በቱርክ የቀጠለዉ ህዝባዊ ንቅናቄ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 25.06.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

በቱርክ የቀጠለዉ ህዝባዊ ንቅናቄ

ቱርክ ኢስታንቡል የተጀመረዉ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ለአንድ ሳምንት ጋብ ካለ በኋላ ዳግም አገርሽቷል። በእጃቸዉ ቀይ አበባ የያዙ በበሽዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞች በተቃዉሞዉ እንቅስቃሴ ወቅት ህይወታቸዉን ያጡትን ለመዘከር ወደታክሲም አደባባይ ወጥተዋል።

የጸጥታ አስከባሪ ፖሊሶች በበኩላቸዉ ተቃዉሞዉን ለመበተን ዳግም ዉሃ እና አስለቃሽ ጢስ በትነዋል። ቱርክ ኢስታንቡል ታክዚም አደባባይ  ላይ ሲካሄድ የሰነበተዉ  ሕዝባዊ ተቃዉሞ በፖሊስ ኃይል ለስድስት ቀናት ከበረደ በኋላ ባሳለፍነዉ ሳምንት መጨረሻ ዳግም ተቀስቅሶአል። ተቃዋሚ ሰልፈኞች  በተቃዉሞ ሰልፉ ወቅት ህይወታቸዉን ያጡቱን ለማስታወስ  ታክሲም አደባባይ የመታሰብያ ዝግጅት በማድረግ ላይ ሳሉ  ነበር ፤ የጸጥታ አስከባሪ ፖሊስ ዳግም  ሰልፉን ለመበተን አስለቃሽ ጋዝና ዉሃ መርጨት የጀመረዉ። በዚህ የመታሰብያ ዝግጅት ላይ በተለያየ የእድሜ ክልል የሚገኙ ተሳትፈዋል።  ህጻናትና በተሽከርካሪ ወንበር የሚንቀሳቀሱ አካል ጉዳተኞችም  ተገኝተዋል።

  ፖሊስ ሰልፈኞች እንዲበተኑ ባስጠነቀቀ ከአንድ ሰዓት በኋላ ዉሃ በመርጨትና እና አስለቃሽ ጢስ በመበተን ሰልፉን ለመበተን ሞከረ። ሰልፈኞቹ በበኩላቸዉ በእጃቸዉ የያዙትን ቀይ አበባ በማዉለብለብ «የናንተ የሆነዉን ሰዉ አሳልፋችሁ  አትስጡ» ሲሉ መለሱ። ከዚያ ጥቂት ቀደም ሲል የተቃዉሞ ሰልፈኞቹ ጠንከር ባለ ድምጽ ይህ ጅማሮ ነዉ፤ ትግሉ ይቀጥላል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ራችብ ኤርዶኻንን አስጠንቅቀዋል።  የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲ AKP  በህግ ይጠየቃል፤ ፖሊስ ያደረሰብን ጥቃትና፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን  ማሰፈራራት በህግ የምንጠይቅበት ቀን ይመጣል፤ ሲሉም ዝተዋል።  ጠቅላይ ሚኒስትር ራችብ ኤርዶኻን በታክሲም አደባባይ የወጣ ሰልፈኛ ሁሉ «አሸባሪ ነዉ » ማለታቸዉ ይታወሳል።


ባለፈዉ ሳምንት ቅዳሜ ዳግም ባንሰራራዉ ህዝባዊ ተቃዉሞ ላይ ተሳታፊ የነበረ  አንድ ሰልፈኛ እንዳለዉ«አሸባሪ ሳንሆን የቱርክ ዜጎች ነን። ተቃዉሞአችንን እያሰማን የተቻለንን ሁሉ ለታክሲም  እናደርጋለን» ሌላዋ ተቃዋሚም በበኩላቸዉ «ሰዎችን በማዋከብ ዝም እናሰኛለን  የሚል ግምት ነበራቸዉ። ግን ያንን ማድረግ አልቻሉም። ህዝቡ እንደማይፈራ አሳይቶአቸዋል»
አሁን አሁን የተቃዉሞ ሰልፈኞቹ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠንካራ ንግግር  እና የፖሊስን የኃይል እርምጃ እንደለመዱት ይናገራሉ፤ ከሰልፈኞቹ አንዷ እንደዉም ሊያደርጉ የሚችሉትን እናዉቃለን ይላሉ፤«በቀጣይ ምን ሊከሰት እንደሚችል እናዉቃለን። በበኩሌ አልፈራም። ቁጥራችን በበዛ ቁጥር ተስፋችንም ከፍ ያለ ነዉ» የቱርኩ የተቃዉሞ ሰልፍ በማህበረሰቡ መካከል ክፍፍል እንዳለ የሚጠቁም ምልክት ሆንዋል። ለዘብተኛዉ ወገን ከተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ጋር ህብረቱን ሲያሳይ፤ እስልምናን የሚያጠብቀዉ ወግ አጥባቂ ዉ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርዶኻንን ይከተላል።   
ባለፈዉ ቅዳሜ ኤርዶኻን «የሕዝብህን ፍላጎት አክብር» በሚል ሳምዙን በተሰኘችዋ ከተማ በጠሩት ስብሰባ 15,000 ደጋፊዎቻቸዉ ተገኝተዋል።  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸዉ  ሃይማኖታዊ መከራከሪያዎችን በማስቀደም የዉጭ  ኃይሎችን በቱርክ ለሚካሄደዉ ሕዝባዊ ንቅናቄ ተጠያቂ አድርገዋል።የቱርክ የንግድ ማዕከል በሆነችዉ በኢስታንቡል ከተማ የሚገኘዉ «ጌዚ» መናፈሻ ስፍራ ላይ የንግድ ማዕከል ግንባታ ሥራ እንዲካሄድ  መንግስት ያወጣዉን ትእዛዝ በመቃወም፤ የጀመረዉ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ዛሬ የነፃነትና የዲሞክራሲ ጥያቄ የሚቀርብበት መድረክ ሆንዋል።  ኢስታንቡል ላይ የተጀመረዉ የተቃዉሞ ሰልፍም ወደተለያዩ የቱርክ ከተሞችም ተዛምቷል። በመቶ ሽህ የሚቆጠሩት ተቃዋሚ ሰልፈኞች ጠቅላይ ሚኒስትር ረችብ ታይብ ኤርዶኻን ስልጣን እንዲለቁም ጠይቀዋል።
በቱርክ ታሪክ ትላለች፤ የዶቼ ቬለ የቱርክ ቋንቋ ክፍል ጋዜጠኛ ጽሁፍዋን ስታጠናቅቅ በዚህም በቱርክ ታሪክ፣ ለነፃነት እና እና ለዲሞክራሲ በሚደረግ ትግል ማህበረሰቡ ለመጀመ ርያ ግዜ በአንድ አካባቢ ላይ  ዴሞክራሲን ማየት ጀመሯል።

አዜብ ታደሰ
ሸዋዪ ለገሰ

Audios and videos on the topic