በአለም ገና የመኖሪያ ቤቶች ሊፈርሱ ነው | ኢትዮጵያ | DW | 07.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በአለም ገና የመኖሪያ ቤቶች ሊፈርሱ ነው

በአለም ገና አካባቢ በርካታ የመኖሪያ ቤቶች ሊፈርሱ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ። ነዋሪዎቹ ኦሮሞ ባለመሆናችን የመኖሪያ ቤቶቻችን ይፈርሳሉ ተብሏል ሲሉ ወቀሳ ቢያቀርቡም የሰበታ ከተማ አስተዳደር ግን አስተባብሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:55

በአለም ገና የመኖሪያ ቤቶች ሊፈርሱ ነው

በሰበታ ወረዳ ሥር በምትገኘው አለም ገና የቀበሌ 09 ነዋሪዎች በመኖሪያ ቤቶቻቸው ላይ ማስጠንቀቂያዎች ተለጥፈውባቸዋል። ማስጠንቀቂያው በመኖሪያ ቤታቸው በር ላይ የተለጠፈባቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት ህገ-ወጥ ግንባታ ተብለው ከተፈረጁት መንደሮች ንብረቶቻቸውን ለማውጣት ሰባት ቀናት ተሰጥቷቸዋል። ከባለቤታቸው እና አንድ ልጃቸው ጋር በአለም ገና የሚኖሩ ግለሰብ «መኖሪያ ቤታችሁ ሕገ-ወጥ ግንባታ ስለሆነ ንብረቶቻችሁን በሰባት ቀናት ውስጥ እንድታነሱ።» የሚል ማስጠንቀቂያ ከበራቸው ላይ መለጠፉን ይናገራሉ። የመኖሪያ ቤታቸው በ2001 ዓ.ም. መገንባቱን የሚናገሩት ግለሰብ ቤታቸውን የቀን ሥራ እየሰሩ መገንባታቸውን ይናገራሉ። መኖሪያ ቤታቸው የመፍረስ እጣ የተጋረጠበት ሌላ ግለሰብ በበኩላቸው «ወደ 4,500 አባዎራዎች ቤታቸው ይፈርሳል።» መባሉን ተናግረዋል። ከስምንት እስከ አስር ቤተሰብ የሚኖርባቸው መኖሪያ ቤቶች ጭምር ማስጠንቀቂያው እንደሚመለከታቸውም ገልጠዋል።

የመኖሪያ ቤቶቹን ለመገናባት መሬት ከገበሬዎች እና ከወጣቶች መግዛታቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች ሕጋዊ የባለቤትነት ሰነድ እንደሌላቸው አልሸሸጉም። መኖሪያ ቤታቸውን የሰሩበት ቦታ ለወጣቶች የተመራ እንደነበር የተናገሩ ሌላ ግለሰብ በሰባት ቀናት ውስጥ የኪራይ ቤት እንኳ ማግኘት አይቻልም ሲሉ የተሰማቸውን ሥጋት ይገልጣሉ። ነዋሪዎቹ የወረዳ አስተዳደሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ነዋሪዎች ለይቶ የመኖሪያ ቤቶቻቸውን ሊያፈርስ ነው የሚል ክስ ያቀርባሉ።

የሰበታ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ወርቁ ደበላ በአለም ገና ሕገ-ወጥ የተባሉ የመኖሪያ ቤቶች እንደሚፈርሱ አረጋግጠዋል። «አካባቢው ገጠር ሥር ነበር» የሚሉት አቶ ወርቁ «ወደ ከተማ ሲጠቃለል በአጭር ጊዜ ውስጥ በወረራ መልክ» አሁን ይፍረሱ የተባሉት የመኖሪያ ቤቶች መገንባታቸውን ገልጠዋል። «ተሰሩ የተባሉት ቤቶች በአሁኑ ሰዓት ሰው የማይኖርባቸው ፤ሕገ-ወጥ ሰዎች መሬት አስቀምጠው ለመሸጥ ብቻ አስር እና 20 ቆርቆሮ በገበሬ ማሳ ላይ የተሰሩ ቤቶች ናቸው።» ሲሉም አክለዋል።

አቶ ወርቁ የከተማ አስተዳደሩ በብሔር ለይቶ የመኖሪ ቤቶቻችንን ሊያፈርስ ተነስቷል የሚለውን ወቀሳ አይቀበሉም። «ሕገ-ወጥ ግንባታ የፈጸሙት ሰዎች ሌላ ብሔር ብቻ አይደለም። ብዙ ኦሮሞዎችም አሉ። ብሔርን ለይተን ትናንትናም አላደረግንም። ወደፊትም አናደርገውም።» ሲሉም አክለዋል።  ከተማችን የሁሉም መኖሪያ ናት የሚሉት አቶ ወርቁ ሕገ-ወጥ የመኖሪያ ቤቶች የማንም ይሁኑ የማን እናፈርሳለን ሲሉ በአፅንዖት አስረድተዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic