በአማራ ክልል ሕግ በማስከበር ላይ እንዳሉ የተገደሉ ሥራ ኃላፊዎች | ኢትዮጵያ | DW | 01.06.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በአማራ ክልል ሕግ በማስከበር ላይ እንዳሉ የተገደሉ ሥራ ኃላፊዎች

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ ሁለት የስራ ኃላፊዎች በኮሮና መከላከል ዙሪያ ህግ በማስከበር ላይ እንዳሉ ትናንት በጥይት ተመትተው መገደላቸውን የራያ ቆቦ ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ ቤት አስታወቀ፤ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ክትትል እየተደረገ እንደሆነ ደግሞ የራያ ቆቦ ወረዳ ፖሊስ አመልክቷል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:23

የሟቾቹ የቀብር ሥነ-ስርዓት ዛሬ ከሰዓት በፊት ተፈፅሟል

የራያ ቆቦ ወረዳ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት የሚዲያ ይዘትና ማበልፀግ ስምሪት አስተባባሪ አቶ አየነ አማረ በስልክ ለዶይቼ ቬለ አንደገለፁት ኃላፊዎቹ ትናንት ለአስቸኳይ ሥራ ከዞኑ ማዕከል ወልዲያ ከተማ ሄደው ሲመለሱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ በመተላለፍ በአንድ ባለ ሶስት እግር ተሸከርካሪ ውስጥ ከሚፈቀደው የተሳፋሪ ቁጥር በላይ የያዘን አሽከርካሪ አስቁሞ ለመጠየቅ ባደረጉት ሙከራ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪና የወረዳው ሰላምና ደህንነት ጽ/ቤት ኃላፊ ሮቢት ከተማ አቅራቢያ ልዩ ሳሟ መንጀሮ በተባለች ቀበሌ በጥይት ተመትተው ተገድለዋል፡፡

አመራሮቹ በ30ና 40 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ አየነ ተጠርጣሪዎች ሲገለገሉባት የነበረች ባለሶስት እግር ባጃጅ ተሸከርካሪ በቁጥጥር ስር መሆኗን አመልከተዋል፡፡  የአማራ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ህሊና መብራቱ ድርጊቱ መፈፀሙንና ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

 የራያ ቆቦ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ነጋ ድንበሩ በበኩላቸው ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የመከላከያ፣ የአማራ ልዩ ኃይልና መደበኛ ፖሊስ በቅንጅት እየሰራ እንደሆነ ነው ለዶይቼ ቬለ ያመለከቱት፡፡

 ኮሮናን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ለማስፈፀም በተደረገ ጥረት ከዚህ በፊት በደቡብና ትግራይ ክልሎች በተመሳሳይ ሰዎች መገደላቸውን የተለያዩ ብዙሐን መገናኛ ድርጅቶች ዘግበዋል፡፡

 ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ 

እሸቴ በቀለ 

Audios and videos on the topic