1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«በትግራይ ክልል አዲስ መንግስት ይቋቋም» ተቃዋሚዎች

ማክሰኞ፣ መስከረም 7 2017

ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ፣የትግራይ ነፃነት ፓርቲ፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ እና ባይቶና በጋራ መግለጫቸው እንዳሉት የትግራይ የፀጥታ ሐይሎች በሲቪል አስተዳደር ስር ሆነው፣ በገለልተኛነት መንቀሳቀስ ሲገባቸው፥ በአንድ ፓርቲ ውስጣዊ መሳሳብ ቀጥታ በመግባት፥ መጥፎ ሁኔታ ላይ ያለው የትግራይ ፖለቲካ ይበልጥ እያወሳሰቡት ነው ሲሉ ወቅሰዋል

https://p.dw.com/p/4kj8m
የአራቱ የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎች በክልሉ ሁሉን አቀፍ አዲስ የሲቪል ጊዚያዊ መንግሥት እንዲመሰረት ጠይቀዋል
ከግራ ወደ ቀኝ ዮሴፍ በርሃ (የባይቶና ምክትል ሊቀመንበር)፣ አሉላ ሃይሉ (የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበር)፣ዓምዶም ገብረስላሴ (የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር)፣ ዶክተር ደጀን መዝገበ (የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ሊቀመንበር)ምስል Million Hailessilasie/DW

«በትግራይ ክልል አዲስ መንግስት ይቋቋም» ተቃዋሚዎች

 

በትግራይ የሚንቀሳቀሱ አራት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በክልሉ ሁሉን አካታች እና ሲቪላዊ አዲስ ግዚያዊ አስተዳደር እንዲመሰረት ጠየቁ። በትግራይ ክልል ያሉ ችግሮች መነሻ ፖለቲካዊ ናቸው የሚሉት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፥ መፍትሔውም ሁሉ አካታች ፖለቲካዊ መድረክ ነው ብለዋል። ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ለዴሞክራሲ፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ እና ባይቶና በጋራ በሰጡት መግለጫ የትግራይ ሐይሎች እያሳዩት ነው ያሉት ፖለቲካዊ ተሳትፎ ኮንነዋል።

ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ፣ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ እና ባይቶና በጋራ መግለጫቸው እንዳሉትየትግራይ የፀጥታ ሐይሎች በሲቪል አስተዳደር ስር ሆነው፣ በገለልተኛነት መንቀሳቀስ ሲገባቸው፥ በአንድ ፓርቲ ውስጣዊ መሳሳብ ቀጥታ በመግባት፥ መጥፎ ሁኔታ ላይ ያለው የትግራይ ፖለቲካ ይበልጥ እያወሳሰቡት ነው ሲሉ ወቅሰዋል። አሁን ላይ በትግራይ ተከስቶ ያለው ችግር መነሻ ፖለቲካዊ ስለሆነ መፍትሄው መሆን ያለበት ፖለቲካዊ ነው የሚሉት እነዚህ ፓርቲዎች፥ ይህ እንዲሆንም ሁሉን አካታች ሲቪላዊ ጊዚያዊ አስተዳደር እንደአዲስ እንዲቋቋም ጥሪ አቅርበዋል።

 

የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበር አቶ አሉላ ሐይሉ "ገጥሞን ያለው ችግር መነሻው ፖለቲካዊ ስለሆነ፥ ይህ ውድቀት ሊፈታ የሚችለው ደግሞ ምክርቤት ያለው፣ ሁሉም የፖለቲካ ሐይል በእኩልነት የሚያሳትፍ፣ ሲቪል ግዚያዊ አስተዳደር ሲቋቋም ስለሆነ፥ የትግራይ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ድያስፖራ በአጠቃላይ መላው ህዝባችን ይህ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲመጣ፥ በአንድ ስርዓት ውስጥ ያሉ ቡድኖች መሳሳብ ወደጎን በማለት፥ ከእኛ ጋር ተሰልፎ እንዲታገል ጥሪ እናቀርባለን" ብለዋል።

 

የትግራይ የፀጥታ ሐይሎች በትግራይ ፖለቲካ በአጠቃላይ፣ በዋነኝነት ደግሞ በህወሓት የውስጥ ፍጥጫ በተደጋጋሚ እጃቸው እያስገቡ መቆየታቸው ያነሱት የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ በበኩላቸው፥ ይህ የትግራይ ሐይሎች ውግንና የያዘ ፖለቲካዊ ተሳትፎ አደገኛ እና ሊቆም የሚገባው ብለውታል።አቶ ዓምዶም "ሲቪል አስተዳደር እንዳይመሰረት ብቻ ሳይሆን፥ በተለይም ከህወሓት ውጭ ያሉ ፖለቲካዊ ፖርቲዎች ከሰላማዊ ትግል ለመግፋት እና የራሳቸው ብቻ የሆነ ወታደራዊ ሐይል የሚያዩበት አካሄድ የመፍጠር ሁኔታ አለ። ይህ በትግራይ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል የሚዘጋ ስለሆነ ሊወገዝ የሚገባው ተግባር ነው" ብለዋል።

ከግራ ወደ ቀኝ  ዮሴፍ በርሃ ፣የባይቶና ምክትል ሊቀመንበር እና አሉላ ሃይሉ (የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበር
ከግራ ወደ ቀኝ ዮሴፍ በርሃ (የባይቶና ምክትል ሊቀመንበር)፣ አሉላ ሃይሉ (የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበርምስል Million Hailessilasie/DW

 

የትግራይ ነፃነት ፓርቲሊቀመንበር ዶክተር ደጀን መዝገበ በበኩላቸው፥ በስልጣን ሽኩቻ ተጠምደው ያሉ ያልዋቸው የህወሓት መሪዎች እና የግዚያዊ አስተዳደሩ ባለስልጣናት አንገብጋቢ የሆነ የትግራይ ህዝብ ጥያቄዎች ዘንግተው በእርስበርስ መወነጃጀል ላይ ተጠምደዋል በማለት ተችተዋል። ዶክተር ደጀን ጨምረውም "እነዚህ በግጭት ውስጥ ያሉ ሐይሎች የትግራይ አጀንዳ ከነአካቴው ረስተውታል። ስለየትግራይ ግዛት መመለስ ጉዳይ፣ ስለተፈናቃዮች፣ ስለየፕሪቶርያው ስምምነት አፈፃፀም፣ ስለየቀድሞ ታጋዮች ወደሰላማዊ ኑሮ የመመለስ አጀንዳ ሙሉ በሙሉ ተረስቷል። የእነዚህ ሐይሎች ግጭት እልም ወዳለ ጎጠኝነት አምርቶ፥ ወደማንወጣው አዘቅት እየመራን ነው" ሲሉ አክለዋል።

 

ባለፈው ሳምንት መጀመርያ ለመገናኛ ብዙሐን ተናግረው የነበሩት የትግራይ ሐይሎች አዛዥ እና የግዚያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ በህወሓት ውስጥ የተፈጠረው ልዩነት ተከትሎ የፀጥታ ችግር መፈጠሩ በመጥቀ፥ ሰልፍ የማድረግ እገዳ ጨምሮ በግዚያዊነት የተለያዩ ክልከላዎች መደረጋቸው ገልፀው ነበር። በትግራይ ሁሉን አካታች እና ሲቪል ግዚያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም በተቃዋሚ ፓርቲዎቹ እየቀረበ ያለው ጥሪ አስመልክተን ከክልሉ አስተዳደር ኮምኒኬሽን ፅሕፈት ቤት ምላሽ ለማግኘት የተደረገ ጥረት አልተሳካም።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ነጋሽ መሐመድ

ፀሐይ ጫኔ