በተፈፀመው ዓመት፣ እ.ጎ.አ. በ2003፣ የዓለም ኤኮኖሚ ሂደት እንዴት እንደነበር ... | ኤኮኖሚ | DW | 20.01.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

በተፈፀመው ዓመት፣ እ.ጎ.አ. በ2003፣ የዓለም ኤኮኖሚ ሂደት እንዴት እንደነበር ...

ባለፈው ሣምንት በአሜሪካና በአውሮጳ አንፃር ተመልክተነው ነበር፣ ዛሬ ደግሞ የዚያኑ መልእክት ፪ኛ ከፊል በማቅረብ፣ የተቀረው ዓለም ኤኮኖሚያዊ ሁኔታ በዚያው በ2003 የነበረውን ሂደት መለስ ብለን እናስተውላለን።

በዚያው በኤኮኖሚው ሂደት ረገድ ብዙ የሚደረጁ ሀገሮች ነበሩ መለጠቅ ተስኗቸው ሲዳክሩ የቆዩት። ስለዚህም ነበር በካንኩን/ሜክሲኮ በተካሄደው በዓለም ንግድ ጉባኤ ላይ ከባድ ንትርክ ተፈጥሮ፣ ጉባኤውም ያለውጤት የተፈፀመው። በዚያው ወቅት የአጽናፋዊው ድንበርአልባ ኤኮኖሚ ተቃራኒዎች ብቻ አልነበሩም በተዛናፊውና በኢፍትሐዊው የሐብት ስርጭት አንፃር ብርቱ ተቃውሞ ያቀረቡት፤ ግን አዲስ ክስተት ሆኖ የታየው፣ የሚደረጁት ሀገሮች በዚያው በሜክሲኮው ካንኩን በተካሄደው ጉባኤ ላይ በአንድ አቋምና በአንድ ድምጽ ለመቅረብ መቻላቸው ነው። ከአከራካሪዎቹና ከአጨቃጫቂዎቹ ነጥቦች መካከል አንዱ፣ የግብርናው መርሕ ነው።--በዚህ ረገድ የሚደረጁት ሀገሮች በእንዱስትሪ-ሀገራቱ ላይ የሚያቀርቡት ስሞታ፣ እነዚያው ሐብታሞቹና እንዱስትረኞቹ ሀገራት ለግብርናው ዘርፋቸው ከፍተኛ ድጎማ እየከፈሉ በሚደረጁት ሀገሮች የግብርና ውጤቶች አኳያ የገበያውን ዕድል ይደመስሱታል የሚል ነው። በዚሁ ጥያቄ ረገድ ስምምነት ሊገኝ ባለመቻሉ ነበር በካንኩን/ሜክሲኮ የተካሄደው የዓለም ንግድ ድርጅት ጉባኤ ከሻፊ የሆነው። ሆኖም፣ ጀርመናዊቱ የግብርና ጉዳይ ሚኒስትሪት ሬናተ ኩይናስት እንደሚያስገነዝቡት፣ የዓለም ንግድ ድርጅት ጉባኤ እንዲቀጥል ከማድረግ በስተቀር ሌላ አማራጭ የለም። በእርሳቸው አመለካከት መሠረት፣ ሂደቱን መለጠቅ እየተሳናቸው ገና በመዳከር ላይ ለሚገኙት አዳጊ ሀገሮች የተለየ የገበያ ዕድል እንዲከፈት እጅግ አስፈላጊ ነው የሚሆነው፣ ይህ ነው ከዓለም ንግድ ድርጅት የሚጠበቀው ትልቁ የውሳኔ ጥበብ።

ግን፣ ይኸው የውሳኔ ጥበብ ምኑን ያህል አስቸጋሪ እንደሚሆን፣ በኋላ በባሕረሰላጤው አካባቢ ዱባይ ላይ የተካሄደው የዓለምአቀፉ ገንዘባዊ ድርጅት/አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ጉባኤ በግልጽ ነበር ያሳየው። በመሠረቱ ታዲያ፣ በአጽናፋዊው የሚዛን ዝንፈት ረገድ አንዳች የተቀየረ ነገር የለም፤ ራሳቸው የዓለም ባንክ ሊቀመንበር ጄምስ ዎልፈንዘን እንደሚሉት፣ አሁንም ቢሆን ጥቂቶች እጅግ ብዙ ሲኖራቸው፣ እጅግ ብዙዎቹ ደግሞ አለቅጥ ትንሽ ነው ያላቸው።

“ከስድስት ሚሊያርዱ የዓለም ሕዝብ አንድ ሚሊያርዱ ብቻ ከዓለም ጠቅላላ ገቢ ፹ በመቶውን አጠቃልሎ ሲይዝ፣ አንድ ሚሊያርድ ሕዝብ ደግሞ በቀን ከአንድ ዶላር ባነሰ ገቢ ሲንጠራወዝ እንዲኖር ግዴታ ይሆንበታል፣ ይህ ዓለም አለቅጥ ነው ከሚዛኑ ያፈተለከው” ይላል የዓለም ባንክ ሊቀመንበር ማስገንዘቢያ። ሊቀመንበሩ ዎልፈንዘን አበክረው እንደሚያስገነዝቡት፣ የልማትን ርዳታ በተመረጡ ዘርፎች ማዋል ብቻውን በቂ አይሆንም፣ ከዚህም አልፎ ከሐብታሙ ሰሜን ወደ ድሃው ደቡብ ይበልጥ ገንዘብ መሸጋገር ይኖርበታል። ዎልፈንዘን እንደሚሉት ከሆነ፣ በሐብታሞቹ እንዱስትሪ-ሀገሮች ውስጥ አሁንም ትልቅ የሚዛን ዝንፈት ነው የሚታየው፤ እነዚያው ሐብታም ሀገሮች ለልማት ርዳታ ፶፮ ሚሊያርድ ዶላር ብቻ ቆንጥረው ሲሰጡ፣ ለግብርና ዘርፋቸው ድጎማ ፫፻ ሚሊያርድ ዶላር ይመዛሉ፣ ለመከላከያ ደግሞ ፮፻ ሚሊያርድ ይከሰክሳሉ።

አለቅጥ የሚገዝፈው ወታደራዊ በጀት በብዙ የሚደረጁ ሀገሮችም ውስጥ ነው ለትምህርት፣ ለኤኮኖሚ መዋቅር ግንባታ እና ለጤና ጥበቃው አገልግሎት መዋል የሚገባውን ገንዘብ እያሟጠጠ ያለርባታ የሚያስቀረው። በቀውሶችና በውዝግቦች ፍርርቅ የሚዋከበው የአፍሪቃው አህጉር ከዓመታት በፊት ጀምሮ ነው የዓለም ኤኮኖሚን ሂደት መለጠቅ እየተሳነው በጠርዙ ላይ ሲዳክር የቆየው። በብዙ ያፍሪቃ ሀገሮች ውስጥ ቀሳፊው በሽታ ኤድስ የሚስፋፋበት ሁኔታ እንደቀጠለ ነው፣ በሚመጡትም ዓመታት ውስጥ እያንዳንዱን የልማት ርምጃ ገና በጅምሩ አሰናክሎ የሚያስቀረው እንደሚሆን ክፉኛ ነው የሚያሠጋው።

በእስያ ሁኔታው የተለየ ሆኖ ነው የሚታየው። ሕዝባዊት ቻይና ያካባቢው ኤኮኖሚያዊ ሞተር የምትሆንበት ዝንባሌ ነው የሚንፀባረቀው፤ ቻይና የምታስመዘግበው ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ሌላው ቀርቶ አውሮጳውያኑንና አሜሪካውያኑንም ሊያስቀና የሚችል መስሎ ነው የሚታየው። የኤኮኖሚውን ሂደት የሚገመግሙት ጀርመናዊው ፕሮፈሰር አክሰል ቬበር እንደሚሉት፣ ቻይና ውስጥ ግዙፍ የኤኮኖሚ ግስጋሴ ነው የተተካው፤ ይኸው ግዙፍ ዕድገት ቢያንስ በ፰ በመቶ ነው የሚገመተው፤ ቻይና በደቡብ-ምሥራቅ እስያ እውነተኛ የኤኮኖሚ ዕድገት ሎኮሞቲቭ ሆና ነው የምትታየው። ይኸው ሁኔታ ለዚያው አካባቢ አንቀሳቃስ ሞተር ከመሆኑም በላይ፣ ለጀርመንም ኤኮኖሚ ከፍተኛ የኤክስፖርት ገበያ ዕድል እንደሚሰጥም ነው ፕሬፈሰሩ የሚገምቱት።

በ2003 አጋማሽ ላይ የላቲን አሜሪካ ሀገሮች ኤኮኖሚ ሂደት የእስያውን ያህል ደምቆ ባይታይም፣ እዚያም ቢሆን ለኤኮኖሚው ዕድገት የተሥፋ ውጋጋን መታየቱን ሊቃውንቱ ይጠቁማሉ። በላቲን አሜሪካ ቀጥሎ የሚኖረውን ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ጀርመናውያኑ ሊቃውንት በአንድ በመቶ ግድም ነው የሚገመግሙት።

በምሥራቅና በደቡብ-ምሥራቅ አውሮጳም የኤኮኖሚው ዕድገታዊ ሂደት በ2003 ፍፃሜ ላይ የሚያሻቅብበት ሁኔታ ነበር የታየው። በተለይም ለአውሮጳው ኅብረት አባልነት በመዘጋጀት ላይ የሚገኙት ሀገሮች ናቸው ጉልህ ንቃት የተንፀባረቀባቸው።

በእነዚያው የምሥራቅና የደቡብምሥራቅ አውሮጳ ሀገሮች ውስጥ በተለይም የውኢሎተንዋዩ አየር ነበር አነቃቂ እየሆነ የተገኘው። የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ስለ ዓለምአቀፉ የገበያ ውድድር ሁኔታ ያቀረበው ዓመታዊ ዘገባ እንደሚያመለክተው፣ ባለፉት ፲ ዓመታት ውስጥ በተለይ የማዕከላይና የምሥራቅ አውሮጳ ሀገሮች ናቸው ከምንጊዜውም ይበልጥ ኤኮኖሚያዊውን ዕድገት ለማስመዝገብ የበቁት። ልክ እንደዚሁ፣ የደቡብ አውሮጳ ሀገሮች መዋቅራዊውን ለውጥ ማንቀሳቀስና ማራመድ፣ የጠቅላላ ኤኮኖሚውንም የዕድገት መርሕ ማጠናከር ይኖርባቸዋል። አሁን ሁንጋሪያ፣ ኤስቶኒያ፣ ወይም ስሎቬኒያ እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ እነዚያው የማዕከላይና የምሥራቅ አውሮጳ ሀገሮች በጊዜው ሂደት ውስጥ የተሻሻለ ውጤት ለማምጣት ብዙ መጣር እንዳለባቸው ይነገራቸዋል። ኮሙኒዝም ከተወገደበት ከትልቁ ለውጥ ወዲህ በእነዚያው ሀገሮች ውስጥ የተካሄዱት ብሔራዊ ኤኮኖሚዎች በግልጽ እንደሚያሳዩት፣ እነርሱም ቢሆኑ አጽናፋዊውን ውድድር ሊወጡት የሚበቁ መስሎ ነው የሚታየው። እነዚያው ሀገሮች የአውሮጳው ኅብረት አባላት በሚሆኑበት ጊዜ ለገበያው ውድድር አቅም ማሻሻያ እጅግ አስፈላጊ የሚሆኑትን ቅን የፖለቲካ መርሆዎች እንዲያጠናክሩ ግዴታ መሆኑን ነው ጠበብቱ የሚያስገነዝቡት። እንግዲህ፣ በጠቅላላው ሲታይ፣ በጎርጎራዊው ዓመት ፪ሺ፫ መጀመሪያ ላይ ከነበረው የዓለም ኤኮኖሚ ሁኔታ ይልቅ፣ በዚያው ዓመት ማለቂያ ላይ የተተካው የፈውሱ ዝንባሌ ነው በይበልጥ አነቃቂ ሆኖ የሚታየው። ይኸው አነቃቂ የዓለም ኤኮኖሚያዊ ሂደት ዘንድሮም በዚያው መስመር ላይ የሚቀጥል እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው።