በብራስልሱ ጥቃት የተጠረጠረው 3ኛ ሰው ተያዘ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 26.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

በብራስልሱ ጥቃት የተጠረጠረው 3ኛ ሰው ተያዘ

ቤልጂየም ብራስልስ አዉሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ማክሰኞ ዕለት በደረሰው ጥቃት እጁ እንዳለበት የተጠረጠው 3ኛ ሰው በቁጥጥር ስር ዋለ። የቤልጂየም አቃቤ ሕግ ዛሬ እንደገለፀው በቁጥጥር ስር የዋለው ሰው ከጥቃቱ አንስቶ ሲፈለግ የቆየው ፋይሳል ሼፉ ነው። በአሸባሪነት በርካታ ክስ ይጠብቀዋል ተብሏል።

እንደ ቤልጂየም «ሌ ሶር » ጋዜጣ ከሆነ ለዐርብ አጥቢያ በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪ ሽብርተኞቹን ወደ አይሮፕላን ማረፊያው በወሰደው ታክሲ ነጂ በሚገባ ተለይቷል። ይሁንና በሽብር ጥቃት ዛሬ ክስ የተመሰረተበት ፋይሳል ሼፉ በቁጥጥር ስር ሲውል ምንም አይነት የጦር መሣሪያም ይሁን ፈንጂ እንዳልተገኘበት ተገልጿል። ቤልጂየም እና ጀርመን ውስጥ በአሸባሪነት የተጠረጠሩ ዐሥራ አንድ ሰዎች ተይዘዋል። ዘጠኙ ተጠርጣሪዎች ቤልጂየም የቀሩት ጀርመን ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተዘግቧል።

ፋይሳል ሼፉ በደኅንነት ካሜራ ማክሰኞ እለት ከተቀረጹት ሦስት ሰዎች መካከል አንደኛው ሳይሆን አይቀርም ተብሏል። ሁለቱ በታጠቁት ፈንጂ የአጥፍቶ መጥፋት ወንጀል ፈጽመው 11 ሰዎችን በመግደል በርካቶችን ማቁሰላቸው መዘገቡ ይታወሳል።

በእርግጥም ፋይሳል ሼፉ ሦስተናው ተጠርጣሪ ስለመሆኑ ለማጣራት ፖሊስ የዘረ-መል (DNA) ምርመራ እያከናወነ መሆኑ ተዘግቧል።

ከፍተኛ ውድመት የደረሰበት የብራስልስ አዉሮፕላን ማረፊያ ቢያንስ እስከ መጪው ማክሰኞ ድረስ ተዘግቶ ይቆያል። ባለፈው ማክሰኞ ብራስል አዉሮፕላን ማረፊያ እና አንድ የምድር ዉስጥ የባቡር ጣቢያ ላይ በደረሱት ሦስት የቦምብ ፍንዳታዎች ከ30 በላይ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል።

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ