በአማራ እና አፋር አዋሳኝ ቦታ ውጥረት ሰፍኗል | ኢትዮጵያ | DW | 10.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በአማራ እና አፋር አዋሳኝ ቦታ ውጥረት ሰፍኗል

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ከአፋር ክልል ጋር በሚያዋስነው ቦታ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በተፈጠረ ግጭት ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ የጸጥታ ኃይሎች ወደ አካባቢው ከተሰማሩ በኋላ ግጭቱ ቢበርድም አሁንም በስፍራው ውጥረት እንዳለ እማኞች ያስረዳሉ፡፡ የአካባቢው ባለስልጣናት ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረግን ነው ይላሉ፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:14

በሰሞኑ ግጭት 12 ሰዎች ሞተዋል ተብሏል

በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ የምትገኘው ሶዶማ ቀበሌ ሰሞኑን በውጥረት ውስጥ ሰንብታለች፡፡ በአፋር ክልል ውስጥ ከሚገኘው ጭፍራ ወረዳ ጋር የምትጎራበተው ይህቺው ቀበሌ በመሬት እና ውኃ ይገባኛል በየጊዜው የሚያገረሹ ግጭቶችን ስታስናግድ መቆየቷን የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ በሶዶማ ባለፈው ረቡዕ የተቀሰቀሰው ግጭት ግን ቀደም ሲል ከነበሩት የከፋ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የሶዶማ አቅራቢያ ነዋሪ በሰሞኑ ግጭት ከአፋር እና አማራ ወገን 12 ሰዎች መሞታቸውን ለዶይቸ ቨለ አስረድተዋል፡፡

“ተኩሱ የጀመረው ረቡዕ ነው፡፡ ከሶዶማዎች ሁለት ሰዎች እንደሞቱ ነው የሰማነው፡፡ በቀጣዩ ቀን ሐሙስ እዚያው ተፋጥጠው አደሩ፡፡ ጠዋት ላይ ውጊያ ጀመሩ፡፡ የፌደራል ፖሊሶችም በሕግ አምላክ ብለው፣ ባንዲራ ይዘው ሄደው ነበር፡፡ ነገሩን ለማስቆም ሞክረው ነበር ግን ወደ እነሱም ሲተኮስባቸው ያው እንደህዝቡ ተመልካች ነው የሆኑት፡፡ አፋሮች ስለሆኑ ወደ አማራው ድንበር የመጡት በርከት ያሉ እንደሞቱ ነው የሰማነው፡፡ በመጀመሪያ ስድስት እየተባለ ነበር፡፡ በኋላ ማታ አካባቢ ዘጠኝ ሞተዋል፡፡ በቀጣዩ ቀን አፋሮቹ አንድ ሰው ጠፍቷቸው ነበር፡፡ ፈልገው ወደ አስር እንደሞቱ ነው የተነገረው።” ሲሉ ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ በአካባቢው የነበረውን ግጭት ያስከትለውን ጉዳት ያብራራሉ፡፡ 

የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከዓርብ ጀምሮ አካባቢውን በመቆጣጠራቸው ግጭቱ መርገቡን እኚሁ ነዋሪ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ሆኖም በአካባቢው አሁንም ውጥረት እንደነገሰ እና ዳግም ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ፍራቻ እንዳለ ይናገራሉ፡፡ ይህንን አስተያየታቸውን ያነጋገርናቸው የሶዶማ ነዋሪም ይጋሩታል፡፡ 

“ያማ ትክክል ነው፡፡ ይፈራል፡፡ በትክክል ይፈራል፡፡ እኛ እንደምንሰማው አፋር ይመጣል ሲባል ነው፡፡ ረቡዕ እና ሐሙስ ግጭት ነበር፡፡ እንኳን አካባቢው ከዞን እስከ ክልል ድረስ ሰምቶታል፡፡ ህዝቡ አሁን አገሩን ወደየት አባታችን እንልቀቅ እያለ ነው።” ሲሉ በህዝቡ ዘንድ ያለውን ስጋት ይገልጻሉ፡፡ 

የአካባቢው እና የዞን ባለስልጣናት በግጭቱ የደረሰውን ጉዳት ለመመልከት ወደቦታው መጥተው አንደነበር የሶዶማ ነዋሪ ያስረዳሉ፡፡ የሰሜን ወሎ ዞን የአስተዳደር እና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አደራው ጸዳሉ ግጭቱ መከሰቱን ቢያምኑም “አሁን በአካባቢው ውጥረት የለም” ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ በግጭቱ ስለጠፋው ህይወት በማስረዳት ይጀምራሉ፡፡ 

“በግጭቱ ከወደ አፋር የሞተውን አላወቅነውም፡፡ ከወደ እኛ ሁለት ሰው ሞቷል፡፡ አሁን ያለው ምንድነው? የፌደራል እና የመከላከያ ኃይል ስለገባ ውጥረቱ በርዷል፡፡ በመካከል ላይ ሁለቱ ኃይሎች አሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች ስለገቡ [ግጭቱ] ቆሟል፡፡ ችግሩን በድርድር ለመፍታት እያሰብን ነው፡፡ ድርድሩንም ነገ እንግዲህ የሁለቱንም ክልል ወረዳዎች፤ የሀብሩ እና የጭፍራን ወረዳዎች፤ የሰላም ኮሚቴዎች ለማገናኘት አስበናል፡፡ ተኩሶች አሉ፡፡ የሰው ህይወት አልፏል፡፡ ይህንን ችግር እንግዲህ ለመፍታት ተቀራረበን ጥረት እያደረግን ነው፡፡ እንፈታለን ብለን እናስባለን” ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡ 

የአካባቢው ነዋሪዎች በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ቦታ ላይ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ግጭት ከቦታ ይገባኛል ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ፡፡ የአስተዳደር እና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊው ግን ምክንያቱ ሌላ ነው ባይ ናቸው፡፡ 

“አሁን በክረምቱ ችግሮች ነበሩ፡፡ ህዝቡ እና ህዝቡ በውኃ ይጣላሉ፣ በተለያዩ ሰበብ አስባብ እረኛው ይጣላል፡፡ ችግሩ የመሬት ይገባኛል ሳይሆን ከበፊት የመጡ ችግሮችን እየፈታን ባለመሄዳችን እና ያ ቁርሾ እየተያያዙ ሲገናኝ አንዱ ያበላሸዋል፡፡ አንዱ እረኛ ይተኩሳል፡፡ በዚያ ላይ ኅብረተሰቡ ጎራ ለይቶ የመተኳኮስ ሁኔታዎች አሉ፡፡ በዚህ መልክ ነው።” ሲሉ የግጭቶቹ መንስኤ ያሉትን ያስረዳሉ፡፡ 

ጉዳዩን አስመልክቶ ከአፋር ክልል ወገን ያለዉን መረጃ ለማግኘት ወደሚመለከታቸዉ ባለስልጣናት በስልክ ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ምላሽ የሚሰጠን ማግኘት አልቻልንም፡፡ 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች