በሶማሊያ ምርጫ የሴቶች ተሳትፎና የአውሮፓ ህብረት የአፍሪቃ ድጋፍ | አፍሪቃ | DW | 30.01.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

በሶማሊያ ምርጫ የሴቶች ተሳትፎና የአውሮፓ ህብረት የአፍሪቃ ድጋፍ

የአውሮፓ ህብረት ለአፍሪቃ ሀገራት ሰራዊት ወታደራዊ ስልጠና መስጠት የተለመደ ሲሆን፤በአዲሱ ማሻሻያ ግን የጦር መሳሪያ ማስታጠቅንም ያጠቃልላል።ተችዎች ይህ ድጋፍ አደገኛ ነው ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:20

ሴቶች ወደ ፖለቲካው እንዲመጡ ከፍተኛ ምኞት አለ

አሚና ሞሃመድ አብዲ  ለመጀመሪያ ጊዜ ለሶማሊያ ፓርላማ የተወዳድረችው በጎርጎሪያኑ 2012 ዓ/ም የ 24 ዓመት ወጣት ሳለች ነበር ። በዚያ ምርጫ  አሸናፊ ሆነችና በሀገሪቱ ፓርላማ ካሉት ጥቂት ሴቶች መካከል አንዷ ለመሆን በቃች።በአብዛኛው ወግ አጥባቂ የጎሳ ሽማግሌዎች በሚወስኑባት ሶማሊያ ሴቶች  ወደ ፖለቲካ እንዲመጡ  ብዙም ፍላጎት የለም። ያ በመሆኑ በወቅቱ  ለአሚና ሁኔታው ቀላል አልነበረም።

«ሴተኛ አዳሪ መሆን ትፈልጊያለሽ? ሲሉ ጠየቁኝ። አንዲት ሴት እንዴት ጎሳን ትወክላለች? አሉኝ። እኔ ግን  አንድ ጎሳ በወንዶች ብቻ የሚወከል አይደለም። በማለት አጥብቄ ተቃወምኩ። »ብላለች።

አሚና አሁን የ 32 ዓመት ሴት ስትሆን፤ በመንግስት ላይ የሰላ ትችት ከሚያቀርቡ ሰዎች መካከል አንዷ ነች። በመጭው የጎርጎሪያኑ የካቲት 8  ቀን ለተቆረጠለት  የፓርላማ እና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ  ለሦስተኛ ጊዜ ለመወዳደር ትፈልጋለች። ለተመሳሳይ ወንበር ከሚወዳደሩ  ስድስት እጩዎች መካከልም ብቸኛዋ ሴት ነች ፡፡ 

ከጎርጎሪያኑ ከ1991 ዓ/ም ወዲህ ስሟ ከግጭት ጋር የተቆራኘው ሶማሊያ  ፖለቲካዋ በወንዶች የበላይነት የተያዘ ነው።329 መቀመጫዎች ባሉት የሶማሊያ የበታችና ከፍተኛ ምክር ቤቶች ውስጥ በአሁኑ ወቅት  24 በመቶው በሴቶች የተያዘ ነው። 

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሃመድ ሁሴን ሮቤል በጥር  ወር አጋማሽ እንዳስታወቁት በመጭው የካቲት ወር  በሚደረገው ምርጫ  አንድ ሦስተኛው የምክር ቤቱ መቀመጫ  በሴቶች የሚያዝ ይሆናል። የሴቶች መብት ተሟጋቾች ይህ እንዲሆን ለረጅም ጊዜ  ሲታገሉ  ቆይተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከምርጫ ህጉ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ማሻሻያ በሀምሌ 2020 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀ ሲሆን፤የላዕላይ ምክር ቤቱና የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ደግሞ እየጠበቀ ነው። 

«ሂር ውመን»በመባል የሚጠራው የሴቶች መብት ተሟጋች ድርጅት ሊቀመንበር የሆኑት ደቃ አብዲቃሲም ሰላድ ግን ስለ ተግባራዊነቱ ይጠራጠራሉ።እንዲያውም በዚህ ምርጫ የሴቶች ተሳትፎ ከነበረው 24 በመቶ በታችም ሊወርድ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው። ምክንያቱም በሀገሪቱ ለሴቶች የሚሰጥ «ኮታ» ወይም የልዩ ተጠቃሚነት ዕድልን በተለከተ የወጣ  ህግ የለም።ለዚህም «እኛ ሴቶች ጉዳዩ በሕገ-መንግስቱ ውስጥ እንዲካተት በቂ ግፊት ባለማድረጋችን» ስህተት ሰርተናል ይላሉ።

«ፓርላማ ውስጥ ያሉ ሴቶችና የሲቪሉ ማኅበረሰብ ማድረግ ያለባቸው ።የ30 በመቶን አጀንዳ የበለጠ መግፋትና በህገመንግስቱ መፃፉን ማረጋገጥ አለባቸው።የሴቶች እና የሲቪል ማህበራት ይህንን ባለማድረጋቸው የኛ የሴቶች  ስህተት  አድርጌ ነው የምመለከተው። አጀንዳውን መግፋትና  በሕገ-መንግስት ውስጥ የተካተተ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።ያ ከሆነና በህገ መንግስቱ ከሰፈረ፤ ፖሊሲውን በቀላሉ ማፍረስ አትችልም።ነገር ግን አሁን እየተባለ ያለው ፖሊሲ ሳይሆን ምክረ ሀሳብ ነው።»

የቀድሞዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ፎዚያ ዩሱፍ ሀጅ በበኩላቸው  የልዩ ተጠቃሚነት ዕድል ለሶማሊያ ሴቶች አስፈላጊ እርምጃ ነው ይላሉ።ይህም ሴቶችን ወደ ምክር ቤት ለማስገባትና የሚወክሉትን የሕብረተሰብ  ክፍል በትክክል ለማንፀባረቅ ይረዳል ብለዋል። ፎዚያ ፤በ2012  የሀገሪቱ  የመጀመሪያ ሴት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ሰርተዋል።በአሁኑ ጊዜ  ከሌሎች ሀላፊነቶች በተጨማሪ የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ናቸው።ሴቶች ወደ ፖለቲካው እንዲመጡ ከፍተኛ ምኞት ያላቸው ሲሆን፤ ወደ ፖለቲካው ሲገቡ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮችም በደንብ ያውቃሉ ፡፡ 

«ተግዳሮቶቹ በሶማሊያ ማለቂያ የሌለው ግጭት ፣ የሰላምና መረጋጋት እጦት እንዲሁም ሁሉንም የልማትና ዴሞክራሲያዊ ሂደቶች ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩ የአልሸባብ አሸባሪዎች ናቸው ።ሌላው ምክንያት ለብዙ  የፖለቲካ ፍላጎት ላላቸው ሴቶች  የገንዘብ ድጋፍ አለመኖሩ ነው።»

በመጪው ምርጫ  ለምክር ቤት የሚወዳደር እያንዳንዱ ሰው ከ 10,000 እስከ 20,000 የአሜሪካ ዶላር የምዝገባ ክፍያ መክፈል አለበት።ቀደም ሲል እንደታየው በድርጅቶችና እና በጎሳ አባላት የገንዘብ ድጋፍ ከተደረገላቸው ወንድ ባልደረቦቻቸው ጋር ሲነፃፀር ገንዘብ ማግኘት ለሴቶች በጣም ከባድ ነው። 

ከዚህ በተጨማሪ የሶማሊያ የሶማሊያ 4.5 የሚባለው ፖሊሲና የሽማግሌዎች መርህም ሌላው ችግር ነው።በ 4.5 ፖሊሲ መሠረት የፓርላማ አባላቱ በሕዝብ የተመረጡ ሳይሆኑ  በሽማግሌዎች  የተመረጡት የጎሳ ልዑካን ናቸው። ልዑካኑ ራሳቸው የጎሳ ሽማግሌዎችን ያካተቱ ሲሆን 30 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እና 20 በመቶው ወጣቶችንም ያካትታል።በሶማሊያ የሚገኙት አራቱ ታላላቅ ጎሳዎች በፓርላማ ተመሳሳይ ቁጥር ሲኖራቸው፤ ትናንሽ ጎሳዎች ደግሞ ግማሹን ያገኛሉ። በዚህ የጎሳ መርህ  ለብዙ ሴቶች በምርጫ  ተፎካካሪ መሆን  ከባድ ነው።በዚህ የተነሳ የሶማሊያ 4.5 ፖሊሲ እስካለ ድረስ ልዩ ጥቅም ሴቶችን አይጠቅምም ይላሉ   

«ልዩ ተጠቃሚነትን ስንመለከት  የ 4.5 መመሪያ በሶማሊያ እስካለ ድረስ  የልዩ ተጠቃሚነት ዕድል ለሴቶች የሚጠቅም አይሆንም።ምክንያቱም በ 4.5 መርህ መሰረት ወደ ፓርላማ ማን መሄድ እንዳለበት የሚወስኑ የጎሳ ሽማግሌዎች ናቸው።እነሱ ደግሞ ሴቶች ያንን ጎሳ ወክለው የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረጋቸውን አያምኑበትም።»

በመሆኑም ሶማሊያውያን በመጪው ምርጫ  «የአንድ ሰው አንድ ድምፅ» ስርዓት ተግባራዊ እንዲሆን ይሻሉ።ሉል ኢሳክ አዳን ከዚህ ዓመት  ዕጩ ተወዳዳሪዎች ውስጥ አንዷ ናቸው።እሳቸው እንደሚሉት ሴቶች በኃይልና በገንዘብ ረገድ ከወንዶች ያነሰ ብቃት እንዳላቸው አድርጎ የማየት ጭፍን ጥላቻም ትልቁ ችግር ነው።በዚህ የተነሳ አንዳንድ ጎሳዎች እና ንዑስ ጎሳዎች ምርጫ ላይ ወንዶችን እንዲደግፉ በሽማግሌዎቻቸው ላይ ጫና ያሳድራሉ።ያም ቢሆን  ሉል ኢሳቅ አዳን ለዶቼ ቬለ DW እንደተናገሩት  እንደሚያሸንፉ ተስፋ ያደርጋሉ።

እንደ ሩዋንዳ ባሉ ሀገራት የሴቶች ልዩ ተጠቃሚነት ተስፋ ሰጪ ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል።ከ2003 ዓ/ም ጀምሮ 30 በመቶ የሴቶች ድርሻ በሕገ-መንግስቱ የተደነገገ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 61 በመቶ የፓርላማ አባላት ሴቶች ናቸው ፡፡

የሶማሊያ ስፖርት እና ወጣቶች ሚኒስትር ሀምዛ-ሰይድ-ሀምዛ  በሶማሊያ እንዲህ ዓይነቱ ለውጥ እንዲመጣ ይመኛሉ። ነገር ግን  ይላሉ ሚንስትሯ በሶማሊያ  ይህንን መሰሉን የሴቶች እኩልነት ለማረጋገጥ የሚቀረው መንገድ በጣም ብዙ ነው።

ለአፍሪቃ ሰላምና ፀጥታ የአውሮፓ ህብረት ድጋፍ 

የአውሮፓ ህብረት ለአፍሪቃ የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርግባቸው ጉዳዮች አንዱ  የሰላምና የፀጥታ ዘርፍ አንዱ ነው።ከዚህ ጋር ተያይዞ የአውሮፓ ህብረት በአፍሪቃ የሰላም ተቋም በኩል  በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለተሰማሩ የአሚሶም ወታደሮች ብቻ እስካሁን ከ1 5 ቢሊዮን በላይ ዮሮ  እገዛ ማድረጉን መረጃዎች ያሳያሉ።ከዚህ በተጨማሪ ህብረቱ እንደ አሚሶም ያሉ የአፍሪቃ ህብረት የሰላም ጥረቶችንና በህብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ የሚሰሩ ሌሎች ተጓዳኝ መዋቅሮችን ለመደገፍ  በ2019 ዓ/ም ብቻ 2,7 ቢሊዮን ዮሮ ድጋፍ ሰጥቷል።ያምሆኖ ይህ የገንዘብ ድጋፍ  አሚሶምን ማጠናከር አልተቻለም።ሶማሊያም ብትሆን ተረጋግታ በሁለት እግሯ የቆመች ሀገር መሆን አልቻለችም።ከዓለም አቀፉ የቀውስ ተንታኝ ድርጅት ሊሳ ሙሲዮል እንደሚሉት ህብረቱም ቢሆን በዚህ ልገሳ የተሳለቸ ይመስላል።

«የአውሮፓ ህብረት አሚሶምን ለመሳሰሉ  የሶማሊያ አፍሪካ ህብረት ተልዕኮዎች ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ለዓመታት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል ። ነገር ግን የአውሮፓ ህብረትም በዚህ የገንዘብ ልገሳ ግንኙነት ወጥመድ ውስጥ  የገባ ያህል ተሰምቶታል።»

በጎርጎሪያኑ 2018 የአውሮፓ ኦዲተሮች ፍ/ቤትም የአውሮፓ ህብረት ለአፍሪካ ሰላምና ደህንነት የሚያደርገው ድጋፍ «እምብዛም ውጤት ያላመጣ በመሆኑ»ህብረቱ  አካሄዱን በፍጥነት  መመርመር እንደሚያስፈልገው ገልጿል። የአውሮፓ ህብረትም እንደበፊቱ መቀጠል አይፈልግም።ስለሆነም ሰፊ የማሻሻያ ሂደት እያካሄደ ነው።ለወደፊቱ የዘመቻዎቹን ስራ ማስኬጃ  ወጪዎች መደገፉን በማቆም  የአፍሪካን ጦር በተለያዩ ሙያዊ እገዛዎች ለማጠናከር ይጥራል።አፍሪካዉያንም ቢሆን ማሻሻያ ይፈልጋሉ።የክልሎች ህብረት ከአሁን በኋላ በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ለሚነሱ ጥያቄዎች በውጭ ለጋሾች ጥገኛ መሆን አይፈልግም።የደቡብ አፍሪካ የፀጥታ ጥናት ኢንስቲትዩት  ባልደረባ የሆኑት ፖል-ሲሞን ሃንዲ «ከዚህ አንፃር የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካን ፍላጎትና ምኞት እየተከተለ ነው» ብለዋል።  

«የዚህ ማሻሻያ ዋና ዓላማ ከሆኑት ውስጥ አንዱ  የአፍሪካን ሰላምና ደህንነት  በገንዘብ በመደገፍ ረገድ  የተሻለ አፍሪካዊ ባለቤትነትን ማምጣት ነው። ስለዚህ ከዚህ አንፃር የአውሮፓ ህብረት እየተከተለ ያለው  የአፍሪካ ምኞትና እየጨመረ የመጣውን  ራስን የመቻል ፍላጎት ነው።» 

ስለሆነም «የአፍሪካ የሰላም ተቋም» በዚህ ዓመት «የአውሮፓ የሰላም ተቋም» ይሆናል ፡፡ ይህ ከቀላል የስም ለውጥ በላይ ነው።ከአሁን በፊት የአውሮፓ ህብረት እርዳታ በአፍሪካ ህብረት በኩል ይደርስ የነበረ ሲሆን፤ለወደፊቱ ግን በቀጥታ በአፍሪካ ውስጥ ለሚገኙ  ክልሎች ፣ ሀገሮች ወይም ሰራዊት ጋር በቀጥታ ሊሰራ ይችላል።ፖል ሲሞን ሃንዲ «ይህ ለአውሮፓ ህብረት የበለጠ የመንቀሳቀስ ነፃነትን ሲሰጥ ለአፍሪካ ህብረት ግን ከሌሎች ተዋንያን ጋር የበለጠ ውድድር ይጠብቀዋል» ብለዋል። 

በዚህ ለውጥ አምስቱን የሳህል ሀገራት ህብረትን የመሳሰሉ አካባቢያዊ ህብረቶችና ድርጅቶች ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል።ሃንዲ እንደሚሉት ደግሞ ይህ ለውጥ የአፍሪካ ህብረት በአፍሪካ ሰላም እና ደኅንነት ያለውን ተሳትፎ ግን ሊቀንስ ይችላል ። 

ሌላው በአፍሪቃ ተፅዕኖ ይፈጥራል የተባለው አዲሱ ማሻሻያ የአውሮፓ ህብረት ለወደፊቱ የአፍሪካ ሀገሮችን ሰራዊት የጦር መሳሪያ ያስታጥቃል መባሉ ነው።ህብረቱ የአፍሪቃ ሀገራትን ሰራዊት ወታደራዊ ስልጠና መስጠት የተለመደ ሲሆን፤በአዲሱ ማሻሻያ ግን የጦር መሳሪያ ማስታጠቅንም ያጠቃልላል።ተችዎች ግን ይህ ድጋፍ አደገኛ ነው ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

«የአውሮፓ ህብረት የደህንነት ስጋት ባለባቸው የአፍሪካ ሀገሮች ለጥፋት የሚዳርግ መሳሪያ ለመስጠት ሲያስብ በጣም መጠንቀቅ አለበት።በእኛ እይታ በእነዚህ ተጎጂ ሀገሮች ውስጥ የጦር መሳሪያዎች እና ጥይቶችን ከመደገፍ ሙሉ በሙሉ መቆጠብ አለበት። ምክንያቱም መሳሪያዎቹን ያለአግባብ የመጠቀም አደጋ ወይም  በተሳሳቱ እጆች ላይ በመውደቅ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎች ፤ይህ ድጋፍ ሊሰጥ ከሚችለው ጥቅም በላይ ነው።»ብለዋል ከዓለም አቀፉ የቀውስ ተንታኝ ቡድን ሙሲኦል።

መሲኦል አያይዘውም ይህ መሰሉ የህብረቱ ርምጃ ያልተፈለገ ውጤት ያመጣል ሲሉም ይከራከራሉ።ለዚህ ከሚያቀርቡት ምክንያትም ቀደም ሲል ጀርመንን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረት ወታደሮች ማሊና ሶማሊያን በመሳሰሉ ሀገሮች ባደረጉት ወታደራዊ ድጋፍ የማሊው ወታደራዊ አዛዥ ኬታ ባለፈው ነሀሴ በሀገሪቱ መፈንቅለ መንግስት ሲያካሂዱ፤በሶማሊያ የሰለጠኑ በርካታ ታጣቂዎች ደግሞ ከስልጠና በኋላ እስላማዊ ሚሊሺያ አልሸባብን ወይም የባህር ዳርቻ ወንበዴዎችን መቀላቀላቸውን ያስታውሳሉ። እናም ከህብረቱ በተገኙ ዘመናዊ መሳሪያዎች እንደነዚህ ያሉ ቡድኖች በጣም በከፋ ሁኔታ የከፋ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ።በማለት የህብረቱን እርምጃ አደገኝነት ያስረግጣሉ። 

 

ፀሀይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ

 

Audios and videos on the topic