በአምቦ፤ዶዶላ እና ሻሸመኔ ተቃውሞ ተደረገ | ኢትዮጵያ | DW | 11.10.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በአምቦ፤ዶዶላ እና ሻሸመኔ ተቃውሞ ተደረገ

በአምቦ፤ ዶዶላ እና ሻሸመኔ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ተደረጉ። የዓይን እማኞች "በሰላም ተጠናቋል" ባሉት የአምቦ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላ ትችት ተሰንዝሮበታል። በዶዶላ ከተማ በተደረገ ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች የባለቤትነት ጥያቄ መነሳቱን የከተማዋ ነዋሪ ተናግረዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:51

በዶዶላ የጸጥታ ኃይሎች ጭምር በተቃውሞ ተካፍለዋል

ከአዲስ አበባ በ126 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው የአምቦ ከተማ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ነዋሪዎች የኢትዮጵያ መንግሥትን ተችተዋል። የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፤ የመንግሥት ሠራተኞች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተቃውሞው ትልቅ ነበር ሲሉ ለዶይቸ ቬለ አረጋግጠዋል። የዓይን እማኞች እንደሚሉት ዛሬ ጠዋት 4 ሰዓት አካባቢ የጀመረው ተቃውሞ እስከ ስድስት ሰዓት ዘልቋል። በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ኦሮሞ ሊዋሐድ ይገባል የሚሉ ጥሪዎች ተደምጠዋል የሚሉት የከተማዋ ነዋሪ መንግሥት ይውረድ የሚል መፈክርም ተደምጧል ብለዋል። 

"በቃ ሕብረተሰቡ በሙሉ ማለት እንችላለን ከተማው አልቀረም ጫፍ እስከ ጫፍ ብዙ ነበረ። ደስ የሚል ነበረ። በሰላም ነው የተጠናቀቀው። መፈክሮች ወያኔ ይጥፋ፤ ወያኔ ይብቃን ካሁን በኋላ ኢሕአዴግ አይግዛን ኦሮሞ ራሳችንን እናስተዳድራለን ነው።"

የተቃውሞ ሰልፉ እንደ ከዚህ ቀደሙ በወጣቶች ብቻ ሳይሆን መላ የከተማዋን ነዋሪዎች አካቷል የሚሉት ሌላኛዉ የአምቦ ነዋሪ ለሁለት ሰዓት መካሔዱን ተናግረዋል። የተቃውሞ ሰልፈኞች የመብት ጥያቄዎችን ጠይቀዋል የሚሉት የዓይን እማኙ በአካባቢው የነበሩት አድማ በታኝ ፖሊሶች ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዳቸውን ተናግረዋል። በአምቦው ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፈኞች ፋብሪካ መነቀል የለበትም፤ ዜጎች ከሶማሌ ክልል ሊፈናቀሉ አይገባም የሚሉ መፈክሮች ማሰማታቸውን የከተማዋ ነዋሪ ነኝ ያሉ ግለሰብ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

የዛሬው የተቃውሞ ሰልፍ ከአምቦ ባሻገር ሻሸመኔ እና ዶዶላን በመሳሰሉ አካባቢዎችም ተደርጓል። የዶዶላው ነዋሪ አቶ አህመድ መሐመድ እንደታዘቡት ከቀኑ ሰባት ሰዓት ገደማ የተጀመረው የተቃውሞ ሰልፍ ከወትሮው በተለየ አመራሮች እና የጸጥታ ኃይሎች ጭምር የተሳተፉበት ወጥነትም የነበረው ነው።  

 በዶዶላው ተቃውሞ በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራሮች ይፈቱ ከሚለው ጥያቄ ባሻገር የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ የባለቤትነት ጥያቄ ተነስቷል ሲሉ የዓይን እማኙ አክለዉ ነግረውናል።
በሻሸመኔ ከተማ በተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ አንድ የተመታ ሰው አለ የሚል መረጃ ቢኖርም ለማረጋገጥ ሳንችል ቀርተናል። የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኃላፊዎችም በተደጋጋሚ ያደረግናቸዉን የስልክ ጥሪዎች አልመልሱም።  

 
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic