በሴይንት ፒተርስበርግ የከ/ምድር ባቡር ላይ የደረሰ ፍንዳታ | ዓለም | DW | 03.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

በሴይንት ፒተርስበርግ የከ/ምድር ባቡር ላይ የደረሰ ፍንዳታ

በሩስያ በአንድ የሴይንት ፒተርስበርግ ከተማ የከርሰ ምድር ባቡር ሁለት ፉርጎኖች ላይ በደረሰ የፍንዳታ አደጋ ወደ አስር የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸው እና 47 መቁሰላቸውን የከተማይቱ የፀጥታ እና የጤና ጥበቃ ባለስልጣናት አስታወቁ።

በሩስያ በአንድ የሴይንት ፒተርስበርግ ከተማ የከርሰ ምድር ባቡር ሁለት ፉርጎኖች ላይ በደረሰ የፍንዳታ አደጋ ወደ አስር የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸው እና 47 መቁሰላቸውን የከተማይቱ የፀጥታ እና የጤና ጥበቃ ባለስልጣናት አስታወቁ። የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላዲሚር ፑቲን ከፍንዳታው በኋላ እንዳመለከቱት፣ የፍንዳታው ምክንያት ገና በውል አልታወቀም፣ የአደጋውን መንስዔ ምንነት፣  ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዘ መሆን አለመሆኑም ጭምር እየተመረመረ መሆኑን አስረድተዋል።  የሩስያ ይፋ የዜና ወኪል «ኢንትርፋክስ» ባወጣው ዘገባ መሰረት፣ መንስዔው ጓዳ ሰራሽ ቦምብ ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል።  ፍንዳታውን ተከትሎ በከተማይቱ የከርሰ ምድር ባቡር ጣቢያዎች በጠቅላላ ተዘግተዋል፣ የከተማይቱ የመጓጓዣ አገልግሎት ሰጪ ዘርፎች ጥበቃም ተጠናክሮዋል። ከቤላሩስ አቻቸው አሌግዛንደር ሉካሼንኮ ጋር ዛሬ በሴይንት ፒተርስበርግ ከተማ የተገናኙት የሩስያ ፕሬዚደንት ፑቲን ለሟቾች ቤተሰቦች ልባዊ ሀዘናቸውን በመግለጽ ጉዳዩ እንደሚጣራ አረጋግጠዋል።


«  የአደጋውን መንስዔ ለይተን ለማወቅ የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፣ ከዚያ ምን እንደሆነ ሙሉ  ማብራሪያ እንሰጣለን። የከተማይቱ እና የፌዴራል ባለስልጣናትም የሟቾችን ቤተሰቦች እና የቆሰሉ ዜጎቻችንን ለመርዳት አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋሉ። » 
 የሩስያ ፀጥታ ኃይላት በከተማይቱ ማዕከል በሚገኝ አንድ ሌላ የከርሰ ምድር ባቡር ጣቢያ ሌላ ፈንጂ አግኝተው ማክሸፋቸውን ብሄራዊ ፀረ ሽብር ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በከርሰ ምድር ባቡር ጣቢያ የተተከሉ የመቆጣጠሪያ ካሜራዎች በሁለት ፉርጎናች ላይ የደረሰውን ፍንዳታ ሳያቀነባብር አልቀረም ተብሎ የሚጠረጠር አንድ ግለሰብ ምስልን መቅረጻቸውን በመጨረሻ የወጣ የ«ኢንተርፋክስ» ዘገባ አስታውቋል።