በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የአውሮጳ አምባሳደሮች ጥረት
ረቡዕ፣ ኅዳር 4 2017የትግራይ ትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፦ ዓለምአቀፍ ተቋማት ለተፈናቃዮች የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቀረበ ። የዓለምአቀፉ የፍልሰተኞች ተቋም (IOM)፣ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮምሽን (UNHCR)፣ እንዲሁም ሌሎች የተባበሩት መንግስት ኤጀንሲ ተወካዮች ትናንት በመቐለ ከተማ ተገኝተው ተፈናቃዮችን በመጠልያ ጣቢያ ጎብኝተዋል ። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው ባለመመለሳቸውም ለከፋ ችግር እየተዳረጉ ነው ብሏል ።
በትግራይ ክልል የነበረውን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በክልሉ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው ሊመለሱ ተስፋ አድርገው የነበረ ቢሆንም፥ እስካሁን ተግባራዊ እንቅስቃሴ አለመጀመሩ በማንሳት በትግራይ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለክልሉ አስተዳደር፣ ለፌደራሉ መንግስት፣ ለተለያዩ ርዳታ ለጋሽ ድርጅቶች እና ዓለምአቀፍ ተቋማት ቅሬታቸው ያሰማሉ ። ትናንት በመቐለ የተገኙት እና በከተማዋ ትልቁ የሆነው ሰብዓ ካሬ የተፈናቃዮች መጠለያ የጎበኙት የተባበሩት መንግስት ድርጅት ዓለምአቀፋዊ ተቋማት ለኢትዮጵያ ተልእኮ መሪዎች እንዲሁም ለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከተፈናቃዮቹ የቀረበላቸው ዋነኛ ጥያቄም ይህ ነበረ ።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በትግራይ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች እስካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ድረስ ይመለሳሉ ብሎ ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም፥ በተወሰነ መጠን ከተደረገው ተፈናቃዮች የመመለስ ሥራ በዘለለ አሁንም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት በመጠልያዎች ኑሮአቸው እየገፉ ናቸው። የሰብአዊ ርዳታ መቆራረጥ እና ለሁሉም አለመዳረስ፣ ሕክምና ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎት ማጣት፣ በተለይም ህፃናት ከትምህርት መራቅ እና ሌሎች ችግሮች ተፈናቃዮቹን እየፈተኑ መሆናቸው በክልሉ አስተዳደር በኩል ይገለፃል። ከተፈናቃዮች ለሚቀርብ በተለይም መች ወደቀዬአችን እንመለሳለን ለሚል ጥያቄ ቁርጥ ያለ ምላሽ ያልሰጡት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሣኤ አስተዳደራቸው ከፌደራል መንግስቱ ጋር ንግግር ላይ መሆኑን ለተፈናቃዮቹ ጠቁመዋል።
የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ተቋም አይኦኤም፣ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮምሽን ዩኤኤች ሲአር፣ እንዲሁም ሌሎች የተባበሩት መንግስት ኤጀንሲ ተወካዮች ትላንት በመቐለ ተገኝተው በተፈናቃዮች መጠልያ ካደረጉት ጉብኝት በተጨማሪ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ የተወያዩ ሲሆን በውይይቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪ ራሚዝ አለክባሮክ፥ ለተፈናቃዮች የሚደረግ ድጋፍ ወደዘላቂ ማቋቋም ለመቀየር መታቀዱ ይፋ አድርገዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የጀርመን፣ ኢንግሊዝና፣ ኔዘርላንድ እና የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደሮች በመቐለ በመገኘት ከክልሉ ባለስልጣናት ጋር የተወያዩ ሲሆን መንግስታቱ የትግራይ ሐይሎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት መልሶ የማደራጀት እቅድ እንዲፈፀም እንደሚደግፉ፣ የሽግግር ፍትህ እና ሀገራዊ ምክክር እንደሚያግዙ ገልፀዋል ።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ