1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«በአማራ ክልል የፀጥታ ችግር ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምሕርት ቤት አይሄዱም»

ሐሙስ፣ ሰኔ 20 2016

የትምሕርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ በአማራ ክልል የፀጥታ ችግር ምክንያት በ2016 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ብቻ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ባለመመዝገባቸው ትምህርት ቤት አለመግባታቸውን ከ3ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች አለመከፈታቸውን ተናግረዋል።በሰሜኑ ጦርነት ወቅትም በትምህርቱ ዘርፍ ከፍተኛ ጉዳቶች ተመዝግበዋል” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4hXew
የሰላምና የትምሕርት ጉባኤ በባህር ዳር
የሰላምና የትምሕርት ጉባኤ በባህር ዳርምስል Alemnew Mekonnen/DW

«በአማራ ክልል የፀጥታ ችግር ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምሕርት ቤት አይሄዱም»

በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ 50ሺህ ያክል ትምህርት ቤቶች አብዛኛዎቹ የትምህርት መሰረተ ልማትና ግብዓት እንደሌላቸው የኢፌድሪ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፣ በአማራ ክልል ደግሞ በክልሉ ባለው የፀጥታ እጦት 3ሺህ ትምህርት ቤቶች በዚህ ዓመት አልተከፈቱም ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት አልገቡም ተብሏል፡፡
የአማራ ክልል የትምህርት ቢሮ ያዘጋጀው የትምህርት ንቅናቄ መድረክ ዛሬ በባሕር ዳር ሲጀመር የተገኙት የኢፌድሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ ባለፉት ዓመታት አገሪቱ  በተደራሽነትና በፍትሐዊነት የተሻሉ ውጤቶች ቢመዘገቡም፣  የትምህርት ጥራት ግን በተለያዩ ምክንያቶች ማሽቆልቆሉን ተናግረዋል፡፡ የተነሳሽነት ማነስ፣ በትምህርት  ቤቶች ምቹ የትምርት አካባቢ አለመኖርና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለትምህርት ጥራት ውድቀት ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ግጭት ባለባቸው የሰሜን ጎጃም እና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ለብሔራዊ ፈተና አይቀመጡም


ከዚህ በተጨማሪም የትምህርት ቤቶች የመሰረተ ልማት መጓደል ሌላው ተጠቃሽ ምክንያት መሆኑን ነው የጠቀሱት፡፡“በሀገራችን ከ50ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ የመማር ማስተማር መሰረተ ልማቶች የሌሏቸው በመሆኑ ተማሪዎች በተጓደለ የትምህርት ሁኔታ ውስጥ እንዲማሩ ተደርጓል፣ ይህ ደግሞ በትምህርት ትራት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ይህን ችግር ለማሻሻልና ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ማህበረሰቡና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ባለፈው ዓመት ትምህርት ለትውልድ በሚል የትምህርት ንቅናቄ በመፍጠር በአጠቃላይ እንደሀገር 25 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ ትምህርት ቤቶች እንዲገነቡና የተጎዱ ትምህርት ቤቶች እንዲጠገኑ ተደርጓል፡፡” ብለዋል፡፡የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉነሽ ደሴ በበኩላቸው፣ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በአማራ ክልል ባለው የፀጥታ ችግር በርካታ ትምህርት ቤቶች ሥራ ያቆሙ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ደግሞ ከትምህርት ገበታ ተለይተዋል ነው ያሉት፡፡

ወይዘሮ አየለች እሸቴ የትምሕርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ
ወይዘሮ አየለች እሸቴ የትምሕርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ ምስል Alemnew Mekonnen/DW

“በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በ2016 ዓ ም የትምህርት ዘመን ብቻ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ባለመመዝገባቸው ወደ ትምህርት ቤት አልገቡም፣ ከ3000 በላይ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች አልተከፈቱም፣ ትምህርት በጀመሩ ተማሪዎችና መምህራን ላም ከፍተኛ ጫናና መዋከብ ደርሷል፡፡ በሰሜኑ ጦርነት ወቅትም በትምህርቱ ዘርፍ ከፍተኛ ጉዳቶች ተመዝግበዋል” ሲሉ ገልፀዋል፡፡በምስራቅ ጎጃም ዞን ፈረስ ቤት ከተማ ነዋሪ የሆኑ ወላጅ በዚህ ዓመት ትምህርት በመቋረጡ ልጃቸው አንድ ዓመት ያለምንም ትምህርት ማሳለፏን ጠቁመው ቀጣዩንም ለመገመት መቸገራቸውን አመልክተዋል፡፡ስማቸውና ያሉበት አካባቢ እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የምዕራብ ጎጃም ዞን ነዋሪ መምህር የሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት የተማሪዎች ኮምፒዩተር ክፍል

በከባድ መሳሪያ ተመትቶ መውደሙን ጠቁመው፣ ትምህርት በመቆሙ ደግሞ በርካታ ተማሪዎች ወደ ትዳር እየገቡ ነው ብለዋል፡፡“የትምህርት ቤቱ የቤተ ሙከራ ኮምፒዩተሮች በከባድ መሳሪያ ተመትተው ወድመዋል፣ በህይወቴ ትምህርት ቤት ተዘግቶ፣ ተማሪና መምህራን አልባሌ ቦታ ሲውሉ ያየሁበት ጊዜ አሁን ነው፣ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ገጠር ተማሪዎች ናቸው፣ ትምህርት በመቆሙ 60 ከመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ወደ ትዳር እየገቡ ነው፡፡

ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ የአማራ ክልል ትምሕርት ቢሮ ኃላፊ
ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ የአማራ ክልል ትምሕርት ቢሮ ኃላፊምስል Alemnew Mekonnen/DW

”በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፣ ተመራማሪና ችግር ፈቺ የሆነ ትውልድ ለማፍራት በሚደረገው እርብርብ  የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ሁሉም ባለድርሻ አካል በትምህርቱ ዘርፍ ውጤት ያለው ስራ እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡
በአማራ ክልል በዚህ ዓመት በተሰጠው የ6ኛና 8ኛ ክፍል አጠቃላይ ፈተና ባለው የፀጥታ ችግር ምክንት በምዕራብ ጎጃምና ምስራቅ ጎጀም ተማሪዎች ፈተና እንዳልወሰዱ ቀደም ሲል የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉነሽ ደሴ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ