በቄለም ወለጋ ሰባት ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ | ኢትዮጵያ | DW | 30.05.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በቄለም ወለጋ ሰባት ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ

በቄለም ወለጋ ዞን ሰባት ሰዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። ከሟቾቹ መካከል የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት የአካውንቲግ ተማሪ ነበር የተባለው ወጣት ካዩ አቦሴ ይገኝበታል። የኦሮሚያ ክልል ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ "ሰላማዊ ሰው ስለመሞቱ መረጃ የለኝም" ብለዋል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:49

የክልሉ መንግሥት አስተባብሏል

በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ደንቢዶሎ ከተማ እና ሳዩ ወረዳ አንድ ገጠር ቀበሌ ውስጥ የመንግስት ጸጥታ ሀይሎች በወሰዱት እርምጃ የሰው ህይወት ማለፉን ነዋሪዎች ተናገሩ። የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ «የክልሉ ፖሊስ በሰላማዊ ሰው ላይ ጉዳት  አላደረሰም» ብለዋል።  በደምቢ ዶሎና ሌሎችም ቦታዎች ከሸማቂዎች ጋር የወገኑ ግለሰቦች ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል፣ ወደ ህግ የማቅረብ ስራም እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በቄለም ወለጋ ዞን የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ ተሰማርተዋል በተባሉ የመንግስት ጸጥታ ሀይሎች እንግልት ደርሶብናል ይላሉ በስልክ ያነጋርናቸው የደንቢዶሎና አካባቢው  ነዋሪዎች።  ከሰሞኑ ከደረሱት ጉዳቶቸ መካከል ወጣት ካዩ አቦሴ የተባለው የደንቢዶሎ ከተማ ነዋሪ ግድያ አንዱ ነው። ወጣቱ በከተማው በሚገኙ የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት የአካውንቲግ ተማሪ እንደሆነም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። በአካባቢው ተሰማርቶ በሚገኘው የመንግስት ጸጥታ ሀይሎች ተይዞ ከታሰረ ከአንድ ወር በኋላ  ባለፈው ማክሰኞ ቤተሰቦቹ ለመጠየቅ ወደታሰረበት በደምቢ ዶሎ ከተማ የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ  ሲሄዱ ልጁ ህይወቱ ማለፉን እንደተነገራቸውም ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ አንድ የካዩ አቦሴ ቤተሰብ "ሚያዚያ 13 ነበር ወደ አምቦ እየሄደ ባለበት ወቅት በነቀምቴ ከተማ በፖሊሶች የተያዘው፡፡ ከሸማቂዎች ጋር ትሰራለህ ተብሎ ነው የተያዘው። ሚያዚያ 14 ደግሞ ወደ ደምቢዶሎ አምጥቶ አሰሩት፡፡ ለመጠይቅ ብዙ ጊዜ ተመላልሰን ማግኘትም አልቻልነም፡፡ አንዳ አንዴ እዚህ የለም ሌላ ጊዜ ደግሞ ምርመራ ላይ ነን እያሉ ይመልሱን ነበር፡፡ የሼነ ደጋፊ ነህ ተብለው ያለምንም ወንጀል ነው የታሰረው፡ ታስሮ አንድ ወር ከቆየ በኃላ  በደምቢዶሎ  እስር ቤት ውስጥ ህይወቱ አልፈዋል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በዞኑ ሳዩ ወረዳ የደምቢ ዶሎ አየር ማረፍያ አካባቢ በሚገኘው አንድ ቀበሌ ውስጥ የሚኖሩ ወይዘሮ ኦብሴ ደቤላ የተባሉ አርሶ አደርም በጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪ ገልጸዋል። ሌሎች ሶስት ወጣቶችም ከከተማው ውጭ በሚገኘው ሚኮ በተባለ ስፋራ ከሸማቂዎች ጋር ትሰራላችሁ ተብለው መገደላቸውን ጠቁመዋል።

"ወይዘሮ ኦብሴ የተባለችው ደንቢ ዶሎ አየር ማረፊያ አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ በጥይት ነው የተገደሉት፡፡ አቶ ዛክር የተባሉት ደግሞ የቤተሰባቸው አባል ሲሆኑ በደረሰባቸው ድብደባ በአሁኑ ጊዜ የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡  አሮን አህመድ፣ ደሳለኝ ጀበሳ እና አህመድ ደገፋ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪዎችም ወጣት ካዩ አቦሰ በተገደለበት ዕለት  ከደንቢዶሎ ከተማ በ9 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚትገኘው ሚኮ በተባለች ስፍራ በፖሊሶች ተገድለዋል፡፡ ሶስቱም ወጣቶች በጉልበት ስራ የሚተዳደሩ ናቸው" ብለዋል አንድ የአካባቢው ነዋሪ።

የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ በደምቢ ዶሎ እና ሌሎችም ስፍራዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ደርሰዋል ስለተባለው ጥቃት በሰጡት ማብራሪያ «የኮቪድ 19ን ለመከላከል የታወጀውን አዋጅ የተላለፉ አካላት ላይ እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ በተለየ መልኩ የተወሰደ እርምጃ የለም» ብለዋል፡፡ በደምቢ ዶሎ ከተማና ሌሎች አካባቢዎችም ከሸማቂዎች ጋር ግንኙነት ያላቸውና በወንጀል ድርጊት የተሳተፉ  ግለሰቦችን ወደ ህግ ከማቅረብ ውጭ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ህይወቱ ያለፈ ሰው ስለመኖሩ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት  በምዕራብ ወለጋ  ላሎ አሳቢ ወረዳ ከሸማቂዎች ጋር ግንኙነት አላችሁ ተብሎ በተወሰደው እርምጃ አምስት ሰዎች መገደላቸው እና  አራት ቤቶች መቃጠላቸውን መዘገባችን ይታወሳል። በምዕራብ ኦሮሚያ ለሶሰት ወራት ተቋርጦ የነበረው የስልክ አገልግሎት በተለቀቀበት ዕለት መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም የክልሉ መንግስት ለመገናኛ ብዙሐን በሰጠው መግለጫ በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ሸማቂዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንና አካባቢው  ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እየተመለሰ መሆኑን ገልጾ ነበር።

ነጋሳ ደሳለኝ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች