በሶርያ የአይ.ኤስ. መሪ አቡ ሰያፍ ተገደለ | ዓለም | DW | 16.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

በሶርያ የአይ.ኤስ. መሪ አቡ ሰያፍ ተገደለ

ራሱን «እስላማዊ መንግስት» በምኅፃሩ አይ.ኤስ. እያለ የሚጠራው ቡድን መሪ የነበረው አቡ ሰያፍ በአሜሪካን ልዩ የጦር ኃይል ተገደለ። የአሸባሪ ቡድኑን የነዳጅ ዘይት ሽያጭ እና ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን በበላይነት ይመራ ነበር የተባለው የአቡ ሰያፍ መገደል ለአይ.ኤስ. ትልቅ ኪሳራ መሆኑን አሜሪካን አስታውቃለች።

የዋይት ሃውስ ብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ በርናዴት ሜሃን አቡ ሰያፍ በተልዕኮው ወቅት ከአሜሪካን ልዩ ኃይል ጋር የተኩስ ልውጥ በሚያደርግበት ወቅት መገደሉን እና ተልዕኮው የተፈጸመው የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በማይጣረስ መልኩ ከኢራቅ ባለስልጣናት ጋር ሙሉ መግባባት ተደርሶበት መሆኑን ተናግረዋል።

ዩ.ኤስ. አሜሪካ በአይ.ኤስ. ላይ በምትወስደው ርምጃ የአሳድ መንግስት ጣልቃ እንዳይገባ ማስጠንቀቋን ያስታወሱት በርናዴት ሜሃን በተልዕኮው ከሶርያ መንግስት ጋር ምንም አይነት ትብብር አለማድረጓን አስታውቀዋል።

የአሜሪካን ልዩ ኃይል በምስራቃዊ ሶርያ አል አሚር የተባለ አካባቢ አቡ ሰያፍን እና ባለቤቱን ኡም ሰያፍን እንዲይዝ ትዕዛዝ እንደተሰጠው አርብ እለት የፔንታጎን ኃላፊ አሽተን ካርተር ተናግረው ነበር። ሰያፍ በአሸባሪ ቡድኑ የጦር ተልዕኮዎች ውስጥ ተሳትፎ እንደነበረውና ሕገ-ወጥ የነዳጅ ሽያጭንና የገንዘብ ቁጥጥርን ይመራ እንደ ነበር ካርተር በፔንታጎን ድረ-ገጽ ላይ ይፋ በሆነው የመከላከያ መሥሪያ ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል። ባለቤቱ ኡም በአሸባሪ ቡድኑ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፎ እንደነበራቸውና በቅርቡ በአሜሪካን ጦር ተልዕኮ ነጻ የወጡትን ወጣት የያዚዲ ሴቶችን በባርነት በመግዛት እጃቸው ሳይኖርበት አይቀርም ተብሏል።

ተልዕኮው ለአይ.ሲስ. ታላቅ ኪሳራ መሆኑን እና አሜሪካን ለአሸባሪዎች የሚመች ገነት እንዲኖር እንደማትፈቅድ አሽተን ካርተር ተናግረዋል።

ራሱን አይ.ሲስ. በማለት የሚጠራው አሸባሪ ቡድን እጅግ በተለጠጠ የሸሪዓ አተረጓጎም የሚያምን ሲሆን ሰፊ ሰሜናዊ የኢራቅ አካባቢዎችንና ሶርያን ይቆጣጠራል። ቡድኑ በቀጣናው ጽኑዕ በኾነ እስላማዊ ሕግጋት የሚተዳደር አገር የመመስረት እቅድ አለው።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ