በአማራ ክልል የሚደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ቀጥሏል | ኢትዮጵያ | DW | 24.04.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በአማራ ክልል የሚደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ቀጥሏል

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በአማራ ክልል ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለው ሞትና መፈናቀል እንዲቆም የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ ተካሂዷል። ሰልፈኞቹ መንግሥት ለንፁሐን ጥበቃ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። አንዳንድ ሰልፈኞች ሀዘናችንን ይገልፃል ያሉትን ጥቁር ባንዲራ መያዛቸውም ተመልክቷል፡፡

ተቃውሞ ሰልፍ በሰቆጣ ከተማ

በኦሮሚያ ወለጋ የተለያዩ ዞኖች፣ በሰሜን ሸዋና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ ወረዳዎች፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ ኢትዮጰያ ጉራፈርዳና በሌሎችም አካባቢዎች ማንነትን መሠረት ባደረጉ ጥቃቶች በርካቶች ህይወታቸው አልፏል፣ ሀብት ንብረታቸው ተዘርፎ፣ ተቃጥሎና ወድሞ ተፈናቅለዋል፡፡ ለዓመታት ያፈሩትን ሀብት ጥለው ከሚኖሩበት ከተፈናቀሉ ወገኖች መካከል አንዳንዶቹ በቅርቡ ለዶይቼ ቬለ DW ተናግረው ነበር፡፡
በአጠቃላይ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ሞት፣ መፈናቀልና ወከባ በመቃወም በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ የተቃዉሞ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው፡፡ ዛሬም ግድያና መፈናቀል እንዲቆም የሚጠይቅ ሰልፍ በሰቆጣ ከተማ ተካሂዷል፡፡ ከሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል አቶ ሀብታሙ መንግስቴ “እየተገደልን ያለነው በአፀደቅነው ህገመንግሰት ነው” ይላሉ የሰልፉን ዓላማ በተመለከተም ለዶይቼ ቬለ ገልፀዋል፡፡ሌላው በሰልፉ ላይ የነበሩ አስተያየት ሰጪ እንዳሉት በግፍ ለተገደሉና ለተፈናቀሉ ድምፅ ለመሆን በሰልፉ ላይ መገኘታቸውን አብራርተዋል፡፡
በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በንፁሀን ላይ የሚደርሰውን መሰደድ መንግስት እንዲያስቆም ለመጠየቅ የተዘጋጀ ሰልፍ እንደሆነ ደግሞ አቶ መብራቱ መኮንን አመልክተዋል፡፡
በሰልፉ የተለያዩ መልዕክቶች መተላለፋቸውን የተናገሩት አቶ መብራቱ አንዳንድ ሰልፈኞች ሀዘናቸውን ለመግለፅ ጥቁር ባንዲራ ይዘው መታየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከባለፈው ማክሰኞ ጀምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በአማራ ተወላጆችና በሌሎችም ንፁሀን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ግድያ፣ የአካል ጉዳትና መፈናቀል በመቃወም ሰልፎች በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ተካሂደዋል።


ዓለምነው መኮንን

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic