በሶማልያ ጠረፍ እስካሁን ያልተወገደው የባህር ላይ ውንብድናና የመፍትኄ ሐሳብ፣ | ዓለም | DW | 09.04.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

በሶማልያ ጠረፍ እስካሁን ያልተወገደው የባህር ላይ ውንብድናና የመፍትኄ ሐሳብ፣

የአውሮፓው ኅብረት፣ የዩናይትድ ስቴትስ፣ የሩሲያ፣ የህንድና የሌሎችም አገሮች ባህር ኃይሎች በአደን ባህረ-ሰላጤ በኩል ቢሠማሩም ፣

default

የጀርመን ባህር ኃይል፣ ባለፈው የካቲት ወር ማለቂያ ገደማ በአደን ባህረ-ሰላጤ፤ የባህር ላይ ወንበዴዎችን በቁጥጥር ሥር እንዳዋሉ የሚያሳይ ፎቶግራፍ፣

ከሶማልያ በኩል የሚሠነዘረውን የባህር ላይ ውንብድና ፈጽሞ ሊገቱት አልቻሉም።

ለምሳሌ ያህል ትናንት ፣ አንዲት የአሜሪካ ዕቃ ጫኝ መርከብ ከሶማልያ ጠረፍ ማዶ፣ በባህር ላይ ላይ ወንበዴዎች ቁጥጥር ሥር መዋሏ የታወቀ ሲሆን፣ ካፒቴኑን ያገቱት ጠላፊዎችና የአሜሪካ ባህር ላይ እንደተፋጠጡ ይገኛሉ። እገታው እንዴት ሊያከትም እንደሚችል፣ የሚታወቅ ነገር የለም።

ሊገታ ስላልቻለው የባህር ላይ ውንብድናና መፍትኄው፣ ዋና ጽ/ቤቱ በለነደን የሚገኘውን የዓለም አቀፉን የባህር ላይ ንግድ ጉዳይ ቢሮ(IMB)ዋና ሥራ አስኪያጅ Mr. Pottengel Mukundan ን ፣ ተክሌ የኋላ በሰልክ አነጋግሮ የሚከተለውን አጠናቅሯል።

እጅግ ተፈላጊ በሆነው የንግድ መርከቦች መተላለፊያ በሆነው በአደን ባህረ ሰላጤና ከዚያም አልፎ በህንድ ውቅያኖስ የተሠማሩት የአውሮፓው ኅብረት ፣ የአሜሪካ ፣ የሩሲያ፣ የህንድ፣ የሌሎቹም አገሮች ባህር ኃይሎች፣ እንዴት የባህር ላይ ወንበዴዎችን መቆጣጠሩ ተሳናቸው? ለፖቴንጌል ሙኩንዳን ያቀረብኩላቸው የመጀመሪያው ጥያቄዬ ነበር።

«በጥቂቱም ቢሆን ተሣክቶልናል። የባህር ኃይሎች ዋና ትኩረት ፣ በዐቢዩ የባህር ጉዞ መሥመር ፣ በአደን ባህረ-ሰላጤ ላይ ሆኖ ቆይቷል። ካለፉት ጥቅምትና ኅዳር ወራት ወዲህ መርከቦችን የመጠለፉ ተግባር በአጀጉ እንዲቀነስ ለማድረግ ተችሏል። አደጋ ቢሠነዘርም፣ የባህር ላይ ወንበዴዎች፣ ድሮ ያደረጉት እንደነበረው፣ መርከቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ አልተሣካላቸውም።

ባለፈው አንድ ወር ተኩል የሆነው ሆኖ፣ ምንድን ነው---የባህር ላይ ወንበዴዎች ወደ ሶማልያ ምሥራቃዊ ጠረፍና የዐረብ ባህር በመሸጋገር ፣ ተግባራቸውን ማካሄድ መቀጠላቸው ነው። ከሶማልያ ጠረፍ ማዶ፣ በአንዳንድ ረገድ፣ ከ480-640 ኪሎሜትር(ከ 300-400 ማይሎች)ስፋት ያለውን ሰፊ ባህር ነው ለመቆጣጠር ጥረት የምናደርገው።እንደሚገባን፣ የባህር ኃይሎቹ፣ የባህር ላይ ወንበዴዎቹ የተሠማሩበትን አዲስ ዘዴ በመገንዘብ፣ መፍትኄውን መሻታቸው እንደማይቀር ነው። »።

በመንግሥታቱ የባህር ኃይሎች መካከል፣ የተብብሩ ጥንካሬ እስከምን ድረስ ነው?

«የተወሰነ ፣ ኃይልን የማስተባበር እርምጃ አለ። ይህም በአመዛኙ፣ የሚመራው በአውሮፓ የባህር ኃይል አስተባባሪ ማዕከል ነው። እነርሱ ናቸው የባህር ኃይሎችን ተግባር የሚያስተባብሩት። እርግጥ አሁን ካለው በላቀ ሁኔታ የበለጠ ማስተባበር ያስፈልጋል። ምክንያቱም፣ እርስዎ እንደጠቀሱት፣ በዛ ያሉ የባህር ኃይል ግብረ-ኃይሎችአሉና። እንደሚመሰለኝ፣ የአውሮፓው ኅብረት ነው፣ የማቀናጀቱን ተግባር ለማሣካት በመጣር ላይ ያለው። »

አንዳንድ የሶማልያን ይዞታ በጥሞና የሚከታተሉ ታዛቢዎች የባህር ላይ ውንብድና ፣ ምንጩ ፣ ህዝቡን ቀቢጸ-ተስፋ ያሳደረበት የመሰለው፣ እልባት ያልተደረገለት ውዝግብ ነው ይላሉ። በዚህ አስተያየት ይስማማሉ?

«እርግጥ ትክክል ነው። የባህር ላይ ውንብድናን ከእነአካቴው ለማስወገድ፣ ኀላፊነት ያለው ተግባሩን ማካሄድ የሚችል መንግሥት ሶማልያ ውስጥ ሲቋቋም ነው። ችግሩ ፣ እንደሚመስለኝ ይህን በሚመጡት 10 ዓመታት ማየት የምንችል አለመሆናችን ነው።

ጥቃቱ ባለፈው መጠን እስከቀጠለ ድረስ የንግድ መርከቦች ሥምሪት በተሣካ ሁኔታ ሊቀጥል አይችልም፣ የሶማልያ መንግሥት እስኪደረጅ ደግሞ ጊዜ የሚወስድ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ፣ የባህሩ መሥመር መጠበቅ አለበት ፣ በማንም ይህን ለማድረግ ችሎታ ባለው! በአሁኑ ጊዜ ይህን ማድረግ የሚችሉት ደግሞ በአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ ተግባራቸውን በማከናወን ላይ የሚገኙ የባህር ኃይሎች ናቸው።»

የባህር ላይ ውንብድናን በተሣካ ሁኔታ መታገል፣ ከሞላ ጎደል መፍትኄውን ማግኘት የሚቻለው ምን ቢደረግ ነው?

«የባህር ላይ ውንብድናን መታገል የሚቻለው፣በ ሁለት መንገድ ነው። በመጀመሪያ የመረከቦች ኀላፊዎች ፈተናው ምን እንደሆነና ችግሩ ዬት እንደሚያጋጥም ማወቅ ይኖርባቸዋል። የባህር ላይ ወንበዴዎቹ ወደ መርከብ እንዳይገቡ ፣ ዕድሉን መሥጠት የለባቸውም። ይህ ቀዳሚው እርምጃ ነው። 2ኛውና በጣም ጠቃሚው ፣ ጉዳዩ በሚመለከታቸው የባህር ኃይሎች መወሰድ ያለበት እርማጃ ፣(በአደን ባህር ሰላጤ በአርግጥ ተግባራቸውን በማካሄድ ላይ ናቸው፣ በዐረብ ባህርም ይህን ያደርጋሉ ብለን እንጠብቃለን፣)

የምንመክራቸው፣ ዋንኛዋን ፣ ወንበዴዎቹ፣ በጀልባዎች እንዲሠማሩ የምታስቸልውን «እናት» መርከብ ለይተው በማወቅና ነጥሎ ዒላማ በማድረግ ወደፊት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ጥቃቶችን እንዲያከሽፉ ነው። በተጨማር የሚፈለገው፣የባህር ላይ ወንበዴዎችንቹን መያዝና ማሠር ነው።»

ተክሌ የኋላ፣

ነጋሽ መሐመድ፣