1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል ጦርነት እና ግጭት ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ማውደሙ ተገለጸ

ሐሙስ፣ ግንቦት 24 2015

በአማራ ክልል ጦርነት እና ግጭት በንብረት ላይ ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሱን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ። በአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ፈንድ ጽህፈት ቤት ያከናወነውን ጥናት ጠቅሰው ኃላፊው ዶክተር አባተ ጌታሁን እንዳሉት በክልሉ በጦርነት እና በግጭት 522 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ጠፍቷል

https://p.dw.com/p/4S4Lu
Äthiopien | Rehabilitations- und Wiederaufbaufond
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል ጦርነት እና ግጭት ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ማውደሙ ተገለጸ

የአማራ ክልል መንግስት ሁለተኛው የጦርነት ጊዜ እየተባለ እስከሚጠራው ታህሳስ 2014 ዓ ም ድረስ በክልሉ የደረሰውን ቁሳሳዊ ውድመት አስጠንቶ በወቅቱ 294 ቢሊዮን ብር የሚገመት  ውድመት መድረሱን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡  ጦርነቱ  በክልሉ ያደረሰውን ውድመት እንዲከታተልና መልሶ የማቋቋም ተግባር እንዲያከናውን ኃላፊነት ተሰጥቶት ባለፈው ዓመት የተመሰረተው በአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽ/ቤት  ለሁለተኛ ጊዜ ያስጠናው አጠቃላይ ጥናት ግን ውድመቱ ወደ ከግማሽ ትሪሊዮን ብር መድረሱን የጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አባተ ጌታሁን ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡ 

የአማራ ክልል የ2015  ዓመት አጠቃላይ በጀት ከ100 ቢሊዮን ያነሰ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ጦርነቱ በፈጠረው ጦስ እስካሁንም ግማሽ የሚሆነው የክልሉ ህዝብ በችግር ላይ እንደሆነ ነው ዶ/ር አባተ የሚያስረዱት፡፡ የክልሉ መንግስት ካለው በጀት አብቃቅቶ በመደበው አንድ ቢሊዮን ብር የመልሶ ማቋቋም ስራዎችና የተቋማት ግንባታዎች እየተካሄዱ እንደሆነም ዋና ሥራ አስኪያጁ አብራርተዋል፡፡
በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያዊ ክልልን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት እንዲረባረቡ ዶ/ር አባተ ጠይቀዋል፡፡

በአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽ/ቤት
በአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽ/ቤትምስል Alemnew Mekonnen/DW

የተቋማት ግንባታ ከተጀመረባቸው አካባቢዎች መካከል በሰሜን ወሎ ዞን የወርቄ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ይማም መሀመድ የተጀመሩ የትምህርት ቤትና የጤና ተቋቋም እየተፋጠነ እንደሆነ መስክረዋል፡፡
የወርቄ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ በካሪስ ጎቤም በቀበሌያቸው የተጀመሩ የመልሶ ግንባታ ስራዎች ከ85 ከመቶ በላይ መድረሳቸውን መረዳታቸውን ገልፀዋል፡፡ 

“ትናንትና ሄጀ ነበረ፣ ስጠይቅ ከ85 ከመቶ በላይ ናቸው ሁሉም፣ አራት  የምርመራ ክፍል ያለው ጤና ጣቢያ፣ አንድ ካርድ ክፍል ፣ ደረጃውን የጠበቀ የገበሬ ማሰልጠኛ፣ የእንስሳት ክሊኒክ፣ አራት የመማሪያ ክፍሎችና አዳራሽ፣ በሶስት ቦታዎች ላይ እየተገነቡ ናቸው ፡፡” የኢትዮጵያ መንግስት ከህወሓት ጋር በነበረው ጦርነት ከአማራ ክልል በተጨማሪ በአፋርና በትግራይ ክልሎችም ተመሳሳይ የቁሳዊ፣ የሰብአዊና የማህበራዊ ጉዳቶች መድረሳቸው አይዘነጋም፡፡

ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ