1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየተሰራ ነው ተባለ

እሑድ፣ መጋቢት 22 2016

በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች በየወቅቱ የሚነሱ ግጭቶች ከአስተዳደር ቁርጠኝነት ማነስና ከአመራር ክፍተቶች የሚፈጠሩ እንደሆኑ የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታውቋል። ሰሞኑን በአካባቢው የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት በግጭቶቹ መንስኤዎች ላይ ከሁለቱም ዞኖች ጋር ውይይቶ እየተካሄዱ ነው ተብሏል።

https://p.dw.com/p/4eINK
የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ፤ባህርዳር
የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ፤ባህርዳርምስል Aleminew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች የፀጥታ ሁኔታ

 

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር በየወቅቱ የሚነሱ ግጭቶች ከአስተዳደር ቁርጠኝነት ማነስና ከአመራር ክፍተቶች የሚፈጠሩ እንደሆኑ የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ  ቢሮ አስታውቋል፣  ሰሞኑን በአካባቢው የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት በግጭቶቹ መንስኤዎች ላይ ከሁለቱም ዞኖች ጋር ውይይቶ እየተካሄዱ እንደሆነም ታውቋል፡፡

ሰሞኑን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አዋሳኝ አካባቢዎች ሞትን ያስከተሉ ግጭቶች ነበሩ፣ በተለይ በአጣየ ከተማና አካባቢው ከፍተኛ ውጊያ እንደነበር የከተማዋ ነዋሪዎች ሲገልፁ ሰንብተዋል፡፡

በሁለቱ ዞኖች አዋሳኝ ወረዳዎች ተደጋጋሚ ግጭቶች ይስተዋላሉ፡፡ ችግሮቹ  በአካባቢዎቹ የሚከሰቱት ከአመራር ቁርጠኝነት ማነስና  ከአስተዳደር ክፍተቶች መሆኑን የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ለጋዜጠኞች  መግለጫ በሰጡበት ወቅት ከዶይቼ ቬሌ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

 አቶ ደሳለኝ ጣሰው፤ የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ
አቶ ደሳለኝ ጣሰው፤ የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊምስል Aleminew Mekonnen/DW

የችግሮቹን ምንጭ ተረድቶ ዘላቂ ሰላም በአካባቢዎቹ ለማስፈን የሁለቱም አዋሳኝ ዞን አስተዳደር ነዋሪዎችና አመራሩ ቀናትን የወሰደ ውይይት ማድረጋቸውን ነው ኃላፊው ስረዱት፡፡
ህዝባዊነት የተላበሰና የአካባቢ ነዋሪዎችን ሰላም ለማስፈን የሚያስችል አመራር ለመገንባት እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋለ፤፡፡
የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አሊ መሐመድ በበኩላቸው ከህብረተሰቡና በተዋረድ ካለው አመራር ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በኬሚሴ ከተማ ውይይት መደረጉን ጠቅሰው አሁን የፀጥታ ችግሮች የነበሩባቸው አካባቢዎች የተሻለ የፀጥታ ሁኔታ እንዳለ አመልክተዋል፡፡የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና ሰሜን ሸዋ አዋሳኝ ግጭት

አንድ የአጣየ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው በተመሳሳይ ከህብረተሰቡ ጋር ውይይቶች በአጣየ ከተማ ሰሞኑን መካሄዳቸውን ገልጠዋል፣ ሆኖም አሁንም በሁለቱም ዞን ነዋሪዎች መካከል ፀጥታው ሊደፈርስ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ተናግረዋል፣ በአጣየ ከተማ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ባይመለሱም፣ ካለፈው ሳምንት ሲነፃፀር የተሻለ ሰላም ሁኔታ መኖሩን አስረድተዋል፣ ባንኮችና ሌሎችም ተቋማት ከሰኞ ጀምሮ ስራ እንደሚጀምሮ መገለጹን መስማታቸውንም ነግረውናል፡፡
ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ በአጣየና ዙሪያውና ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አንዳንድ ቦታዎች በነበረው ግጭት የሰዎች ህይወት አልፏል፣ ንብረት ወድሟል፣ ብዙዎችም ከቀያቸው ተፈናቅለው ሰንብተዋል፡፡

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ዓለምነው መኮንን

ፀሀይ ጫኔ