በሽንሌ ዞን የተቀሰቀሰዉ ተቃዉሞ | ኢትዮጵያ | DW | 24.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በሽንሌ ዞን የተቀሰቀሰዉ ተቃዉሞ

ከቀናት በፊት በሽንሌ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች በርዕሰ መስተዳድሩ አብዲ መሐመድ ኡመር አስተዳደደር ላይ ተቃውሞ ተቀስቅሶ እንደነበር ከአካባቢው የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። የተቃዉሞው መነሻ የአስተዳደር ብልሽት እና ሙስና ነው እየተባለ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:36

የተቃዉሞው መነሻ የአስተዳደር ብልሽት እና ሙስና ነው

ከቀናት በፊት በሽንሌ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች በርዕሰ መስተዳድሩ አብዲ መሐመድ ኡመር አስተዳደደር ላይ ተቃውሞ ተቀስቅሶ እንደነበር ከአካባቢው የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ የተቃውሞው መነሻ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ ሞሐመድ ኡመር በሽንሌ እና ሌሎችም ዞኖች ብቃት የሌላቸውን የራሳቸውን ቅርብ ዘመዶች እና የጎጥ ሰዎች በተለያዩ የመንግሥት ሃላፊነት ላይ በመሾማቸው፣ የአስተዳደር በደልና አድልዖ እንዲሁም ሙስና እና የጥቅማጥቅም ግንኙነት በመንሰራፋቱ እንደሆነ ትናንት በሰልክ ያነጋገርኳቸው ካናዳ የሚኖሩት የቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ መሐመድ ሮበሌ ገልጸውልኛል፡፡ አቶ መሐመድ የሽንሌ ዞን ተወላጅና ቀደም ሲል የአይሻ ወረዳ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ የነበሩ ሲሆን አሁን በካናዳ እና ሰሜን አሜሪካ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አመራር ላይ ለሚደረገው ተቃውሞ አንዱ አሰተባባሪ ናቸው፡፡

አቶ መሐመድ እንደሚሉት አሁን የሸንሌ ዞን ሕዝብ ለተቃውሞ የተነሳው ከሌላ ዞን የመጡ ሹሞች በክልሉ መንግስት ባለስልጣናት ላይ በማህበራዊ ሜዲያ ትችት የሚያቀርቡ ሱማሌዎችን የአካባቢው ሽማግሌዎች እንዲያወግዙ በማስገደዳቸው ነው፡፡ ሽማግሌዎቹ ግን ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ከሕብረተሰቡ ውይይት አድርገው ሕብረተሰቡ የአቶ አብዲን ሹሞች ከአካባቢው ለማስወጣት አቋም በመያዙ የተቀሰቀሰ ተቃውሞ እንደሆነ ገልጸውልኛል- አቶ መሐመድ፡፡ በተለይ ስለ ሙስናው እንዲህ ይላሉ፤ ሕዝቡን ያማረረው ሙስና ስውር ፖለቲካዊ ዓላማ ይኖረው እንደሆነ ለጠየቅኋቸው ጥያቄ ሲመልሱም በርግጠኝነት መናገር ባይችሉም ሱማሌ ክልልን እንገነጥላለን ከሚል ስውር ፖለቲካዊ ተልዕኮ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ግን ጥርጣሬ እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡

ተቃውሞው በየትኞቹ አካባቢዎች እንደተቀሰቀሰ ላነሳሁላቸው ጥያቄ አቶ መሐመድ እንዲህ ሲሉ ይመልሳሉ፤ አቶ መሐመድ ባላቸው መረጃ አሁንም በአይሻ ወረዳ ላይ ተቃውሞውን ለመቀጠል ዝግጅት ላይ መሆኑን፤ በቢኪ እና አፍደም ወረዳዎች ግን እስካሁንም ተቃውሞው ከሞላ ጎደል እንደቀጠለ ነው፡፡ በእስካሁኑ ተቃውሞ በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ግን በርግጠኝነት ማወቅ አልተቻለም፡፡

ከቀናት በፊትም ተቃውሞውን ሲያሰተባብሩ የነበሩ ወጣቶችን የከልሉ መንግስት ወደ ጅግጅጋ ወስዶ ስለማሰሩ መረጃ እንዳላቸው አቶ መሐመድ ገልጸው ይህንኑ የሰሙ የድሬዳዋ ወጣቶች ዕሁድ ዕለት በአቶ አብዲ ላይ የተቃውሞ መፈክር እያሰሙ በሰልፍ ወደ ሽንሌ ሲገሰግሱ የመከላከያ ሠራዊቱ አስቁሟቸው እንደነበር ነግረውኛል፡፡ የሠራዊቱ አባላት ለወጣቶቹ ሰልፍ እንደማይቻል እያስረዱ ሳሉ ግን የሱማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ አባላት በድንገት በተሸከርካሪ ደርሰው ወደ ሰማይ ጥይት እንደተኮሱና የፌደራሉ ወታደሮች ግን ጥይት የተኮሰውን የልዩ ፖሊስ አባል መሳሪያውን ከገፈፉ በኋላ በመኪና ጭነው ስለወሰዱት ወጣቶቹ ጉዳት ሳይደርስባቸው መበተናቸውን ነግረውኛል፡፡

እንደ አቶ መሐመድ ምስክርነት ከሆነ ከውጭ ሀገር ተምረው ክልሉን ለማገልገል የመጡት የክልሉ ተወላጅ ወጣቶች እየታሰሩ ልምድ የሌላቸው በከፍተኛ ሃላፊነት ተሹመዋል፡፡ በውጭ ሀገር ያሉ የክልሉ ተወላጆች ተቃውሞ ሲያሰሙ ደሞ የአቶ አብዲ መንግሥት በክልሉ ያሉ ዘመዶቻቸውን ያስራል፡፡ ከሳምንታት በፊት 1,500 እስረኞች በምህረት ከእስር ተፈተዋል መባሉም ሐሰት መሆኑን በርግጠኝነት የሚናገሩት አቶ መሐመድ እሰረኞቹ ከወህኒ ወጥተው በቪዲዮ ከተቀረጹ በኋላ ሃያ የማይሞሉት ብቻ ተፈትተው ሌሎቹ ግን ተመልሰው ወደ ወህኒ ተልከዋል ይላሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰኞ ዕለት ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አብዲ ባደረጉት የካቢኔ ሽግሽግ የሽንሌ ዞን የኢሳ ጎሳ ተወላጅ የሆኑትን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩን አቶ አብዲከሪም ኢጋልን ከሃላፊነት አስነስተው በአቶ ሐምዲ አዳን አብዲ እንደተኳቸው የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡ የምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ መነሳት ስላለው አንድመታ አቶ መሐመድ እንዲህ ይላሉ፤

አቶ አብዲ ሽግሽጉን ያካሄዱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ ጋር በማበር ከሥልጣን ያስነሱኛል የሚል ስጋት ስላደረባቸው እንደሆነ አቶ መሐመድ ጠንከር ያለ ጥርጣሬ አላቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት አዲሱ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሐምዲ በዕድሜ ወጣት፣ በፖለቲካ፣ አስተዳድር እና ትምህርትም ልምድ ያላቸው አይደሉም፡፡ ሹመቱንም አቶ አብዲ ሥልጣናቸውን የማይጋፏቸውን እና በቀላሉ የሚታዘዟቸውን ሰዎች እየመረጡ እንደሚሾሙ ሁነኛ ማረጋገጫ ነው ባይ ናቸው፡፡

በሰሜን አሜሪካ በአቶ አብዲ አመራር ላይ ለሚደረገው ተቃውሞ አስተባባሪ እንደመሆናቸው በቅርቡ ምን እንደሚጠብቁ አቶ መሐመድን ጠይቄያቸው ነበር፤ ተቀማጭነቱ ሰሜን አሜሪካ የሆነውን Somali Region Alliance for Justiceን ጨምሮ በውጭ ሀገራት ባሉ የሱማሌ መብት ተሟጋች ማህበራት ስር የክልሉ ሥልጣን ወደ ሕዝቡ እስኪመለስ፣ ሕዝቡ የፍትሃዊ ዕድገት ተጠቃሚ እስኪሆን፣ ያላግባብ የታሰሩት እስኪፈቱ እና በተለይ በሽንሌ አቶ አብዲ ሸሪክ የሆኑ ሃላፊዎች እስኪነሱ ድረስ ትግላቸውን እንደሚገፉበት ጠቅሰው፣ በማያያዝም እንዲህ ሲሉ አክለው ያብራራሉ፤

በሽንሌ ዞን በብዛት የሚኖሩት የኢሳ ጎሳ ሱማሌዎች ሲሆኑ በአቶ አብዲ ክልላዊ መንግሥት ከፍትሃዊ ፖለቲካ ሥልጣን እና ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የተገለሉ መሆናቸውን ሲዘገብ የኖረ ጉዳይ ነው፡፡ ሽንሌ ዞን የኢትዮ-ጅቡቲ ባብር ሐዲድ የሚያልፍበት እና የኢትዮጵያ መንግሥትም ከጥቂት ዐመታት በፊት ጅቡቲ ለሠላሳ ዐመታት በነጻ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አልምታ እንድትወስድ ፍቃድ ያገኘችበት አካባቢ ነው፡፡ በጅቡቲ የፖለቲካ ሥልጣን በዋናነት በ በኢሳዎች የተያዘ በመሆኑም የአካባቢው ጸጥታ የፌደራሉን መንግሥት ብቻ ሳይሆን የጎረቤት ጅቡቲንም ትኩረት የሚስብ ነው፡፡

 

ቻላቸዉ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች