በቴፒው ግጭዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተፈናቀሉ   | ኢትዮጵያ | DW | 04.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በቴፒው ግጭዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተፈናቀሉ  

ነዋሪዎቹ ሊፈናቀሉ የቻሉት ባለፈው ረቡዕ በቴፒ ከተማ የተነሳው ግጭት በከተማዋ ዙሪያ ወደሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ከተዛመተ በኋላ ነው። በአሁኑወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በከተማው የተለያዩ ሥፍራዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ለዲ ደብሊው ገልጸዋል።  

አውዲዮውን ያዳምጡ። 02:49

እርምጭ ፤ ኮቢጦና አዲስ ዓለም ቀበሌያት በሽዎች ተፈናቅለዋል

በደቡብ ክልል ቴፒ ከተማ በዞን መዋቅር የመደራጀት ጥያቄ ከተነሳ ወዲህ ከተማዋ ላለፉት አራት ወራት በውጥረት ውስጥ እንደምትገኝ ይነገራል። በተለይም ባለፈው ረቡዕ በከተማዋ ወጣቶችና በጸጥታ አካላት መካከል ተነከስቶ የነበረው ግጭት በከተማዋ ዙሪያ ወደሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች መዛመቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል ። በአሁኑ ወቅት እርምጭ ፤ ኮቢጦና አዲስ ዓለም ከሚባሉ ቀበሌያት በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው በመፈናቀል በቴፒ ከተማ ተጠልለው እንደሚገኙ ተናግረዋል። ከእርምጭ ቀበሌ ተፈናቅለው በቴፒ ከተማ የቀበሌ ጽህፈት ቤት አዳራሽ አገኛለው ያሉ አንድ ተፈናቃይ በአሁኑወቅት በከፍተኛ የደህንነት ሥጋት ውስጥ መውደቃቸውን ለዲ ደብሊው ገልጸዋል። ከሶስት ቀናት በፊት ከስድስት ቤተሰቦቻቸው ጋር ኮቢጦ ከተባለ ቀበሌ መፈናቀላቸውን የሚናገሩት ሌላው አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው / አስከአሁን የቴፒ ከተማ ነዋሪዎች እያቀረቡላቸው ከሚገኘው የዕለት ቀለብ በስተቀር ከመንግሥት ምንም አይነት ድጋፍ ባለማግኘታቸው በችግር ላይ መውደቃቸውን ተናግረዋል። በተፈናቃዮች ጉዳይ ዙሪያ ምላሽ ለመስጠት የስልክ ቀጠሮ የሰጡኝ የሸካ ዋና አስተዳዳሪ አቶ የሺዋስ ዓለሙ ከትናንት ጀምሮ ያደረኩላቸው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ባለመነሳቱ ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም ።  በደቡብ ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአማሮ፤ የቡርጂ ፤ የደራሼና የቴፒን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በሚከሰቱ ግጭቶች በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ እንደሚገኝ ይታወቃል። በግጭቶቹ ዙሪያ ዲ ደብሊውን ጨምሮ በርካታ የመገናኛ ብዙሃን ተጎጂዎችን ጠቅሰው ከሚያቀርቧቸው ዘገባዎች በስተቀር የክልሉ መንግሥት አስከአሁን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያም ሆነ ገለጻ ሲሰጥ አይስተዋልም ።  ባለፈው ዓርብ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የነበሩት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተለያዩ ክልሎች በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎችን ወደ አካባቢያቸው የመመለሱ ሥራ በአብዛኛው በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል ማለታቸው ይታወሳል። 


ሸዋንግዛው ወጋየሁ 


አዜብ ታደሰ 
ኂሩት መለሰ
 

Audios and videos on the topic