1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል በጤናው ዘርፍ የሠው ኃይል፣በትምህርቱ ደግሞ የተማሪ ቁጥር ማነስ አጋጥሟል

ቅዳሜ፣ ኅዳር 21 2017

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መልካሙ ጌትነት ከወቅታዊ የክልሉ የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞም በርካታ ጤና ተቋማት መዘጋታቸውንና ሠራተኞች በስራ ገበታቸው ላይ እንዳልሆኑ አስረድተዋል።

https://p.dw.com/p/4nbQk
በተለይ በጤናው ዘርፍ ከሚጠበቀው የሰው ኃይል አኳያ 45 ከመቶ የሰው ኃይል ጉድለት መኖሩን የቢሮው የምክትል ኃላፊ አመልክተዋል
በተለይ በጤናው ዘርፍ ከሚጠበቀው የሰው ኃይል አኳያ 45 ከመቶ የሰው ኃይል ጉድለት መኖሩን የቢሮው የምክትል ኃላፊ አመልክተዋልምስል Alemnew Mekonnen/DW

153 ጤና ተቋማትና ሠራተኞቻቸው በሥራ ላይ አይደሉም

በአማራ ክልል በጤናው ዘርፍ የሠው ኃይል፣ በትምህርቱ ደግሞ የተማሪ ቁጥር ማነስ አጋጥሟል

አማራ ክልል በጦርነትና በበጀት እጥረት የተሟል ሥራ ማከናወን እንዳልተቻል የትምህርትና የጤና የሥራ ኃላፊዎች ተናገርዋል።

በተለይ በጤናው ዘርፍ ከሚጠበቀው የሰው ኃይል አኳያ 45 ከመቶ የሰው ኃይል ጉድለት መኖሩን የቢሮው የምክትል ኃላፊ አመልክተዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መልካሙ ጌትነት ትናንት በቢሯቸው በሰጡት መግለጫ በባጀት እጥረትና በጦርነት ምክንያት ቢሮው 45  ከመቶ የሰው ኃይል ማሟላት አልቻለም ብለዋል። አሁን በክልሉ 72 ሺህ ያክል የጤና ባለሙያ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በዋናንት በሆስፒታሎችና በጤና ጣቢያዎች የባለሙያ እጥረቱ በከፍተኛ ደረጃ መኖሩን ያልሸሸጉት መከተለ ኃላፊው ቅጥር በሚፈልጉ የስራ መደቦች ላይ ተገቢ ሠራተኛ ተቀጥሮ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከወቅታዊ የክልሉ የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞም በርካታ ጤና ተቋማት እና ሠራተኞቻቸው በስራ ላይ እንዳልሆኑ አስረድተዋል።

153 ጤና ተቋማትና ሠራተኞቻቸው በሥራ ላይ አይደሉም

“ከወቅታዊ የአማራ ክልል የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ 141 ጤና ኬላዎችና 12 ጤና ጣቢያዎች ከነሠራተኞቻቸው በሥራ ገበታቸው ላይ አይደሉም” ብለዋል። በዚህም ምክንያት ኦክስጅን የሚፈልጉ ህሙማን፣ ደም የሚያሻቸው እናቶችና ድንገተኛ ታካሚዎች፣ ወደከፍተኛ ህክምና ሊሄዱ የሚገባቸው ታካሚዎች እድሉን ሳያገኙ ለሞት እንደሚዳረጉ ገልጠዋል።

በተደጋጋሚ ከምንገዶች መዘጋት ጋር በተያያዘም መድኃኒቶችን ወደ ህክምና ጣቢያዎች ማድረስ ባለመቻሉ ወቅታዊው የክልሉ የፀጥታ ችግር በመድኃኒት ስርጭትና አቅርቦት ረገድ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን አመልክተዋል። እስካሁን ባለው ሁኔታ መድኃኒቶች ወደ ክልሉ የሚደርሱት በአየር እንደሆነ ጠቁመው ይህ ደግሞ ለከፍተኛ ወጪ እንደሚዳርግ ተናግረዋል፣ ባሀርዳር ከደረሰ በኋላም ወደ ጤና ተቋማት ማድረሱ ሌላ ፈተና መሆኑን ገልጠዋል፣ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በመድኃኒት ስርጭት በኩል እገዛ እንደሚያደርጉም አስረድተዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መልካሙ ጌትነት
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መልካሙ ጌትነትምስል Alemnew Mekonnen/DW

6 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ህገወጥ መድኃኒት በቁጥጥር ስር ውሏል

በጤና ተቋማት በተደርገ ቁጥጥር 27 ከመቶ የሚሆኑ የጤና ተቋማት ህገወጥ በሆነ ሥራ ተሰማርተው ተገኝተዋል ብለዋል፣ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ህገወጥ መድኃኒት በእጃቸው የተገኘባቸው  የግል የጤና ተቋማት ላይም እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት፣ በዚህም መሰረት 5 የግል የጤና ተቋማት የታሸጉ መሆናቸውንና በ15ቱ ላይ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን በመግለጫቸው አመልክተዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን የፈረስ ቤት ጤና ጣቢያ ባልሙያ የሰው ኃይል እጥረቱ ባይኖርም ከፍተኛ የመደኃኒት እጥረቶች እንዳሉ አመልክተዋል።

መድኃኒቶችና ሌሎች ግብዓቶች ከባሕር ዳር ሰለሚመጡና ያን ለማድረግ ደግሞ የመኢናዎች እንቅስቃሴ የተገደበ በመሆኑ የግብዓት እጥረት በወረዳው ከፍተኛው ችግር እንደሆነ ነው የተናገሩት።

አንድ የደንበጫ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ባለሙያ በበኩላቸው በጤና ኬላ ደረጃ የሐኪሞች እጥረት መኖሩን ገልጠዋል።

የባለሙያና የግብዓት እጥረት

“በደንበጫ ከተማ ጤና ጣቢያ ደረጃ የፋርማሲና የቤተሙከራ ባለሙያ እጥረቶች አሉ፣ በገጠር ጤና ጣቢያዎች ላይ ደግሞ የሐኪሞች እጥረት አለ፣ ሥራዎች የሚሸፈኑት ከሚጠበቀው ደረጃ በታች ባሉ ሠራተኞች ነው” ብለዋል።

የደብረወርቅ ከተማ ጤና ጣቢያ ባለሙያ እንዳሉት ደግሞ ከፍተኛ የሰው ኃይል እጥረትበመኖሩ አንዱ የሌላውን እየሸፈነ ይሰራል ብለዋል።

በትምህርት መስክ ቢሆንም በተለይ በምዕራብ አማራ ተማሪዎች ወደ ትምህርት እየመጡ እንዳልሆን የክልሉ ትምህርት ቢሮ በቅርቡ አመልክቷል፡፡  

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2017 ዓ ም 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን መዘገቦ ለማስተማር አቅዶ የነበረ ቢሆንም የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር ከ2 ሚሊዮን 200 ሺህ እንደማይበልጡ ቢሮው በተለያዩ ጊዜዎች አመልክቷል። እስከአሁንም ለትምህርት የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሌለውና በተለይም በምዕራብ አማራ ዞኖች ችግሩ መቀጠሉን የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል የተጠበቀውን ያክል ተማሪዎች መመዘገብ አልተቻለም ተብሏል
በአማራ ክልል የተጠበቀውን ያክል ተማሪዎች መመዘገብ አልተቻለም ተብሏልምስል Alemnew Mekonnen/DW

የተጠበቀውን ያክል ተማሪ መመዘገብ ስላለመቻሉ

ምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ጎጃም፣ ምስራቅ ጎጃም በከፊል፣ ደቡብ ጎንድር በከፊል፣ አዊ ብሔርሰብ አስተዳደር በከፊል የተመዝጋቢ ተማሪ ቁጥር በጉልህ ቀንሶ የሚታይባቸው አካባቢዎች እንደሆኑ አስረድተዋል። ማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተሻለ አፈፃፅም ቢያስመዘግብም፣ በአንዳንድ ወረዳዎች ኝ አሁንም ችግሮች እንዳሉ አቶ ጌታቸው ገልጠዋል። የምስራቅ አማራ ዞኖች ከምዕራብ አማራ ዞኖች ሲነፃፀር የተሻል የተማሪ ምዝገባ መካሄዱንም ተናግረዋል።

የመጽሐፍት እጥረት

የተመዘገቡ ተማሪዎቹ ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም በትምህርት ላይ ያሉ ተማሪዎች ከፍተኛ የመጽሐፍት እጥረት እንዳለባቸው ተማሪዎች ይናገራሉ።

አረሴማ መስፍን በደሴ ከተማ አስተዳደር ሆጤ ሁለተናኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን የሒሳብ፣ የእንግሊዝኛና የፊዚክስ መማሪያ መጽሐፍት እጥረት በስፋት መኖሩን ነግራናልች።

በባሕር ዳር ከተማ የአፄ ሠርፀ ድንግል ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ዮናስ ተሻገር በበኩሉ በተለይ የሙያ ትምህርት መጽሐፍት በትምህርት ቤቱ በከፍተኛ ሁኔታ እጥረት እንዳለበት አስረድቷል።

ዓለምነው መኮንን

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ