በቱርኩ ጥቃት ቢያንስ ዘጠኝ ጀርመናዉያን ተገድለዋል | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 12.01.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

በቱርኩ ጥቃት ቢያንስ ዘጠኝ ጀርመናዉያን ተገድለዋል

ቱርክ ኢስታንቡል የአገር ጎብኝዎች በሚያዘወትሩበት ቦታ በደረሰ ፍንዳታ 10 ሰዎች ተገደሉ 15 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደረሰባቸዉ። ከሟቾቹ መካከል ቢያንስ ዘጠኙ ጀርመናዉያን መሆናቸዉን የቱርክ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህሜት ዳቩቱግሉ ለጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ተናግረዋል።

ይህ ዜና ይፋ ከመዉጣቱ ቀደም ሲል የጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክልም ሆኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር በጥቃቱ የተጎዱ ጀርመናዉያን መኖራቸዉን ግን የሞተ እንደማይኖር ገልፀዉ ነበር። ፕሬዚዳንት ሪቺብ ታይብ ኤርዶጋን፤ አጥፍጦ ጠፊ ጥቃቱን ያደረሰዉ ግለሰብ የ 28 ዓመት ሶርያዊ መሆኑን ተናግረዋል። በጥቃቱ ከሞቱት መካከል ቱርካዉያንና የዉጭ አገር ዜጎች እንደሚገኙበት ሲነገር ነበር ያረፈደዉ። ኖርዌ አንድ ዜጋዋ በኢስታንቡሉ ጥቃት መጎዳቱን ያስታወቀች የመጀመርያዋ አገር መሆኗም ተዘግቦ ነበር። የሕክምና ባለሞያዎች ከተጎጂዎቹ መካከል ጀርመናዉያንና አንድ የፔሩ ዜጋ እንደሚገኝበት መግለፃቸዉም ተመልክቶአል።
ጥቃቱ እንደደረሰ የቱርኩ ጠቅላይ ሚኒስትር አህሜት ዳቩቱግሉ የሀገር አስተዳድረ ሚኒስትሩንና የሀገሪቱን የፀጥታ ጥበቃ ዋና ተጠሪ ለአስቸኳይ ዝግ ስብሰባ መጥራታቸዉ ተዘግቦአል። አስቸኳይ ስብሰባዉ ለማንኛዉም ሚዲያ ዝግ መሆኑን የቱርክ ባለሥልጣን መስርያ ቤት አስታዉቋል። አንድ ቦታዉ ላይ የነበሩ የዓይን እማኝ እንደገለፁትአጥፍቶ ጠፊ የጣለዉ ቦንብ ነዉ ። ጥቃቱ የደረሰበት ቦታ አይቼ ወደ ሆቴሌ ተመልሻለሁ። የጥቃቱ ቦታ እጅግ ምስቅልቅል የበዛበት ነበር። አሁን ፖሊስ አደባባዩን በሙሉ በሙሉ አጥሮ ምንም አይነት ዝዉዉር የለም።
አጥፍቶ ጠፊ ራሱን ያነጎደዉ በኢስታንቡል በቀድሞ ጊዜ በተቆረቆረዉ ሱልታን አህሜት በሚባለዉ የከተማ ክፍል በሚገኘዉ በታዋቂዉ ሰማያዊ መስጊድ ፊት ለፊት እንደሆነ ተገልጾአል። የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ ኢስታንቡል ተጓዥዎችም ሆነ ወደሌሎች የቱርክ ከተሞች የሚጓዙ ጀርመናዉያን ሰዉ በብዛት ከተሰበሰበት ቦታ እንዲሁም የአገር ጎብኝዎች ከሚጎበኙት ቦታ ከመገኘት እንዲቆጠቡ ሲል አሳስቦአል።


አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ