1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቁማር፤ በሃሺሻ፤ በጫት፤ ቤቶች ላይ ርምጃ ተወስዶአል

ሰኞ፣ መስከረም 14 2011

የአ/አበባ ፖሊስ ኮሚሽን: 1,200 ወጣቶች ጦላይ መላካቸዉን ፤ 174 በሕግ የሚጠየቁ ተጠርጣሪዎችን ማሰሩን እንዲሁም ፤ ሕገወጥ ቁማር ቤቶች ፣ ጫት ቤቶች ሺሻ ቤቶች ርምጃ መወሰዱን አስታወቀ ።

https://p.dw.com/p/35Q6p
Logo der Polizei-Kommission Addis Abebas
ምስል Addis Ababa Police Commission

174 ተጠርጣሪዎች ሕግ ፊት ይቀርባሉ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሺን ከመስከረም 2፤ እስከ መስከረም 7፤ 2011 ዓ,ም ድረስ በአዲስ አበባ ሁከት እና ግርግር፤ ብሎም ሥርዓት አልበኝነት ነግሶ እንደነበር አመለከተ። ሜጀር ጄነራል ደግፌ በዲ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ተከስቶ በነበረዉ  ጥቃትና ሁከት በድምሩ የ28 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የተለያዩ ጉዳቶችም መድረሳቸውን ዘርዝረዋል። ከዚሁ ጋር በወቅቱ በሕግ መጠየቅ አለባቸዉ የተባሉ ከአስሩም ክፍለ ከተማ የተያዙ በአጠቃላይ  174  ተጠርጣሪዎች ወደ ሕግ ፊት እንደሚቀርቡም አስታውቀዋል። በጥቃቱ ቁጥራቸዉ በዉል የማይታወቅ ሰዎች ቀላልና ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸዉና፤ በንብረትም ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ሜጀር ጄነራል ደግፌ በዲ ተናግረዋል። በሁለት ሦስት ቀናቱ ሁከትም በርካታ ሱቆች ተዘግተዉ በኢኮኖሚዉ ላይ ጉዳት ደርሶሷም ብለዋል። ሁከቱን ለማስቆም ፖሊስ በአስለቃሽ ጢስም ሆነ በምክር በማረጋጋት ላይ ሳለ በሰልፉ ጥፋት ሲሰሩ የነበሩ በቁጥጥር  ያዋልናቸዉን  «ለሕንጸት » ወደ ጦላይ ልከናቸዋል ሲሉ ሜጀር ጀነራል ደግፌ በዲ ተናግረዋል። ፖሊስ ከዚህ በተጨማሪ ኅብረተሰቡ ቀደም ብሎ ዝጉልን ያላቸውንና ፖሊስ ሲከታተላቸው የነበረ ሕገወጥ ንግድ ቤቶች ማለትም ቁማር ፣  ሺሻ፣  ጫት፣  ሃሺሽ፣ ቤቶች ላይ ርምጃ መወሰዱን አስታዉቀዋል። በሳምንቱ መጨረሻ አዲስ አበባ ላይ በርካታ ወጣቶች በፖሊስ መታሰራቸዉን ተከትሎ ነዋሪዉ ስጋቱን በተለያየ መንገድ እየገለፀ ነው። 

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ