በሶማሊያ የተባባሰው የአሸባብ ጥቃት | አፍሪቃ | DW | 30.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

በሶማሊያ የተባባሰው የአሸባብ ጥቃት

የሶማሊያው ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በሶማሊያ የተለያዩ አካባቢዎች ተከታታይ ጥቃቶች እየጣለ ነው። ከመካከላቸው ባለፈው ዓርብ ደቡብ ሶማሊያ ውስጥ በሚገኝ የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ጦር ሰፈር ላይ የተጣለውና 50 ሰላም አስከባሪዎች የተገደሉበት ጥቃት ይገኝበታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:12
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:12 ደቂቃ

በሶማሊያ የተባባሰው የአሸባብ ጥቃት

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የሶማሊያው ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ በሶማሊያ የተለያዩ ክፍሎች ጥቃት መጣሉንና ውጊያ መክፈቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። በነዚህ ጥቃቶችም ጥቂት የማይባሉ ሰላማዊ ሰዎች፣ በሶማሊያ የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪዎች እንዲሁም የሶማሊያ ወታደሮች ና የአሸባብ ሚሊሽያዎች ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረቶችም ወድመዋል። ከቅርብ ጊዜዎቹ የአሸባብ ጥቃቶች መካከል ደቡብ ሶማሊያ ውስጥ በሚገኝ የጦር ሰፈር ላይ ባለፈው ዓርብ የተጣለው ጥቃት አንዱ ነው። በዚህ ጥቃት ከ50 ሰላም አስከባሪዎች መገደላቸው ተዘግቦ ነበር። ይሁንና የዶቼቬለ የመቅዲሾ ተባባሪ ዘጋቢ ሞሀመድ ኦማር ሁሴን እንደሚለው አሁን የሟቾቹ ወታደሮች ቁጥር ከተነገረው በላይ ነው።
«ሌጎ በተባለው ከሶማሊያ ዋና ከተማ ከመቅዲሾ በስተምዕራብ 120 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ወታደራዊ የጦር ሰፈር በተለይ የብሩንዲ ሰላም አስከባሪዎች በነበሩበት ስፍራ ከሶስት ቀናት በፊት ጥቃት ደርሷል። በአካባቢው የነበሩት ወታደሮች 100 ይሆናሉ። ቅርብ ጊዜ ከአካባቢው የሚወጡ ዘገባዎች ቢያንስ 70 ያህል ወታደሮች መገደላቸውን ፤ 30 ው ደግሞ ወደ

ጫካ መግባታቸውን ያመለክታሉ። »
የአሸባብ ጥቃት የተከታተለው በተለይ የሙስሊሞች ጾም ሮመዳን ከገባ በኋላ ነው። ሞሀመድ እንደሚለው በዚህ ጊዜ የአሸባብ ጥቃት ተጠናክሮ የቀጠለበት ምክንያት አንድ ነው።
«ዋነኛው ምክንያት ልንል የምንችለው የሶማሊያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ህዝቡ የሮመዳንን ፆም በሰላም እንዲያሳልፍ እናደርጋለን ሲሉ ይናገራሉ። አሸባብ ደግሞ የባለሥልጣናቱን ንግግር የሚቃረን እርምጃ ይወስዳል። አሸባቦች በሮመዳን ጥቃት ማድረስ በፈጣሪ ፊት ከፍተኛ ዋጋ ያስገኛል ስለሚሉ ከሌሎቹ ጊዜያት ይልቅ በዚህ ጊዜ ጥቃት ይፈፅማሉ።»
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አሸባብ መዳከሙ ነበር ተደጋግሞ የሚሰማው። አሸባብ አሁን በሶማሊያ ተከታታይ ጥቃት ለማድረስ ያበቃው ምን ይሆን ? ይህስ እንደገና የመጠናከሩ ምልክት ይሆን ?

« ከመንግሥትም የደህንነት ስለላ በላይ ቀድመው ሄደዋል ማለት ይቻላል። ምክንያቱም የመንግሥት ወታደሮች ሌት ተቀን እየተዘዋወሩ ጥበቃ ቢያደርጉም እነዚህ ኃይሎች የአጥፍቶ ጠፊትዎችና ሌሎች ተመሳሳይ ጥቃቶችን መጣል ችለዋል። አንዳንድ ጊዜ ግን የአሸባብ ጥቃቶች ሊከሽፉ ይችላሉ ሆኖም ለምሳሌ 2 ጥቃቶች ማክሸፍ ቢቻል አሸባቦች 8 ጥቃቶችን ሊያደርሱ ይችላሉ። »
እንደ መሀመድ በሶማሊያ ለአሸባብ ጥቃት መጠናከር አስተዋፅኦ ያደረገ ሌላም ምክንያት ።
«እነዚህ ሰዎች ከቀን ወደቀን እየተጠናከሩ በመሄድ ላይ ናቸው። በሶማሊያ ግልፅ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች አሉ። እንደሚመስለኝ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው ISIS የተባለው ቡድን እየተጠናከረ መሄድ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ኃይሎች ባለፉት 2 ና 3 ወራት ISIS እየተጠናከረ ከሄደ በኋላ እየበረቱ የሄዱ ይመስላል።»

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic