በቡሀሪ አመራር የምተተዳደር ናይጀሪያ | አፍሪቃ | DW | 04.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

በቡሀሪ አመራር የምተተዳደር ናይጀሪያ

የናይጀሪያ ህዝብ ባለፈው የሳምንት መጨረሻ በተካሄደ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የቀድሞው ወታደራዊ መንግሥት መሪ መሀማዱ ቡሀሪን ሀገሪቱን ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት እንዲመሩ አዲሱ ፕሬዚደንት አድርገው መርጠዋል።

ናይጀሪያ እአአ በ1999 ዓም ሥርዓተ ዴሞክራሲን ከተከለች ወዲህ አንድ በሥልጣን ላይ ያለ ፕሬዚደንት በዴሞክራቲክ ምርጫ ስልጣኑን ሲያጣ እና በተቃውሞ ፓርቲ ሲተካ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነው።እአአ በ1983 ዓም በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ስልጣን በመያዝ እስከ 1985 ዓም ድረስ ሀገሪቱን ጥብቅ ቁጥጥር ይታይበት በነበረ አገዛዝ የመሩትን እና የተቃውሞውን የጠቅላላ ኮንግረስ ፓርቲ ዕጩ ቡሀሪን መምረጡ ብዙዎችን እንዳስገረመ አቡጃ የሚገኘው የዶይቸ ቬለ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ዘጋቢ ቤን ሻሙና ገልጾልናል።

« ቡሀሪ ማሸነፋቸው በጣም አስገራሚ ነው፣ ምክንያቱም የወታደራዊው መንግሥት መሪ ሳሉ ህዝብ በብዛት ይነቅፋቸው ነበር። እጅግ ጠንካራ ሕጎችን በማስተዋወቅ በፈላጭ ቆራጭነት ነበር ሀገሪቱን የመሩት። እና ይህ ሁሉ እየታወቀ ይኸው አሁን ድል ተቀዳጅተዋል። »

እአአ በ2003፣ 2007 እና 2011 ዓም ለፕሬዚደንትነቱ ስልጣን የተወዳደሩት እና በአራተኛው ሙከራቸው ብቻ የቀናቸው ራሳቸውን ዴሞክራት አድርገው የሚያቀረቡት የቀድሞ ወታደራዊ አምባገነን መሪ ቡሀሪ በናይጀሪያ ዴሞክራሲያዊውን የመንግሥት አስተዳደር የመቀጠል እቅድ እንዳላቸው ቢያስታውቁም፣ ብዙ ናይጀሪያውያን የቡሀሪን ዴሞክራትነት መጠራጠራቸው እንዳልቀረ በለንደን የሚገኘው የአንድ ፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ ቴኖ ማንጂ ቼቶ አመልክተዋል።

እአአ ከ2010 ዓም ወዲህ ናይጀሪያን የመሩት የተሰናባቹ ፕሬዚደንት ጉድላክ ጆናታን የስልጣን ዘመን የሙስና ቅሌት የበዘበት እና ፅንፈኛው ቦኮ ሀራም በሰሜን ምሥራቃዊ በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቭሎችነ የገደለበት እና በመቶ የሚቆጠሩ ልጃገረዶችን እና ሌሎችን ያገተበት የሽብር ተግባር የተስፋፋበት ነበር።

የምርጫውን ሂደት የተከታተሉት የፖለቲካ ተንታኞች እንዳስረዱትም፣ ለፕሬዚደንት ጉድላክ ጆናታን መሸነፍ ሙስናን ያላስወገዱበት እና የቦኮ ሀራምን የሽብር ጥቃት ያላበቁበት ድርጊት በመራጩ ህዝብ ውሳኔ ላይ በዋነኝነትትልቅ ተፅዕኖ አሳርፈዋል። ባጠቃላይ ናይጀሪያውያን ከወታደራዊ አገዛዝ በኋላ በተከተሉት 16 ዓመታት የገዢው የህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራር መሰላቸታቸውን ነው የፕሬዚደንታዊው ምርጫ ውጤት በግልጽ ያሳየው። እርግጥ፣ በነዚህ ዓመታት በሀገሪቱ የቢልየነሮች ቁጥር ቢጨምርም፣ ሰፊው ህዝብ መሠረታዊ የሆኑት የኮሬንቲ እና የመጠጥ ውሀ አቅርቦት እጥረት በተባባሰበት እና የኑሮው ደረጃም ባሽቆለቆለበት ድርጊት እንደተቸገረ ነው።

ሙስናን ለማጥፋት በመቆማቸውየሚታወቁት ቡሀሪ ሰፊ ድጋፍ ያላገኙት በተለይ የወታደራዊው መንግሥት መሪ በነበሩበት ጊዜ ልጆች ከነበሩ ወይም ያኔ ካልተወለዱ ወጣት ናይጀሪያውያን ነው። እና ናሥዩሙ ፕሬዚደንት መሀማዱ ቡሀሪ በሥልጣን ዘመናቸው ለውጥ እንደሚያመጡ እና ካለፉት ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ ለቀጠሉት በርካታ ችግሮች መፍትሔ እንደሚያስገኙ ብዙ ናይጀሪያውያን ተስፋ ማድረጋቸውን ሲገልጹ፣ በምርጫ ዘመቻ ወቅት ሙስናን ለመታገል ቃል የገቡት ቡሀሪ ህዝቡ የሚጠብቅባቸውን ለውጥ ሊያስገኙ የሚችሉበት አዝማሚያ መኖሩን የፖለቲካ ተንታኟ ቴኖ ማንጂ ቼቶ አመልክተዋል።

«እርግጥ፣ መንግሥታቸው ምን ዓይነት አመራር እንደሚከተል በወቅቱ ማንም የሚያውቅ የለም፣ ይሁንና፣ የወታደራዊው መንግሥት መሪ በነበሩባቸው ሁለት ዓመት ያህል ገደማ ፣በሌሎች ናይጀሪያውያን ባለሥልጣናት አንፃር፣ ከሙስና የጸዱ ባለሥልጣን በመሆናቸው መልካም ስም ማትረፋቸውን ስናስታውስ ይኸው ባህርያቸው በመንግሥታቸው እና በሚሾሟቸው ባለሥልጣናት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል እንገምታለን። ይህ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነጥብ ነው። »

በናይጀሪያ ኤኮኖሚ ዋነኛ በሚባሉት የአክስየን ገበያ፣ የቦንድ ሽያጭን በመሳሰሉት ዘርፎች ላይ እየደረሰ ያለው ፈጣኑ ውድቀት ባለወረቶች በሀገሪቱ መንግሥት ላይ እምነት ማጣታቸውን አሳይቶዋል። እና የቡሀሪ ማሸነፍ ይህንኑ እምነት ሊመልስ ይችል ይሆናል።

« ናይጀሪያውያን መንግሥት መለወጥ እንደሚችሉ ለዓለም በማሳየታቸው፣ እንዲሁም፣ ናይጀሪያን አሉታዊ ስም ባሰጠው ሙስና አንፃር ቆርጠው የተነሱት ቡሀሪ አዲሱን መንግሥት የሚመሩበት ሁኔታ የባለወረቶችን እምነት ሊመልስ እና የናይጀሪያን ኤኮኖሚ መልሶ ለማነቃቃት አስፈላጊ የሆነውን ተጨማሪ ገንዘብ ሊያስገኝ ይችላል። »

ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ቦኮ ሀራም ባስፋፋው ሽብር ሰበብ ሀገሪቱን ከምትገኝበት አዳጋች ሁኔታ በማላቀቅ ረገድ የቀድሞው ጀነራል ቡሀሪ ከተሰናባቹ ፕሬዚደንት ጉድላክ ጆናታን የተለየ ፖሊሲ ሊጠቀሙ ይችሉ ይሆናል ብለው እንደሚያስቡ በሀምበርግ የሚገኘው ጊጋ የተባለው የጀርመናውያኑ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ ሮበርት ካፕል

« ቡሀሪ በቦኮ ሀራም አንፃር የተጀመረውን ትግል አጠናክረው ሊቀጥሉ እና ከወታደራዊው ዘዴ ጎን ለጎንም በድርድር መፍትሔ ሊያፈላልጉ ይችሉ ይሆናል ተብሎ ነው የሚጠበቀው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ በፕሬዚደንት ጉድላክ ጆናታን ዘመን ስር የሰደደውን ሙስና መታገላቸው አይቀርም። ሶስተኛ፣ እንደሰሜን ናይጀሪያ ተወካይ እና እንደ ሙሥሊም በኤኮኖሚያዊ ልማት ችላ በተባለው በዚሁ አካባቢ ለሚታየው ችግር፣ በተለይ ከፍተኛውን የወጣቱን ስራ አጥነት መቀነስ እና ደካማውን የትምህርት ሥርዓት ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል። ይህን በማድረግ ሀብታም በሚባለው ደቡቡ እና በድሀው ሰሜን መካካል ያለውን ልዩነት ሊያጠቡ የሚችሉበትን ድርሻ ሊያበረክቱ ይችላሉ ይሆናል።»

ሥዩሙ ፕሬዚደንት ቡሀሪ እአአ የፊታችን ግንቦት 29፣ 2015 በይፋ ሥልጣናቸውን ይረከባሉ።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic