በሽታና ድርቅን መቋቋም የሚችሉት የስንዴ ዝርያዎች  | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 07.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

በሽታና ድርቅን መቋቋም የሚችሉት የስንዴ ዝርያዎች 

ኢትዮጵያ ለስንዴ እና ለማካሮኒ ምርት የሚሆነውን ዱረም የተባለ ስንዴ በብዛት የምታስመጣው ከውጭ ሀገር ነው፡፡ ጥራት ያለው እና ምርታማነቱ የተመሰከረለት ይህን አይነት ስንዴ በሀገር ውስጥ በብዛት እንዲመረት ምርምር እያደረጉ ያሉ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ሁለት አዲስ የስንዴ ዝርያዎችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ እንዲውል አስችለዋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:59

አዲሶቹ የስንዴ ዝርያዎች ለፓስታ እና ማካሮኒ ምርት ይሆናሉ

በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን ደዋ ተምቤን ወረዳ ያሉ አርሶ አደሮች አጭደው የከመሩትን የስንዴ ምርት በአምስት በሬዎች እገዛ እየወቁ ነው፡፡ ለአጨዳ የተዘጋጀ የስንዴ ማሳም በአቅራቢያቸው ይታያል፡፡ የአካባቢው አርሶ አደሮች አዳዲስ የስንዴ ዝርያዎች መጠቀም ከጀመሩ በኋላ አዝመራ ይይዝላቸው ይዟል፡፡ አዳዲሶቹን ዝርያዎች ያገኟቸው ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ነው፡፡  የምርምሩ ጠንሳሽ ዶ/ር ደጀኔ ካሳሁን ይባላሉ፡፡ ለማካሮኒ እና ፓስታ ምርት በሚያገለግለው የዱረም ስንዴ ላይ ምርምር ማድረግ የጀመሩት ከ2003 ዓ.ም አንስቶ ነው፡፡ ስድሳ የትግራይ ክልል አርሶ አደሮችን በመያዝ የተጀመረው የአዳዲስ ዝርያዎች ሙከራ ዛሬ እስከ 900 ሰዎችን ያቀፈ ሆኗል፡፡

“እኛ እየሰራን ያለነው ሀገር በቀል ዝርያዎች አሉን፡፡ በማካሮኒ እና ፓስታ ስንዴ ብዙ ብዝሀ ህይወት አለን፡፡ እነዚያ ስንዴዎችን በአግባቡ ለረጅም ጊዜ አልተጠቀምንባቸውም እና እነዚያን ከብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት፣ ታቅበው ከሚቀመጡበት ቦታ፣ አውጥተን ለተለያዩ ነገሮች ስንሞክራቸው ነበር፡፡ አንደኛው እኛ የምንሰራበት አካባቢ ላይ ተስማሚነታቸው ምን ይመስላል? የሚል ማየት ነበር፡፡ ሁለተኛ ምርታማነታቸው ምን ይመስላል?  የሚልም እንደዛው አለው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ የአካባቢው የአየር ንብረት ለውጥን እርሱን መቋቋም የሚችሉ አሉ ወይ? የአየር ንብረት ለውጡን ተከትሎ በሽታዎች አሉ እነዚያንም የሚቋቋሙ ዝርያዎችን መምረጥ ነበር ስራችን” ይላሉ ዶ/ር ደጀኔ።

ዶ/ር ደጀኔ እና ባልደረቦቻቸው ለምርምር ስራቸው ከብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዮት የወሰዷቸው ዝርያዎች 477 ዝርያዎችን ነበር፡፡ የሀገሪቱን የብዝሀ ህይወት ሀብት በተገቢው ሁኔታ በሳይንሳዊ መንገድ ለመጠበቅ እና ዘለቄታዊ አጠቃቀም እንዲኖር በተቋቋመው በዚህ ኢንስቲትዮት ውስጥ ዝርያዎች በጂን ባንክ ውስጥ እንዲቀመጡ ይደረጋል፡፡ ከተቋሙ በተገኘው መረጃ መሰረት እስከ ባለፈው መስከረም ወር ድረስ 72‚634 የሰብል እና ሆርቲካልቸር ዝርያዎች ናሙና በጂን ባንኩ ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡ 

በተለያዩ ምክንያቶች ጨርሰው እንዳይጠፉ በጂን ባንክ ውስጥ እንዲቀመጡ ከተደረጉት ውስጥ እነ ዶ/ር ደጀኔ ለምርምር የወሰዷቸው ነባር የስንዴ ዝርያዎች ይገኙበታል፡፡ ዶ/ር ደጀኔ ሀገር በቀሎቹን ዝርያዎች ለምን ወደ አርሶ አደሮቹ መልሶ መውሰድ እንዳስፈለገ እና ስለምንነታቸው ያስረዳሉ፡፡  

“እዚያ የተቀመጡት ዝርያዎች ከዚህ ቀደም አባቶቻችን ሲያመርቷቸው ነበር፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከምርት የወጡ ናቸው፡፡ አንደኛው የተሻሻሉ ከውጭ የመጡ የስንዴ ዝርያዎች አሉ እነርሱ ስለተኳቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የእነዚህ ተፈላጊነትን ይህን ያህል ገብቶን፣ ገበሬውም ስላላስቀመጠቸው ጠፍተው ነበር፡፡ ስለእዚህ እነዚህን ለምን መመለስ አስፈለገ የሚለው የዛሬ ሃያ ሰላሳ ዓመት የነበረው የአየር ንብረት እና ዛሬ ያለው የአየር ንብረት አንድ አይደለም፡፡ ዝርያዎች ደግሞ በየጊዜው መሻሻል፣ መታደስ አለባቸው፡፡ ለማዳሻ የሚያገለግሉት ደግሞ እነዚህ ዝርያዎች ናቸው፡፡ ብዙ የተለያዩ ዘረ መሎች አሏቸው” ይላሉ። 

እነ ዶ/ር ደጀኔ ከብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ከወሰዷቸው ዝርያዎች መካከል ሰላሳ ስድስቱን መርጠው በተለያየ አካባቢዎች ላሉ አርሶ አደሮቹ አከፋፍለዋል፡፡ ነባር ዝርያዎችን ለገበሬዎቹ መልሰው ሲሰጡ እንዲያው ምንም እሴት ሳይጨመርባቸው ሳይሆን ብዙ ስራዎች ተሰርተው እንደሆነ ዶ/ር ደጀኔ ይናገራሉ፡፡ በሚሰሯቸው ሙከራዎች ዝርያዎችን እንደሚፈትሹ እና እንደሚያወዳድሩም ይገልጻሉ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ተቀላቅለው የነበሩ ዝርያዎችን ወስደው ወጥ እንዲሆኑ እንደሚያደርጉም ያብራራሉ፡፡  

“እኛ አሁን በዚህ በመስክ ላይ መፈተሽ ብቻ ሳይሆን በዘረ መል ደረጃ ዲ.ኤን.ኤያቸውን አይተን፣ ጂናቸው ምን ይመስላል? የትኛው ዘረ መል ነው ለበሽታ መቋቋም የሚውለው? የትኛው ዘረ መል ነው ለድርቅ መቋቋም የሚውለው? የትኛው ዘረ መል ነው ለምርታማነት የሚያገለግለው? የሚለውን [እንፈትሻለን]፡፡ የተሻሻለ ዝርያ ውስጥ የሌሉ እነዚህ ውስጥ ያሉ አሉ፡፡ አንደኛው እነዚህ ዝርያን ለነገ ለማሻሻል ስለሚጠቅሙ ባህርያቸውን ተንትኖ ለማወቅ አስፈላጊ ስለሆነ ትንተናውን ሰርተናል፡፡ ሁለተኛ ተሻሽለው ከሌላ ሀገር የመጡ ዝርያዎች ከቦታ ቦታ ምርታማነታቸው የተለያየ ነው፡፡ አንዱ ቦታ ላይ ጥሩ ይሆናሉ፣ ሌላ ቦታ ላይ ጥሩ አይሆኑም፡፡ እኛ በምንሰራበት ክልል ላይ አብዛኞቹ ምርታማነታቸው ይህን ያህል ነው፡፡ ስለዚህ ምርታማነታቸውም፣ ገበሬዎች ጋር ሄዶ ተቀባይነታቸውም እስከዚህም ስለሆነ እነኛን መልሰን ብናመጣቸው እና ብንሞክራቸው ብለን ነው ያመጣናቸው፡፡ ገበሬዎች እንዲመርጧቸው አደረግን፡፡ ገበሬዎች በጣም ነው የወደዷቸው” ሲሉ ዝርያዎቹ ጥሩ ተቀባይነት ማግኘታቸውን ይገልጻሉ። 

በትግራይ ያሉ አርሶ አደሮች በማሳዎቻቸው ከሞከሯቸው የስንዴ ዝርያዎች መካከል ለወደዱት ለአንደኛው ስያሜ ሰጥተውታል፡፡ በስተኋላ ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎት ላይ እንዲውል የተመዘገበው ይህ ዝርያ “ዋሃቢት” የሚል ስያሜ አግኝቷል፡፡ በትግርኛ ቋንቋ ዋሃቢት ሁለት ትርጉም አለው፡፡ አንድም ሰጪ አሊያም የሚሰጥ ማለት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አጥተን የነበረውን መልሰን አገኘን የሚል ትርጓሜ ያዘለ እንደሆነ የደዋ ተምቤን አርሶ አደሮች ይናገራሉ፡፡ 

ዶ/ር ደጀኔ እና ባልደረቦቻቸው ለአርሶ አደሮች ካከፋፈሏቸው ዝርያዎች ውስጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደሚዘገብላቸው ጠይቀው የነበሩት ሶስት ዝርያዎችን ነበር፡፡ እነዚህ ዝርያዎች የተመረጡት በተለያየ መመዘኛ ተፈትነው ብልጫ በማሳየታቸው እንደሆነ ዶ/ር ደጀኔ ይገልጻሉ፡፡ “እነኚያ ዝርያዎች አንደኛው ምርታማነታቸው፣ ካሉን ዝርያዎች በዚህ እኛ በምንሰራበት በትግራይ ክልል የተሻሉ ሆነው ስላገኘኛቸው ነው፡፡ ሁለተኛ ትግራይ ክልል እንደምታውቀው የዝናብ አጠር አካባቢ ነው፡፡ አልፎ አልፎም ቢሆን ድርቅ የሚያጠቃበት ነው፡፡ ያንን የመቋቋም ችሎታቸው በየጊዜው በምርምር ማዕከላትም፣ በገበሬዎች ማሳ ላይም በተለያዩ ቦታዎች ፈትነናቸው በመቋቋም ብልጫ ያሳዩ ናቸው፡፡ ሶስተኛ የዋግ በሽታ መቋቋም የሚችሉ ናቸው” ሲሉ መመዘኛዎቹን ይዘርዝሯቸዋል፡፡

አዳዲሶቹ ዝርያዎች ይቋቁሙታል የተባለው የዋግ በሽታ ፈንገስ በሚባሉ ጥቃቅን ተባዮች የሚከሰት ነው፡፡ እርጥበት አዘል እና ሙቀት ያለው የአየር ጸባይ ለፈንገሱ አመቺ ሁኔታዎች እንደሚፈጥር ዶ/ር ደጀኔ ይናገራሉ፡፡ በሽታው በስንዴ ስለሚያደርሰው ጉዳትም ማብራሪያ አላቸው፡፡ 

“ሰውን የሚያጠቁ በሽታዎች አሉ፡፡ የቫይረስ፣ ባክቴሪያ እና ሌሎችም፡፡ እንደዚያው ሁሉ ሰብሎችን የሚያጠቁ አሉ፡፡ ከእነርሱ የሚመጣ ነው፡፡ [በሽታው] የተለያየ ተጽዕኖ ያመጣል፡፡ አንደኛ ቅጠሉ ላይ ይሰፍሩ እና ቅጠሉን ነው የሚበሉት፡፡ እህሉ ወይም ስንዴው ምግቡን የሚያዘጋጀው በቅጠሉ ነው፡፡ ስለዚህ አንደኛ ምግቡን እንዳያዘጋጅ ያደርጉታል፡፡ photosynthesis የምንለው አለ እርሱን ይዘጉታል፡፡ ሁለተኛ ለምርታማነት ብሎ ያዘጋጀውን ምግቡን ይሻሙታል፤ ይበሉታል፡፡ ጥገኛ ናቸው በባህሪያቸው እህሉ የሚያመርተው ማንኛውም ነገር ይበላሉ፡፡ ምግቡን እንዳያዘጋጅ ያደርጉታል፡፡ ሶስተኛ ደግሞ ሰብል ውስጥ የውሃ መተላለፊያ ቱቦዎች አሉ፡፡ ሲከፋ  ውሃ እንዳይተላለፍ ይዘጉና ሰብሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ” ይላሉ።

አዳዲሶቹ ዝርያዎች የዋግ በሽታን እንዴት እንደሚቋቋሙ ለተጠየቁት ዶ/ር ደጀኔ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ “በሽታን መቋቋም በሁለት ይከፈላል፡፡ አንደኛው በእንግሊዘኛው አጠራሩ vertical resistance የሚባለው ነው፡፡ ይሄ ሙሉ ለሙሉ መቋቋም መቻል ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ horizontal resistance የሚባለው ነው፡፡ በተወሰነ መልኩ የተወሰነ የመጠቃት ባህሪ አለው ግን አብዛኛውን የበሽታ ዓይነቶችን መቋቋም የሚችሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ዝርያዎች ይሄ vertical የሚባለው ሳይሆን horizontal resistance የሚባለው ያላቸው ናቸው፡፡ እኛ ደብረዘይትም ልከን አስመርምረናቸዋል፡፡ የተለያየ pathogens ሲመጡ መቋቋም የሚችሉ ዝርያዎች ናቸው” ሲሉ ያብራራሉ።  

በሀገር አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኙት ሁለቱ የስንዴ ዝርያዎች አሁን በሙከራ ደረጃ ካሉባቸው የትግራይ እና የአማራ ክልል አካባቢዎች ተሻግረው ወደ ሌሎች ቦታዎች ሲዳረሱ በፓስታ እና ማካሮኒ ስንዴ ላይ ያለውን እጥረት ይቀርፈዋል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ኢትዮጵያ ለፓስታ እና ማካሮኒ ምርት የሚውለውን ዱረም የተባለውን ስንዴ ከውጭ ሀገር ለማስገባት በዓመት እስከ አራት ሚሊዮን ዶላር እንደምታወጣ ዶ/ር ደጀኔ ይናገራሉ፡፡ ይህን ለማስቀረትም የእርሳቸውን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ምርምር በመካሄድ ላይ እንዳለ ይገልጻሉ፡፡ ምርምር ከሚሄድባቸው ቦታዎች ውስጥ ባሌ፣ አርሲ፣ ወሎ፣ ጎንደር እና ጎጃም እንደሚገኙበት ይጠቅሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ የዱረም ስንዴ ምርት ዝቅተኛ የሆነባቸውን ምክንያቶች የሚዘርዝሩት ዶ/ር ደጀኔ ወደፊት እየጨመረ በመጣው የሀገር ውስጥ ምርት የተሻለ ነገር እንደሚመጣ ተስፋ ያደርጋሉ። 

“የፓስታ እና ማካሮኒ ስንዴ በጣም ብዙ የተለያየ አይነት ያላቸው ብዙ ሀብት ቢኖረንም ለረጅም ጊዜ ምርምራችን እዚያ ላይ ብዙም አትኩሮት አልሰጠም ነበር፡፡ [ከጎርጎሮሳዊው] 1980ዎቹ ጀምሮ የዳቦ ስንዴ በሀገራችን በከፍተኛ ደረጃ ታወቀ እና እነኚህ የማካሮኒ እና ፓስታ ስንዴ ከምርታማነት እንዲወጡ አድርጓል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ፓስታ እና ማካሮኒን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች በጣም እየተበራከቱ በመጡበት ጊዜ ፍላጎት እና አቅርቦት በጣም ተራርቆ ከውጭ ለማምጣት ተገድዷል፡፡ ስለእኛ ስንዴ ከዚህ በፊት ሲወሩ የነበሩ የተለያዩ ነገሮች አሉ፡፡ ጥራታቸው የደከመ ነው የሚባል ነገር ስላለ ፋብሪካዎች ከውጭ የማምጣቱ ነገር ላይ ያዘወትራሉ እና ያንን ለመቀየር በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለያየ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ እኛም ከአንዳንድ ፋብሪካዎች ጋር እየተነጋገርን ሀሳባቸውን እንዲቀይሩ እና ከእኛ ገበሬዎች ጋር እንዲሰሩ እያደረግን ነው እና ወደፊት ያንን መቀየር የምንችል ይመስለኛል” ሲሉ ተስፋቸውን ተስፋቸውን ያጋራሉ፡፡    

ተስፋለም ወልደየስ  

አዜብ ታደሰ   

Audios and videos on the topic