በአላጥሽ ብሔራዊ ፓርክ አንበሶች መኖራቸዉ ታወቀ | ኢትዮጵያ | DW | 03.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

በአላጥሽ ብሔራዊ ፓርክ አንበሶች መኖራቸዉ ታወቀ

«ቦን ፍሪ » የተሰኘዉ የዱር አራዊት ተንከባካቢና አጥኚ ቡድን ኢትዮጵያ ሱዳን ድንበር አቅራብያ አላጥሽ ብሔራዊ ፓርክ አንበሶች ይገኛሉ ሲል አስታወቀ። የጥናት ቡድኑን የመሩት የብሪታንያዉ ኦክስፎርድ ዩንቨርስቲ ባልደረባ ኔዜርላንዳዊ ሃንስ ባወር ለዶይቼ ቬለ እንደገለፁት በብሔራዊ ፓርኩ ዉስጥ 200 የሚደርሱ አንበሶች ሳይኖሩ አይቀሩም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:07

የአንበሶች መንጋ መኖሩ ታወቀ


በኢትዮጵያ ሱዳን ድንበር አዋሳኝ አላጥሽ ብሔራዊ ፓርክ ወደ ሁለት መቶ ያህል አንበሶች ይኖራሉ ሲል ያስታወቁት የዩኤስ አሜሪካዉ ቦርን ፍሪ ፋዉንዴሽንና የኦክስፎርድ ዩንቨርስቲ የዱር አራዊት የምርምር ቡድን በጋራ ባደረጉት ጥናት ነዉ።

ጥናቱን የመሩት ኔዘርላንዳዊዉ ሃንስ ባወር ዛሬ ከአዲስ አበባ ለዶቼ ቬለ በስልክ እንደገለፁት አካባቢዉ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች አንበሳ እንደሚኖር ቀድመዉ ያዉቁ ነበር።

«በአላጥሽ ብሔራዊ ፓርክ የተካሄደዉን ጥናት የመራሁት እኔ ነኝ። አንበሶችን አግኝተናል። በርግጥ አካባቢዉ ላይ የሚኖሩ ሰዎች አንበሳ እዳለ ያዉቁ ነበር ነገርግን ይህ መረጃ በይፋ በጥናት ታዉቆ በዓለም አቀፍ ደረጃ አልተመዘገበም። ስለዚህም ነዉ ለመጀመርያ ጊዜ በሳይንሳዊ ጥናት መልክ ተገኘ ተብሎ የተነገረዉ። 200 አንበሶች ተብሎ የተነገረዉ ቁጥሩ በግምት የተቀመጠ ነዉ። ትክክለኛ የሆነ ሳይንሳዊ ጥናት አላካሄድንም። ግምታዊ ቁጥር ነዉ የተሰጠዉ»
በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች አንበሳ መኖሩ ይታወቃል ፤ነገር ግን በሰዉ ሰራሽ ነገሮች ቁጥራቸዉ እየተመናመነ መጥቶአል ያሉን፤ ኢትዮጵያ የዱር እንስሳትና ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የብሔራዊ ፓርኮች ማስተባበርያ ዳይሪክተር አቶ ኩመራ

ዋቅጅራ እንደገለፁት፤ የምርምር ቡድኑ በሱዳን በኩል ዲንቢር ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ በኩል በአላጥሽ ብሔራዊ ፓርክ ዉስጥ አንበሶችን አግኝተዋል።

ኢትዮጵያ ዉስጥ የዚህ አዉሬ አጠቃላይ ቁጥር በጥናት ደረጃ የተቀመጠ የቁጥር ማስረጃ አለን፤ ለሚለዉ ኢትዮጵያ የዱር እንስሳትና ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የብሔራዊ ፓርኮች ማስተባበርያ ዳይሪክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ከአንድ ሺህ እስከ አአንድ ሺህ አምስመቶ የሚሆኑ አንበሶች እናዳሉ ቆየት ያለ ጥናት ያመለክታል ሲሉ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ሱዳን ድንበር አቅራብያ አላጥሽ ብሔራዊ ፓርክ አንበሶች መኖራቸዉን ይፋ ያደረገዉ የጥናት ቡድን መሪ ሃንስ ባወር ይህ ጉዳይ በመታወቁ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአንበሶቹ ጠቃሚ ነዉ ብለዋል።

« ይህ ነገር መታወቁ ለኢትዮጵያ በጣም ጥሩ ይመስለኛል። ለአንበሶቹም ጥበቃ ቢሆን ጥሩ ነዉ። ለኢትዮጵያ የዱር አራዊት ጥበቃም ቢሆን አንድ ግበዓትና አማራጭ ይሆናል»


አዜብ ታደሰ


ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic