዋል። ከምሽቱ አንድ ሰዓት ገደማ የጸጥታ አስከባሪዎች ከሁለት አቅጣጫዎች ወደ አምቦ ከተማ መግባታቸውንም አክለው ገልጸዋል። ተቃውሞው ቅዳሜ ጠዋት ቀጥሎ እንደነበር የሚናገሩት የአይን እማኙ "የመሣሪያ ተኩስ በየደቂቃው እንሰማለን" ብለዋል። "የሞቱ ሰዎች አሉ" የሚል ወሬ መስማታቸውንም ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

"በረንዳ ላይ ስቆም እንኳ መከላከያዎች ግባ ብለውኛል" የሚሉት የአምቦ ነዋሪ "በብዙ መከላከያ ተከበናል" ሲሉ አክለዋል። በጥይት የተመታ ጓደኛቸው መንቀሳቀስ እንደማይችልም ተናግረዋል። "አራዳ የሚባል ሰፈር አለ። ወደ ውስጥ ገባ ያለ ነው።  06 ቀበሌ ምናምን። እዛ ነው ሶስት ሰው ተገደለ መባሉን የሰማሁት" ከአምቦ ወደ ጉደር መውጫ ላይ አባት እና ልጅ በጥይት መመታታቸውንም አስረድተዋል። "አባት ሞተዋል፤ ልጅ ደግሞ እየተጠበቀ ነው" ሲባል መስማታቸውን አስረድተዋል።

ሌላ የአምቦ ከተማ ነዋሪ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጠናል ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። "እኛንም አባረውን ነው ሸሽተን የገባንው። በጣም እየተኮሱ ነው። ወደ ልጆች ነው የሚተኩሱት። እንደ በፊቱ ወደ ላይ እንኳ አይተኩሱም። ደዋውለን እንደሰማንው ከሆነ በየቦታው ሰዎች እየሞቱ ነው። ከዛ ውጪ በአይኔ አላየሁም። እስካሁን ያረጋገጥንው የሞተ ሰው ሶስት ነው። በተለይ አራዳ የሚባለው አካባቢ ሁለት ሰው ሞቷል አሉ። እንደዚሁም 05 አንድ ሰው ሞቷል። እስካሁን የተረጋገጠው ሶስት ሰው ነው" ሲሉ ተናግረዋል። 

ሁለቱም የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች አንድ የመከላከያ መኪና እንደተቃጠለ ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ በከተማዋ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን፣ የባንኮች፣ መገበያያ ሱቆች እና የሕዝብ ማጓጓዣ አገልግሎቶችም አለመኖራቸውን ገልጸዋል።

በትናንትናው ዕለት በጊንጪ ከተማም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚቃወም ሰልፍ እንደነበር አንድ የከተማይቱ ነዋሪ ተናግረዋል። ነዋሪው እንደሚሉት ከአዲስ አበባ 75 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው የጊንጪ ከተማ ተሽከርካሪ ተቃጥሏል። የጊንጪው ተቃውሞ በትናንትናው ዕለት 10 ሰዓት አካባቢ ጀምሯል የሚሉት ነዋሪ "ኮማንድ ፖስቶች የሚያርፉበት ቦታ ተቃጥሏል። አራት ቁጥር የመንግሥት መኪና ተገኝታ መግቢያው አካባቢ ተቃጥላለች" ሲሉ አስረድተዋል። የጊንጪው ነዋሪ እንደተናገሩት ተቃዋሚዎች "ከዚህም በፊት ተቀብለን የደረሰብን ነገር ስላለ ኮማንድ ፖስት አንቀበልም" ብለዋል። "ተኩስ ነበረ። ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ ነበር። መንገድ ላይ ሰው እየቀጠቀጡ ነው ያሉት። ማንም የሚንቀሳቀስ የለም። እርግብ እንኳ አይታይም። እኔ ራሱ መውጣት አልችልም" ሲሉ ዛሬ የነበረውን የከተማዋ ድባብ አስረድተዋል። የከተማዋ እንቅስቃሴ እጅግ መቀዛቀዙን የተናገሩት የጊንጪው ነዋሪ የጸጥታ አስከባሪዎች በብዛት እንደሚታዩ ገልጸዋል። በከተማዋ የተኩስ ድምፅ ቢሰማም የሞተም ሆነ የቆሰለ አለመኖሩንም ተናግረዋል። 

ስለ ትላንቱም ሆነ የዛሬው ተቃውሞ የአምቦ ከተማ አስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። የኢትዮጵያ መንግሥት የደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ88 የተቃውሞ እና ሰባት ድምጸ ተዐቅቦ በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው በትናንትናው ዕለት መሆኑ አይዘነጋም። የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ አዋጁ በ346 የድጋፍ ድምፅ መፅደቁን በስብሰባው ማጠናቀቂያ ተናግረው የነበረ ቢሆንም ቆየት ብሎ ከምክር ቤቱ የወጣ መረጃ አዋጁን የደገፉ አባላትን ቁጥር 395 አድርሶታል። 

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ