በሴኔጋል የተመረጠው አዲሱ ምክር ቤት | አፍሪቃ | DW | 07.07.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

በሴኔጋል የተመረጠው አዲሱ ምክር ቤት

በሴኔጋል ፕሬዚደንት ማኪ ሳልን ለዚሁ ከፍተኛ ሥልጣን ያበቃው ቤኖ ቦክ ያር የተባለው የፓርቲዎች ጥምረት በከፍተኛ ድምፅ አሸነፈ። ጥምረቱ፡ በምርጫው ውጤት መሠረት፡ ከ150 የምክር ቤት መንበሮች መካከል 119 በማግኘት አብላጫውን መንበሮች ይዞዋል።

የሴኔጋል ሕዝብ ማኪ ሳልን ባለፈው መጋቢት በተካሄደ ጠንካራ ፉክክር በነበረበት ምርጫ ነበር ፕሬዚደንት አድርጎ የመረጣቸው። ፕሬዚደንት ሳል ከርሳቸው በፊት የነበሩትን ሀገሪቱን ለአሥራ ሁለት ዓመታት በፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት የመሩትን ፕሬዚደንት አብዱላይ ዋድን ተክተዋል። እስከቅርብ ጊዜ በፊት ድረስ በብሔራዊው ሸንጎ ብዙዎቹን መንበሮች ይዞ የነበረው የቀድሞው ፕሬዚደንት የዴሞክራሲያዊው የሴኔጋል ፓርቲ በምክርቤታዊው ምርጫ አሥራ ሁለት መንበሮችን አግኝቶዋል።  
አዲሱ ፕሬዚደንት ማኪ ሳል በፕሬዚደንታዊው ምርጫ ዘመቻ ወቅት ለማካሄድ ቃል የገቡትን የተሀድሶ ለውጥ ዕቅዳቸውን አሁን የብዙኃኑን የምክር ቤት እንደራሴዎች ድጋፍ ስላላቸው ገሀድ ማድረጉ እንደማይከብዳቸው ይጠበቃል። እንደሚታወሰው፡ ሳል ሥልጣን ሲይዙ ወደኃላ የቀረውን የሀገሪቱን የትምህርት ሥርዓት ለማሻሻል እና የኤኮኖሚውንም ዘርፍ ለማሳደግ ዕቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል። ከሴኔጋል ሕዝብ መካከል ሁለት ሦስተኟው አሁንም ማንበብና መፃፍ አይችልም።

Senegal's newly inaugurated President Macky Sall waves to supporters as he travels to the presidential palace to take up residence, in Dakar, Senegal Monday, April 2, 2012. Sall took the oath of office Monday in a ceremony held one week after the country's longtime incumbent conceded defeat only hours after polls closed. The presidential runoff vote solidified the country's reputation as one of the few mature democracies in western Africa, where the unpopular president was ousted at the ballot box instead of a coup. (Foto:Rebecca Blackwell/AP/dapd)

ፕሬዚደንት ማኪ ሳልፕሬዚደንት ማኪ ሳል በውጤቱ መሠረት የብዙኃኑን ድምፅ ቢያገኙም፡ የሚመሩት የሬፓብሊኳ ህብረት ፓርቲያቸው በቤኖ ቦክ ያር የፓርቲዎች ጥምረት ውስጥ ጠንካራው አካል ባለመሆኑ፡ አዲሱ ብሔራዊ ሸንጎ የፕሬዚደንቱን ሀሳብ በጠቅላላ በጭፍን የሚደግፍ አይሆንም። በዎሎፍ ቋንቋ ቤኖ ቦክ ያር የሚል መጠሪያ የያዘው ፡ ሲተረጎም የጋራ ተስፋ ህብረት የተሰኘው ጥምረት በርካታ ፓርቲዎችን ያቀፈ ነው። የቀድሞው ምክር ቤት የቀድሞው ፕሬዚደንት አብዱላይ ዋድ መንግሥት ያቀረባቸውን የሕግ ረቂቆች በጠቅላላ ካላንዳች ውይይት ያፀድቅ እንደነበረው ይታወሳል።
በሴኔጋላዊው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና ጋዜጠኛው ማም ሌ ካማራ አስተያየት፡ይህ አሰራር በአሁኒቷ ሴኔጋል አክትሞለታል። ወደፊት ሴኔጋል ውስጥ አንድ የሕግ ረቂቅ በምክር ቤቱ ለማሳለፍ በሚፈለግበት ጊዜ በተለያዩት ቡድኖች መካከል ብዙ ውይይት ማስፈለጉ አይቀርም።

« በዚህ አብላጫ ድምፅ ይዞዋል በሚባለው አካል ውስጥ በያንዳንዱ ሕግ ላይ ድርድር ይደረጋል። ይህም መንግሥት የሚያቀርባቸው ረቂቆች በምክር ቤት ተቀባይነት እንዳያጡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል። »

©Aliou Mbaye/PANAPRESS/MAXPPP - 01/07/2012 ; Dakar ; Senegal - DAKAR - JULY 1: Chief candidate of a coalition Demba Diop Sy speaks to the media after his vote in his district's polling centre during the general elections on July 1, 2012 in Dakar, Senegal. (Photo Aliou Mbaye/ Panapress) - DAKAR - 1 JUILLET: Demba Diop Sy, tete de liste d'une coalition s'adresse a la presse au bureau de vote de son quartier lors des elections legislatives. Dakar, Senegal, 1 juillet 2012. (Photo Aliou Mbaye/Panapress)

ዕጩ ዴምባ ዲዩፕ ሲ

ማም ሌ ካማራ እንደሚያስታውሱት፡ በምክር ቤታዊው ዘመቻ ወቅት ተፎካካሪ ዕጩዎች አዲሱ ምክር ቤት ከቀድሞው የተለየ እንደሚሆን ፡ የሕዝብ እንደራሴዎች የሚወከሉበት እንጂ የፕሬዚደንቱ ደጋፊዎች የሚሰባሰቡበት ሸንጎ እንደማይሆን ነበር ያስተጋቡት።

« እንደሚመስለኝ እስካሁን ከነበረው በተለየ ሁኔታ ብዙ ክርክር እና ውይይት የሚካሄድበት ቆራጥ ሸንጎ ብሔራዊ ሸንጎ ይሆናል፤ ምክንያቱም፡ እንደራሴዎቹ የፕሬዚደንቱን ፍላጎት የማሟላት እንደሌለባቸው በሚገባ ያውቃሉና። ብሔራዊው ሸንጎ ውሳኔዎች በክርክር እና በውይይት የሚደረስበት ቦታ ይሆናል። እንደራሴዎቹ ፍላጎታቸው ይህ ከሆነ ፡ በብዙ ጉዳዮች ላይ ተፅዕኗቸውን ሊያሳርፉ እና መንግሥት በሚያቀርባቸው ሀሳቦችም ላይ ብዙ ማሻሻያ ሊያደርጉ ይችላሉ። ይህ በርግጥ በብሔራዊው ምክር ቤት አዲስ ዓይነት አሰራር ያስተዋውቃል። »
አዲሱ ምክር ቤት የጋለ ክርክርና ውይይት የሚካሄድበት ብቻ ሳይሆን በብዛት ሴቶች እንደራሴዎችም በብዛት የሚወከሉበት ነው። በቀድሞው ምክር ቤት ውስጥ አንድ ሴት እንደራሴ ብቻ ነበረች። በአዲሱ የሴኔጋል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ግን ከ 150  እንደራሴዎች መካከል 64 ቱ ሴቶች ናቸው። ለሴቶች ተሳትፎ በጉልህ እንዲያድግና  በፖለቲካው ዘርፍ የፆታ እኩልነት እንዲኖር  በ 2010 ዓም በሀገሪቱ የወጣ ሕግ ድርሻ አበርክቶዋል። በዚሁ ሕግ አማካኝነት የሴቶችን የምክር ቤት ውክልና በተመለከተ ሴኔጋል በአፍሪቃ 56 ከመቶ  ውክልና ካስመዘገበችው ከርዋንዳ ቀጥላ ሁለተኛውን ቦታ ይዛለች።
ይህ አበረታቺና አስደሳች ዜና ቢሆንም፡ ድምፁን ለመስጠት የወጣው መራጭ ሕዝብ ቁጥር 37 ከመቶ እንኳን ያልሞላበት ድርጊት ብዙዎቹን ሴኔጋላውያንን ቅር አሰኝቶዋል። በመዲናይቱ ዳካር የሚገኘው የጀርመናውያኑ የኮንራድ አድናወር ተቋም ሰራተኛ ኡተ ቦካንዴ እንዳመለከቱት፡ በምርጫው ዘመቻ ወቅት የተካሄዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጅቶች የብዙ መራጭ ሕዝብ ትኩረትን አልሳቡም። የአንድ የምዕራብ አፍሪቃ የሲቭል ማህበረሰብ ባልደረባ ወይዘሮ ሀዋ ባ እንዳሉት ግን፡ የመራጭ ሕዝብ ተሳትፎ ንዑስ መሆኑ ለሴኔጋል አዲስ አይደለም።
« ያለፈው ታሪክ እንዳሳየው፡ በምክር ቤታዊው ምርጫ ሁሌም የመራጭ ሕዝብ ተሳትፎ በጣም ደካማ ነው። ግን መርሳት የሌለብን፡ ረጅምና ጠንካራ እንዲሁም ብዙ ክርክር ያሰከተለ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ከተካሄደ ብዙ ጊዜ አለማልፉ ነው። ከዚህ በተጨማሪ መራጩ ሕዝብ በምርጫው ዘመቻ ወቅት የቀረቡት አማራጮች የሱን ፍላጎት የሚያንፀባርቁ ሆኖ አላገኛቸው ሊሆን ይችላል። እንዳልኩት፡ እንደራሴዎቹ የሕዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ  የቆሙ አይመስለንም። ለፓርቲዎቻቸው እና ለፕሬዚደንቱ ጥቅም ነው የቆሙት። »

ፔተር ሂለ/ቡባ ጃሎ/አርያም ተክሌ

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic