በስጋት ውስጥ የሚገኙት የዩንቨርስቲ ተማሪዎች | ወጣቶች | DW | 15.11.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

በስጋት ውስጥ የሚገኙት የዩንቨርስቲ ተማሪዎች

ሰሞኑን ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ  አንዳንድ ዩንቨርስቲዎች  የተካሄዱት ብሔር ተኮር ግጭቶች  የተማሪዎች ህይወት እስኪጠፋ የዳረጉ ነበሩ ። አሁን ድረስም የመማር ማስተማር ስራው የተቋረጠባቸው ዮንቨርስቲዎች አሉ። ዮንቨርስቲ ተማሪዎች ስጋታቸውን አካፍለውናል።  

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:27

በስጋት ውስጥ የሚገኙት የዮንቨርስቲ ተማሪዎች እና የመቀራረባቸው ተስፋ

ባለፈው ሳምንት ከወልዲያ ዩንቨርስቲ  ሁለት ተማሪዎች ከተገደሉ በኋላ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩንቨርስቲዎች ብሔር ተኮር የፖለቲካ ግጭት ተጠናክሮ መቀጠሉ ተሰምቶአል። በተመሳሳይ ግጭት ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ አንድ ተማሪ መገደሉን ዩኒቨርስቲው አስታውቋል። የጅማ፣ ሀሮማያ፣ ድሬደዋ እና መቱ ዩንቨርስቲዎችም ግጭቶች ታይተዋል። አንዳንድ ተማሪዎች ግጭትና ጥቃትን ሸሽተዉ በቤተ-ክርስትያናት ተጠጥለው እንደሚገኙ እየተዘገበ ነዉ። የትምህርት ተቋማትንም በስጋት ለቀው የሚሄዱ እንዳሉ የዓይን እማኞች ለ«DW» ገልፀዋል። ሰሞኑን ግጭት ከተቀሰቀሰባቸዉ ዩንቨርስቲዎች መካከል ከወልዲያ ዩኒቨርስቲ ያነጋገርናቸው ወጣቶች እንደገለፁልን ግጭቱ አሁንም ቀጥሏል። በርካቶች እንደሚሉት ተማሪዎች የሚያድሩት ውጪ ሜዳላይ ተሰብስበው ነው። በወልድያ ዩንቨርስቲ የ4ኛ ዓመት ተማሪ እንደሆነ የገለፀልን ወጣት ሌላ ግጭት እንዳይፈጠር በመስጋት ወደ መመገቢያ አዳራሽ እንኳን ስለማንሄድ የምግብ ችግር ገጥሞናል ይላል።« እንሂድ ብንል እንኳን የምንሄድበት መንገድ የለም።መንገዱ ተዘግቷል። ውኃም ምግብም እያገኘን አይደለም» ይላል። የሁሉንም ተማሪዎች ስም ለደህንነታቸው ስንል አንጠራም። ወጣቱ በአሁኑ ሰዓት መፍትሔ ነው የሚለው ተማሪዎች ወደ እየክልላቸው የሚላኩበት መንገድ ቢመቻች ብቻ ነው።

ወደዚሁ ዩንቨርስቲ ከደቡብ ክልል ለመማር የሄደው ሌላው ወጣት ደግሞ ስጋቱን እንዲህ ያስረዳል። « ከቅዳሜ ጀምሮ እስካሁን ምግብ አልተበላም። ውጪ ነው የምናድረውም።»ምንም እንኳን የፌደራል ፖሊስ ግቢ ቢገባም ለተማሪው ችግር መፍትሄ ሊሆን አይችልም የሚለው ወጣት የሚያወያየን አካል እንሻለን ይላል።

Äthiopien Haramaya Universität

የሀሮማያ ዮንቨርስቲ ሰሞኑን ግጭት ከተካሄደባቸው ከፍተኛ ተቋማት አንዱ ነው

ውይይትም ሳይሆን ወደ ቤተሰቦቻችን ይመልሱን የምትለው ሴት ተማሪ ደግሞ ከዚያው ዩንቨርስቲ ሐሙስ ዕለት ሌላ ተማሪ መገደሉን ታስረዳለች። « ዛሬ ጠዋት በተከፈተው ተኩስ አንድ ሰው ሞቶብናል። የምናድረው በብርድ ሜዳ ላይ ነው። እህቶቻችን የመድፈር ሙከራ እየተደረገባቸው ነው። ከሚታሰበው በላይ እየተጉላላን ነው።» ተማሪዎቹ እንደሚሉት ከሆነ ግን ካለፈዉ ቅዳሜ በፊት ሁሉም ተማሪዎች በሰላም እየኖሩ ነበር።እንደ ወልዲያ ዩንቨርስቲ በመቱ ዩንቨርስቲም የመማር ማስተማሩ ሁኔታ ተቋርጧል። እዛም ያሉ ተማሪዎች ስጋታቸውን ገልፀውልናል። « ምንም ሰላም የለም። ተማሪው እራሱ ተሰባስቦ አንድ ላይ ሆነ እንጂ ምንም እንደዚህ ሁኑ ያለን አካል የለም። አሁን ትንሽ ፌደራል ገብቶ ዙሪያውን እየጠበቀ ይገኛል።» የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ እንደሆነ የገለፀልን ይሄው ወጣት ሁኔታው የመረጋጋቱ ሁኔታ አጠያያቂ ቢሆንም አማራጭ አጥተን እየጠበቅን ነው ብሎናል። ሌላው አብሮት ያለው ወጣት ደግሞ የሚመለከተው አካል ይድረስልን ባይ ነው። « በመሞት እና በመኖር መካከል ነን» ይላል።ከትግራይ ክልል ወደ ደብረ ማርቆስ ከተማ ሄዶ ትምህርቱን እየተከታተለ እንደሚገኝ የገለፀልን የ5ኛ ዓመት ተማሪ እሱ ባለበት ዩንቨርስቲ በአንፃሩ የተረጋጋ ሁኔታ ቢኖርም አስተማማኝ ነው ለማለት አይደፍርም። « በሌላ ግቢ ይህ ተፈጥሯል ሲባል ፍርሃት አለ ወደዚህ ቢመጣስ በሚል» ይላል።

Junge Menschen in Äthiopien

በተለያዩ ዩንቨርስቲዎች ሰላምን ለማስፈን እና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸዉ እንዲመለሱ የማረጋጋት ስራ እየተሰራ እንደሆነ ይነገራል። አሁን ባለበት ሁኔታ ተማሪውን ከተከፋፈለበት የብሔር አስተሳሰብ ማላቀቅ ወይም ማግባባት ይቻል ይሆን?  በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአዕምሮ ህክምና ትምህርት ክፍል መምህር እና ሐኪም ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ አሁንም እድል እንዳለ ይናገራሉ። « እዚህ ሁኔታ ላይ መደረሱ የወጣቶች ጥፋት ነው ብዬ አላስብም። ወጣቶች አሁንም ይመለሳሉ፣ መድረኩ ከተሰጣቸው እርስ በዕርሳቸው ተነጋግረው ነገ ለሚረከቧት ሀገራቸው ኢትዮጵያ ሰላምን ይፈጥራሉ ብዬ አስባለሁ» ይላሉ። የአዕምሮ ህክምና ትምህርት መምህር እና ሐኪም የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን እንደሚሉት ምንም እንኳን በአሁኑ ሰዓት ግጭት የሚፈጥሩት ወጣቶች ጎልተው ቢታዩም አብላጫው የኢትዮጲያ ወጣት ስለሀገሩ እና ስለእምነቱ የሚያስብ መሆኑ ተስፋ ሰጪው ነገር ነው።

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች